DiscoverDW | Amharic - Newsየጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
የጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

Update: 2025-10-23
Share

Description

በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሐን ትኩረት አግኝተው ከተንሸራሸሩ አበይት ጉዳዮች የኢትዮጵያ ቭሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ማድረጉን፤ በደሴ መምህራን ኮሌጅ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች የሚሰጣቸው ወርሐዊ የቀለብ ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ ለችግር መጋለጣቸውን እና የዶላር ጭማሪና የኑሮ ውድነት የተወሰኑትን እናቀርባለን።



የቀጣዩ ምርጫ ከአሁኑ እያወዛገበ ስለመሆኑ





የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የ7ኛውንጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አድርጓል። ቦርዱ ይህን በማስመልከት በሐገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ውይይት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት ለማካሄድ ልዩ ልዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጻል። ቦርዱ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው የምክክር መድረክቦርዱ ያዘጋጀውን ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳው የምርጫ ጽ/ቤቶችን ከማደራጀት ጀምሮ እስከ ይፋዊ የምርጫ ውጤት ማሳወቂያ ድረስ ያሉትን ተግባራት ያካተተ መሆኑን ገልጻል። ይህን ተንተርሰው በቀጣዩ ምርጫ አስመልክተው ከተንሸራሸሩ ሐሳቦች የተወሰኑትን እናስደምጣለን።

ወደቀዳሚው አስተያየት ስናልፍ «ይህ ሁሉ ከገዢው ፓርቲ ጀምሮ ሁሉም ለግል ጥቅም እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም የሚፎካከሩት። ለኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ኑሮ አጀንዳው መሆን የነበረበት ዝንተአለም ጨለማ ውስጥ ለሚኖረው የአገሪቱን 85% ለሚሸፍናው ለገጠሬው ዜጋ ነበር። ለኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ኑሮማ ለአገሪቱ የጀርባ አጥንት እና እስትንፋስ ለሆነው ግብርና እና ገበሬን አጀንዳ ያረጉት ነበር። የግል ጥቅም ፈላጊዎች፤ ለህዝብ የሚጠቅም ፖለቲካ ስለሌላቸው ሁሌም አንዱን ህዝብ በዳይና ተበዳይ አስመስለው የዘር እና የጎሳ ፖለቲካ ያራምዳሉ። ሁሉም ቢደመር ለህዝብ የሚሆን ፖለቲካ የላቸውም ። ፎቶ እና ወሬ ብቻ። ልጅ ፈረደ መሠረት ነኝ ከጎጃም አገው ምድር የጃኖ የነፃነት አብዮት ንቅናቄ መስራችና ፕሬዚዳንት ።»

ኤፍሬም የአቤ ልጅ «የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ከክልልጄምሮ እስከ ቀጠና አደረጃጀቱ አዲስ ከሜሆኑ አንፃር አዲስ ቢሆን ይሜረጣል።» ብለዋል። ደምሰው ጥላሁን ያሰፈሩት ሐሳብ ደግሞ

«በአብዛኛው የአማራ ክልል፣ በተወሰኑ የኦሮሚያ ክልል፣ ትግራይ ክልል እና በአንዳንድ የአፋርና ቤንሻንጉል ክልሎች አስቻይ ሁኔታዎች አሉን ? የተሟላ ምርጫ እንዲሆን ከወዲሁ ሰላም ላይ መሰራት ቢቻል። ካልሆነ ግን ውጤቱን የማይቀበል አካል እንዳይፈጠር ያሰጋል።» ገዳ ቢሉሱማ ኦሮሞ በሚል የተጻፈ አስተያየት እንዲህ ይላል።

«የ7 ኛው ሕዝባዊ ምርጫ ቅድመ ሁኔታ አልተሟላም ፣

1. የሕዝብ ተሳትፎ አለመኖሩ፣ ምርጫው ሕዝባዊ በመሆኑ ሕዝቡ የዘንድሮ ምርጫ አጀንዳ ባለደረገበት ፣

2. የሕግ በላይነት አለመረጋገጡ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደራጀት የሰብዓዊ እና ሕገ መንግስታዊ መብት መሆኑ እያለ በፍርድ ቤት ውሳኔ ፍቃዳቸው የተመለሰላቸው እነ ገዳ ቢሊሱማ ፓርቲ ያሉ ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው ፓርቲዎች ሆነ ብሎ ከምርጫ ውድድር ውጭ እየተደረገ በመሆኑ፣

3. ምርጫው የመራጮች ምስጢር አለመጠበቁ፣

በሕገ መንግስቱ መሠረት ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሁሉ አቃፊ እና የመራጮችን ምስጢር የጠበቀ መሆን አለበት የሚለው በመተላለፍ ለአንድ ዕጩ ተወዳዳሪ ከ2000 የድጋፍ ፊርማ የማቅረብ ግዴታ መቀመጡ የመራጮችን ደህንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ፣

4. ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል በር መጥበቡ፤ ሰሞኑን አምሳደር ኩማ ደመቅሳ እንዳሉት ታጥቀው ጫካ የገቡት ኃይሎች የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ስለተዘገባቸው ሊሆን ስለሚችል ከሁሉም ቅድሚያ ለሕዝብ ሰላም እንዲገኝ መነጋገር እና የፖለቲካ ውይይት እና ድርድር አለመደረጉ፣

5. የተመጣጣኝ የምርጫ አላመታወጁ፣

ሁሉም ፓርቲዎች በአገኙት የሕዝብ ድምጽ የመንግስት መቀመጫ ያገኛሉ የሚለው የተመጣጣኝ የምርጫ ሕግ ሁሉም ፓርቲዎች ተስማምተው ቢፈርሙም በሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ አለመታወጁ .ወዘተ ምክንያቶች የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ ሁኔታ አላሟላም ።

ከገዳ ቢሊሱማ ፓርቲ»





ከገዳ ቡሊሱማ ፓርቲ አስተያየት ወደ ማትዮስ ባልቻ ስናልፍ «በእኔ እምነት ምርጫው ለሦስት ዓመት ቢራዘም ይበጃል ። በዚህ ሀገር ምርጫ ማድረግ በጀትና ጊዜ ከማባከን ያለፈ ፋይዳ የለውም።» የሚል አስተያየት አስፍሯል።

አወል የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ቦርዱ በቅድመ ዝግጅት ላይ አበረታች የሆኑ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።» ብለዋል። ሳሙኤል ኬሾ «ህገመንግቱ በሚፈቅደው መሠረት ምርጫው መካሄድ አለበት ። የማይፈልግ ፓርቲ ካለ በፎርፌ የመውጣት መብት የተጠበቀ ነው፤ ብቻ ምርጫ ይካሄድ።» ብለዋል።

፤እስቲበል ዋሴ «በየትኛው ሰላም ነው ምርጫ የሚካሄደዉ? ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምርጫ እንዴት ይታሰባል? ተቃዋሚ የምትባሉትስ እንዴት አሁን አገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ምርጫ መካሄድ ይቻላል ብላችሁ ትቀበላላችሁ ?ለነገሩ ምን ተቃዋሚ አለ!!! በማለት 3 ቃለአጋኖ በማድረግ አስተያየታቸውን ዘግተዋል።

ተስፋሁን አብዩ፤ «ከ10 ዓመት በላይ የሆናቸዉን የወረዳ፣ ከተማና ቀበሌ ምክር ቤቶች ምርጫ ቦርድ በአዲስ መተካት ባለመቻሉ ከክልል በታች ያሉ ወረዳ፣ ከተማና ቀበሌ ምክር ቤቶች ስማቸዉ ብቻ ቀርቷልና ምርጫ ቦርድ አካባቢያዊ ማሟያ ምርጫ በማድረግ አዲስ ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ ሀላፊነቱን ቢወጣ መልካም ነው።» የሻምበል አላመራው የጻፉት አስተያየት «የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፤ ገዢው ፓርቲ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላምን ሁኔታ ትኩረት በመስጠት ሊያረጋግጥና 7ኛ ሀገራዊ ምርጫን ማስኪዬድ እንዳለበት ቦርዱ ጫና ሊያደርግ ይገባል።

ገዢው ፓርቲ(መንግስት) ሆን ብሎ ምርጫን ለማራዘም ዜጎች እርስ በርስ እንዲጋጩና ሰላም እንዳይሰፍን ምርጫው እንዲራዘም እየተደረገ ያለውን ሴራ ቦርዱ ውሳኔ ሊያስቀምጥ ይገባል።

ካልሆነ ግን ቦርዱም የተሰጠውን ስልጣን ወደኋላ በመተው ለገዢው መንግስት አስፈፃሚ መሆኑን በግልፅ ያሳያል።»





የደሴ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተማሪዎች ስሞታ





ወደ ሁለተኛው ርዕሳችን ስናልፍ ወደ ደሴ ይወስደናል። ከ40 አመት በላይ መምህራንን በማሰልጠን የሚታወቀዉ የደሴ መምህራንማሰልጠልኛ ኮሌጂ በመምህርነት በዲግሪና ዲፕሎማ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች በወር ለምግብ የሚሰጣቸዉ 760 ብር ለመኖር ስላላስቻላቸዉ ሰዉ ቤት ተቀጥረዉ በቤት ሰራተኝነት ከጫካ ጭራሮ እየለቀሙ ለምግባቸው የሚሆን እንጀራ እየጋገገሩ ለመማር እንደተገደዱ መዘገባችን ይታወቃል።

ተማሪዎቹ ጦርነቱ ላይ የኑሮ ዉድነት ተጨምሮ ትምህርት ለመማር ተቸግረናል ይላሉ። ነገ ተማሪዎችን ለማስተማር የሚሰለጥኑ መምህራን የሚማሩትን ሳይሆን የሚበሉትን በማሰብ የማገዶ እንጨት በመልቀም፣ የቀን ጉልበት ሠራተኛ በመሆን፣ እንዲሁም ለራሳቸው ለምግብነት የሚውል እንጀራ በመጋገር ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ተማሪዎቹ በምሬት ገልጸዋል። ይህን ዜŀn ተንተርሶ በርካታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል። የተወሰኑትን እናስደምጣችሁ።

«የ ግፍ ግፍ ነዉ።760ብር ካድሬዉ 1 መክያቶ ይጠጣታል። የሚል አስተያየት ያሰፈሩት ንጉስ ቸኮል የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።

ሐይለ አማረ ያሰፈሩት አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል። «መምርነት በተለይም ከዘመነ ----ወዲህ በደንብ እንደሞተ ማሳያ ነው። በተለይ አሁን አሁንማ የሌሎች ሙያዎች የትምህርት አሰጣጥ አጠቃላይ ሁኔታዎች በተቋማት ውስጥ ተመቻችቶላቸው እየሰለጠኑ ባለበት ጊዜ የእነዚህ ተማሪዎች ደግሞ በተቃራኒው እንጨት ለቀማ መዋላቸው ይገርማል!!!!» በማለት በ4 ትምህርተ አንክሮ አስተያየታቸውን ቛጭተዋል።

የማሪያም ልጅ። «መማር ምን ጠቀመን አስናቀን እንጂ፤ የተማረ መኪና የለውም ። የተማረ ቤት የለውም ።

የተማረ ሀብት የለውም ። አሁን ያልተማረ ሀብታም የሆነባት ሀገር እየተፈጠረች ነው። የተማረ የሚያፍርባ የካድሬ መጫወቻ ሆናለች ምን እናድርግ ጎበዝ? በማለት ጥያቄ አዘል መልዕክት ፅፈዋል።

ወደ መልካሙ አለነ አስተያየት ስናልፍ «መነሻችሁ መምህርነት ይሁን እንጂ መዳረሻችሁ ስለማይታወቅ በርቱ!!!!

የትምህርትን ፈተና የሚያቀው የተማረ ብቻ ነው። የመምህርነት ሙያን የሚንቁ ደግሞ በሙያው ያሉት ተገቢ ጥቅም ባለማግኘት ነው። ከሙያው ውጪ የሆኑት ደግሞ መምህር የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን የማያውቁ ናቸው!!!»

ፍጹም ናታን ደግሞ ይሄ ምን ይገርማል የባሰ አለ የሚል አስተያየት ነው ያሰፈሩት «450 የሚከፈልበትም አለ ይሄ ምን ይገርማል?» ሃይለ መስቀል ሃዋዝ «መምህርነት ከዚህ ይጀምራል ትኩረት ማጣቱ።» የሚል አጭር አስተያየት አስቀምጧል።

ልዑል ደምሴ፤ «እኛም ከሱ ተመርቀን ስራ ተቀጥረን እንደገናም ዩኒቨርሲቲ እስከ 2ኛ ድግሪ ተምረን ለውጥ የለም አባቴ !!!» ሲሉ ጀማል መሐመድ ደግሞ «ጭራሮ ቢለቅሙም ሰው ቤትም ቢገቡም ምን ቸግር አለው? ምን አልባት የከተማ ልጆች ካሉ ሊከብድ ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ የባሰ ህይወት ለመጣ ሰው ይህ ቀላላቸው ነው። ለእነሱ ይህ አይቸግራቸውም። እንዲማሩ ማንም አላስገደዳቸውም። ፍላጎቱ ካላቸው ማቋረጥ ይችላሉ በግዴታ ስላልሆነ ብየ ነው።» ሲሉ ማስረሻ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «መምህር ስትሆኑ ያልፍለችሆል በተስፋ ተመሩ።» ብለዋል።

ብርሃኑ ረጋሳ «ቅንጡ ሎጆችና መዝናኛዎችን ማን ይስራቸው?!!!» የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየት ፅፈዋል። ሰምራዊት፤ «አዎ እውነት ነው፤ ደሴ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ኮሌጆች የሚሰለጥኑ ሠልጣኞች ብሩ አልበቃንም እያሉ ችግር ላይ መሆናቸውን የመረጃ ምንጮቻችን ገልፀዋል!! መፍትሔ ይፈለግላቸው!!» ነው ያሉት።



የዶላር ምንዛሪ ማሻቀብና የንሮ ውድነት





የዶላር ምንዛሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ሣምንት ብቻ ከአምስት ብር በላይ ጨመረ የሚል ዜና የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት ከሳቡ ሌላኛው ርዕስ ነው።

ባለፈው አንድ ሣምንት ንግድ ባንክ ዶላር የሚገዛበት እና የሚሸጥበት ተመን አምስት ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ ከፍ ብሏል። የብሔራዊ ባንክ አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን በአንጻሩ 150 ብር ከ90 ሳንቲም ደርሷል። ብር በውጭ ምንዛሪ ገበያው መዳከሙን ሲቀጥል ብሔራዊ ባንክ እርምጃ እንደሚወስድ በድጋሚ አስጠንቅቋል። የዶላር ምንዛሪ ሳያቋርጥ ማሻቀብና የኑሮ ውድነት ጋር አያይዘው ከተጻፉ በርካታ አስተያየቶች የተወሰኑትን እናስደምጣለን።





ሩሁል አሚን በሚል መጠሪያ፤ «አይ ሃገራችን እንደ ዚምባብዌ ገንዘብ በግመል ጭነን ልንገበያይ ነው፤ አዝናለው ወላሂ» የሚል አስተያየት ሲጽፉ ሙላት ደሴ ደግሞ «መንግስት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ብሎ ሃገራዊ የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርግም የበለጠ ንሯል።ለማንኛውም መንግስት የገቢያ የማረጋጋት ስራ ቢሠራ ጥሩ ነበር ።» ብለዋል።

«የመጨረሻ መዳረሻ ለጊዜው ባይታወቅም ሰሞነኛው የውጭ ምንዛሪ የሩጫ እሽቅድድም 200 ብር ለመድረስ ይመስላል።ከዚያስ? የሚለው ጥያቄ በሂደት ማየት ነው።» ያሉት ማትዮስ ገሌቦ ናቸው።

ኤርሚያስ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፤ « መንግሥታችን አንዴ ከዓለም አገራት ሁለትኛ ደረጃ አድገናል ይለናል፤ ሁለተኛ ደረጃ ሲባል ከአሜሪካ ቀጥለን ማለቱ ነው። ሰሞኑን ከአፍራካ ሁለትኛ ሁነናል ይለናል። ከአፍሪካ ሁለትኛ ደረጃ ሲለን ከደቡብ አፍሪካ ቀጥለን ማለቱ ነው። እኛ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ ከልጆቻቻን ጋር አጣላን። ልጆች ይህን ግዙልን ይህን ግዙልኝ እያሉ ኑሮን እንደነፈግናቸው ነው ያዩን። አባ! አንተ አባቴ አይደለህም! እማ! አንች እናቴ አይደለሽም! እያሉን ተቸግረናል። ልጅ የኛን ባዶ ቤት እና የኛን ባዶ ኪስ አያውቅም፤ ግራው ገብቶናል።» ሲሉ ጌታቸው የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው «በዶላር ጭማሪ ተጎጂው በዋናነት ገቢው የተገደበ ስለሆነ መንግስት ሰራተኛ ነው።» የሚል አጭር አስተያየት ሰጥተዋል።

መንግስቱ ቱፋ ያስቀመጡት ሐሳብ የዝግጅታችን ማሳረጊያ ነው።

የኢትዮጵያውያን ኑሮ አልተሻሻለም። ክቡርነትዎ ነጋዴዎች ቀን ከቀን ዋጋ እየጨመሩ ናቸው። ማክሮ ኢኮኖሚ እያደገ ከሆነ የዜጎች ኑሮም መሻሻል አለበት ባይ ነኝ። ሌላው የግቤ ሶስት ጉዳይ መታሰብ አለበት እስከ ኬኒያ ናይኖቢ ብርሃን እየሰጠን ብዙ ሚልዮን ዶላር እያስገባን በጨለማ ለምናደር ለእኛ ለዳውሮ ህዝብ መታሰብ አለበት።

ስለዚህ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት (ማክሮ ኢኮኖሚ) ከዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር በቀጥታ የሚዛመድ አለመሆኑን ልብ ማለት አስፈላጊ ነው። እድገቱ በኢንፍራስትራክቸር፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ሊከሰት ይችላል፣ ነገር ግን የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ያለው ተጽዕኖ በቀጥታ ከዋጋ ንረት፣ ከደመወዝ እና ከማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር የተቆራኘ ነው።

የዋጋ ግሽበት፤ የዋጋ ግሽበትበኢትዮጵያ እንደ ሁሉም አገር አንድ ዋና ፈተና ነው። ይህ በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የአለም ኢኮኖሚ ሁኔታ እና የአገር ውስጥ ምርት እና አገልግሎት አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ነው። መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ በፖሊሲ እና በቁጥጥር ሥርዓቶች ላይ ሊሠራ ይችላል።

የኢነርጂ ፕሮጀክቶች፤ ከኬኒያ ጋር ያለው የኤሌክትሪክ ሽግግር እንደ ረጅም ጊዜ የኢንፍራስትራክቸር ኢንቨስትመንት ሊታይ ይገባል። እንደነዚህ አይነት ፕሮጀክቶች አገርን የሚያገለግሉ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ በቀጥታ ለማሻሻል የሚያስችሉ ባይሆኑም፣ ረጅም ጊዜ ውስጥ ለኢኮኖሚ እድገት እና ለኢነርጂ ዋስትና አስፈላጊ ናቸው።

ማህበራዊ አገልግሎቶች፤ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በጤና፣ በትምህርት እና በማህበራዊ ደህንነት መስኮች ውስጥ ያሉ አገልግሎቶች መሻሻል አለባቸው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ቢሄድም፣ ይህ እድገት በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ እንዲኖረው የሚያስችሉ የፖሊሲ እና የማህበራዊ አገልግሎት ማሻሻያዎች አስፈላጊ ናቸው። የኢነርጂ ፕሮጀክቶች እንደ ረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ተደርገው ሊታዩ ይገባል፣ ነገር ግን በዋጋ ግሽበት እና በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ያለው ትኩረት አስፈላጊ ነው።»





ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር



አዜብ ታደሰ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት