DiscoverDW | Amharic - Newsየኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሹም ሽር
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሹም ሽር

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሹም ሽር

Update: 2025-12-16
Share

Description

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዲሱ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ካሣ ኃላፊነታቸውን ከተሰናባቿ ዶክተር እመቤት መለሰ ትናንት ሰኞ በይፋ ተረክበዋል። ዶክተር ኢሳያስ የባንኩ ፕሬዝንት ሆነው ከመሾማቸው በፊት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነበሩ።



ከፕሬዝደንቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በርከት ያሉ አባላት ተቀይረዋል። የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሣ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሳሙኤል ክፍሌ እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤልን ጨምሮ ሌሎች ስድስት አዳዲስ የቦርድ አባላት ተሾመዋል።



የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ ከዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢነታቸው ተነስተው በዶክተር ብሩክ ታዬ ተተክተዋል። በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ላይ የተደረገው መሠረታዊ ለውጥ “ያልተለመደ” እና “ግራ የሚያጋባ” እንደሆነ የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ።



የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ዶክተር ብሩክ ታዬ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከሚቆጣጠራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ ልማት ባንክ በመሆኑ አዲሱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ብሩክ ተጠሪነታቸው “ለማን ነው?” የሚል ጥያቄ የፋይናንስ ባለሙያው ያነሳሉ።



በልማት ባንክ ላይ ተግባራዊ የተደረገው የአመራር ለውጥ “ተቋማዊ ውጤታማነትን ለማሻሻል” ያለመ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ለዶይቼ ቬለ በኢ-ሜይል በሰጠው ምላሽ አስታውቋል። ባንኩ በመንግሥት “ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ብሔራዊ የልማት ጉዳዮች እና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የለውጥ አጀንዳ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ” የሹም ሽሩ ዓላማዎች ናቸው።



የመንግሥት የመዋዕለ-ንዋይ ክንፍ የሆነው ተቋም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ በሥሩ ከ40 በላይ ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን ወደፊት በሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተመሳሳይ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ለዶይቼ ቬለ ገልጿል።



ባለፈው ሣምንት የተሰናበቱት ዶክተር እመቤት ልማት ባንክን እንዲመሩ የተሾሙት በጥቅምት 2017 ነበር። በባንክ ሥራ ዘርፍ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያገለገሉት የቀድሞዋ ፕሬዝደንት በንብ ባንክ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ሠርተዋል።



ከዶክተር እመቤት በፊት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ከመስከረም 2013 እስከ ጳጉሜ 2017 ድረስ የመንግሥት ብቸኛ የፖሊሲ ባንክ የሆነው ተቋም ፕሬዝደንት ነበሩ። አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ከሰኔ 2010 እስከ መስከረም 2013፣ አቶ ጌታሁን ናና ከኅዳር 2009 እስከ ግንቦት 2010 ገደማ ድረስ ልማት ባንክን መርተዋል።



በባንኩ ረዘም ላሉ ዓመታት ያገለገሉት ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሳለ ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ ኢሳያስ ባህረ ናቸው። አቶ ኢሳያስ በመንግሥት ውሳኔ ከኃላፊነታቸው ከመነሳታቸው በፊት ለስምንት ዓመታት ገደማ ባንኩን በፕሬዝደንትነት መርተዋል።



ልማት ባንክ የእርሻ ሥራ እና ኢንዱስትሪን ጨምሮ ቁልፍ ለሆኑ የኢኮኖሚው ዘርፎች ብድር የማቅረብ ኃላፊነት ቢኖርበትም በርካታ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት አንድ የቀድሞ ባልደረባ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቀድሞ የተቋሙ ኃላፊ “ከባድ” ብለው ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል የተበዳሪዎች ውስን አቅም፣ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች እና የዕለት ተዕለት ሥራዎች ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነቶች ይገኙበታል።



ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት በሰጣቸው ብድሮች ምክንያት እስከ “40 በመቶ ደርሶ ነበር” ከተባለው የተበላሸ ብድር መላቀቅ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፈተና እንደነበር የቀድሞው ኃላፊ ገልጸዋል።



ዶክተር አብዱልመናን ልማት ባንክ “ብዙ ለአደጋ የተጋለጡ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እንዲያደርግ የተቋቋመ ባንክ ስለሆነ በኢንቨስትመንት አጠራጣሪ ባህሪ ያላቸውም ሰዎች ይቀርቡታል” ሲሉ ይናገራሉ።



“ዓላማው ኢንቨትመንትን ማበረታታት ስለሆነ እንደ መደበኛ ባንክም ጥብቅ ላይሆን ይችላል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ከፖለቲካ ንክኪ ካላጸዱት ይኸ ፈተና ወደፊትም የሚቀጥል ነው” የሚል ሥጋት አላቸው። የአስተዳደር እና የቦርድ ገለልተኝነትን ጨምሮ ለሥራ አፈጻጸሙ መመዘኛዎች በማስቀመጥ የፖሊሲ ባንክ የሚፈልገውን ነጻነት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።



የኢትዮጵያ ልማት ባንክ “የመንግሥት የልማት አቅጣጫን መሠረት በማድረግ አዋጪ ለሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች” ብድር የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም ነው። “በጊዜ የተገደበ ተቀማጭ” የሚቀበል ቢሆንም በዋናነት ሥራውን የሚያከናውነው ግን በመደበኛነት የደንበኞችን ተቀማጭ እየሰበሰበ አይደለም።



ተቋሙ በሚሰጣቸው ብድሮች ለትርፍ የተቋቋሙ “የንግድ ባንኮች የማይሸፍኑት ቦታ” ላይ ያተኩራል። “የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት ሲፈለግ ንግድ ባንኮች ብድር አይሰጡም። ምክንያቱም ሥጋት አለው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች እና ፋብሪካዎች የሚገጥማቸውን ክፍተት የመሙላት ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።



አዲስ ፕሬዝደንት የተሾመለት ባንክ ከሌሎች መሰል የፋይናንስ ተቋማት በተለየ የወለድ መጠኑ ከገበያ ዝቅ ያለ ብድር የሚሰጥ ነው። “ምክንያቱም ትልልቅ ፕሮጀክቶች በገበያ ዋጋ እንበደር ቢሉ ማንም ፍላጎት ኖሮት ወደዚያ ኢንዱስትሪ ውስጥ አይገባም” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል።



ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ቦንድ ሸጦ የመሰብሰብ ኃላፊነት የተሰጠው ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነበር። ልማት ባንክ ለሥራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የግል ባንኮች ቦንድ እንዲገዙ የሚያስገድደው አሠራር መንግሥት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲቀር ተደርጓል። በማሻሻያው መሠረት ልማት ባንክ የብድር ሰነዶች ወደፊት በካፒታል ገበያ በኩል ለሽያጭ ሊያቀርብ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።



አርታዒ ሸዋዬ ለገሰ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሹም ሽር

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሹም ሽር