DiscoverDW | Amharic - Newsየፕላስቲክ ብክለት ተጋላጭነት የመቀነስ ጥረት
የፕላስቲክ ብክለት ተጋላጭነት የመቀነስ ጥረት

የፕላስቲክ ብክለት ተጋላጭነት የመቀነስ ጥረት

Update: 2025-12-16
Share

Description

በደቡብ ኮሪያዋ የደሴት ከተማ ጄጁ ላይ በቅርቡ ዓመታዊ ጉባዔውን ያካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ መርኀግብር (UNEP) የፕላስቲክ ቆሻሻን ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳው አድርጎ መክሯል። በጎርጎሪዮሳዊው 2024 ዓ.ም ብቻ ዓለማችን ከ400 ሚሊዮን ቶን በላይ የፕላስቲክ ቆሻሻ ማመነጨቷ በዚሁ ጉባዔ ላይ ተጠቅሷል። ብክለቱ በምድር ላይ የተጋረጠ ከባድ የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር አደጋ መሆኑ በተገለጸበት በዚሁ ጉባዔ የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ ምላሽ ያሻቸዋል በተባሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይም ምክክር ተደርጓል።



የባለሥልጣኑ ጥናት ምን ይዟል?



በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ150 በላይ የታሸገ ውኃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ከኢትዮጵያ የመጠጦች አምራች ኢንዱስትሪ ማሕበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በተለይም የታሸጉ ውኃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች መበራከትን ተከትሎ የፕላስቲክ ብክለት አደጋ ተጋላጭነት እየጨመረ መጥቷል።



በአገሪቱ ከሚታየው የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለት ውስጥ 34 በመቶ ያህሉ ከለስላሳና ከውኃ መጠጥ ኮዳዎች ጋር የተያያዘ ለመሆኑን የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በ2017 ዓ.ም ባደረገው ጥናት አመልክቷል። ትልቁ ችግር ታዲያ በፕላስቲክ የታሸጉ መጠጦችን ማምረቱ ላይ ሳይሆን ከአገልግሎት በኋላ የሚወገዱበት መንገድ የአካባቢ ብክለት መንሥኤ እየሆነ መሆኑ ላይ ነው። ተገቢ የአወጋገድ ሥርዓትን ከመዘርጋት ጎን ለጎን በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ያገለገሉ ፕላስቲኮችን መልሶ በጥቅም ላይ የማዋል ጅማሬዎችን ማስፋት እንደሚገባ በጥናቱ ተጠቅሷል።





ያገለገሉ ፕላስቲኮችን መልሶ የመጠቀም ጥረት በሀዋሳ



በሀዋሳ ከተማ በጥቅም ላይ የዋሉ የፕላስቲክ ኮዳዎችን በመሰብሰብ መልሶ የመጠቀም ሥራ በ2010 ዓ.ም ነው የተጀመረው። በከተማው ዳርቻ ላይ በተዘጋጀው የፕላስቲክ ማከማቻ ሥፍራ በሀዋሳና በዙሪያው ከሚገኙ ከተሞች የተሰበሰቡ የፕላስቲክ ኮዳዎች ቁሳዊ ይዘታቸውን ለመቀየር በማሽን እንዲዳመጡ ይደረጋል። በፕላስቲክ መልሶ መጠቀም ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት 20 ማሕበራት መካከል የሀዋሳ ውበት ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድና መልሶ መጠቀም ማሕበር አንዱ ነው።



የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ሄኖክ ዶንጋቶ እንደሚሉት አሁን ማሕበራቸው በቀን ከአምስት ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ያገለገሉ የፕላስቲክ ኮዳዎችን እየሰበሰቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በዚህም በከፊል ሂደት ውስጥ ያለፉ ፕላስቲኮች ትስስር በፈጠሩባቸው ኩባንያዎች አማካኝነት ወደ ሙሉ ምርትነት እየተለወጡ መሆኑንም አቶ ሄኖክ ጠቅሰዋል።



የመልሶ መጠቀም ዘርፈ ብዙ ጥቅም



በማሕበራቱ የተሰበሰቡትና በከፊል የተዳመጡት የፕላስቲክ ኮዳዎች አዲስ አበባ፣ ሞጆ እና ቢሾፍቱ ወደሚገኙ ኩባንያዎች ይላካሉ። በውጤቱም የተዋረሰ ፀጉር / የሴቶች ዊግ/ እና አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ የፕላስቲክ ዕቃዎች እንደሚመረትባቸው የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ሄኖክ ገልጸዋል።



የመልሶ መጠቀም ሥራው ያስገኘው ጠቀሜታ የአካባቢ ብክለትን መከላከልና በምርት ግብዓት አቅርቦት ብቻ እንዳልሆነ የጠቆሙት ሰብሳቢው «በእኛ ማሕበር ብቻ 96 ቋሚ እና 1,500 የዕለት ሠራተኞችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ አድርጓል» ብለዋል።





የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ



በሀዋሳ ከተማ አስተዳዳር የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አመለወርቅ ገብሩ በሀዋሳ የሚገኙ ማሕበራት በዚህ ረገድ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለው ያምናሉ። ማሕበራቱ ባይኖሩ ኖሮ የሀዋሳን ሐይቅ አሁን ባለው ሁኔታ አናገኘውም ነበር የሚሉት አቶ አመለወርቅ «ቀደም ሲል የፕላስቲክ ኮዳዎች የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎችን በመዝጋት ያስከትሉ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ለማስቀረት ተችሏል። እንዲሁም ፕላስቲኩ ወደ ሐይቁ በመግባት በሐይቁ ብዝኀ ሕይወት ላይ ደቅኖ የነበረውን አደጋ ለመቀነስ አስችሏል» ብለዋል።



በአሁኑ ጊዜ የማሕበራቱ አመራሮችና ሠራተኞች በተሠማሩበት ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እየሰጡ እንደሚገኙ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ «በተጨማሪም እንደየአፈጻጸማቸው ጊዜያዊም ቢሆን የመሥሪያ ቦታ አመቻችተናል። ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በየዓመቱ ዕውቅና በመስጠት ለማበረታታት ጥረት እየተደረገም ይገኛል» ብለዋል።



ሸዋንግዛው ወጋየሁ



ሸዋዬ ለገሠ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የፕላስቲክ ብክለት ተጋላጭነት የመቀነስ ጥረት

የፕላስቲክ ብክለት ተጋላጭነት የመቀነስ ጥረት

ሸዋንግዛው ወጋየሁ