DiscoverDW | Amharic - Newsየዶላር ምንዛሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ሣምንት ብቻ ከአምስት ብር በላይ ጨመረ
የዶላር ምንዛሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ሣምንት ብቻ ከአምስት ብር በላይ ጨመረ

የዶላር ምንዛሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ሣምንት ብቻ ከአምስት ብር በላይ ጨመረ

Update: 2025-10-22
Share

Description

ዶላርን የመሳሰሉ የውጭ ሀገራት መገበያያ ገንዘቦች የምንዛሪ ተመን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ሣምንት ውስጥ ብቻ ከአምስት ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል። የመንግሥት “የፖሊሲ ባንክ” ተደርጎ በሚቆጠረውን ንግድ ባንክ የዶላር ምንዛሪ ተመን በመስከረም ወር የጨመረው በ1.4 በመቶ ገደማ ብቻ ነበር።



ባንኩ የውጪ ሀገራት መገበያያ ገንዘቦች የሚገዛበት እና የሚሸጥበት መደበኛ ተመን ግን ባለፉት ቀናት ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል። ለውጡ መታየት የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 150 ሚሊዮን ዶላር ለ31 ባንኮች ካከፋፈለበት 10ኛው ጨረታ በኋላ ባሉት ቀናት ነው።



ጨረታው በተካሔደበት ዕለት ማለትም ጥቅምት 04 ቀን 2018 ንግድ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ141.0986 ብር ገዝቶ 143.9206 ብር ይሸጥ ነበር። ከሣምንት በኋላ ባንኩ በዛሬው ዕለት ዶላር 146.5986 ብር ገዝቶ 149.5306 ብር ይሸጣል።



በዚህ መሠረት ባለፈው አንድ ሣምንት ንግድ ባንክ ዶላር የሚገዛበት እና የሚሸጥበት ተመን አምስት ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ ከፍ ብሏል። በንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ባለፉት ሰባት ቀናት የታየው ለውጥ 3.9 በመቶ ገደማ ነው።



የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመደበኛ እና ትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያዎች መካከል “ያለውን የተመን ልዩነት ሁልጊዜ ለመቆጣጠር የመሪነት ሚና” እንደሚጫወት የባንክ ባለሙያው አቶ ባህሩ ያሲን ይናገራሉ። “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ” በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው የተመን ልዩነት “እየሰፋ ስለመጣ ያንን ለማጥበብ” ንግድ ባንክ “ሚና እየተጫወተ” እንደሚገኝ አስረድተዋል።



ሌላው ገፊ ምክንያት በባንኮች እና በመስከረም 2017 ፈቃድ በተሰጣቸው የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መካከል ያለውን የተመን ልዩነት ማረቅ ይመስላል። የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የዶላር የምንዛሪ ተመን ከባንኮቹ በጣም ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል። ሮሐ የውጭ ምዛሪ ቢሮ ዛሬ አንድ ዶላር በ165 ብር ከ25 ሣንቲም ገዝቶ በ168 ብር ከ56 ሣንቲም ይሸጣል። ዮጋ የውጭ ምንዛሬ ቢሮ በ164 ብር የገዛውን ዶላር በ167 ብር ከ28 ሣንቲም ይሸጣል።



የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ተመን ከመደበኛው ገበያ ከፍ ማለቱ ባንኮች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ እንደሚጎዳ አቶ ባህሩ ተናግረዋል። ይህ “የትይዩ ገበያውን የተወሰነ እያነቃቃው” እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ባህሩ ከባንኮች የምንዛሪ ተመን ጋር “ያለውን ልዩነት ለማስተካከል” የንግድ ባንክ ዋጋ ከፍ እንዳለ አብራርተዋል።



መንግሥት በኃይል ሊቆጣጠረው በሚሻው የትይዩ ገበያ በአንጻሩ ዶላር እስከ 174 እየተመነዘረ እንደሚገኝ ዶይቼ ቬለ አዲስ አበባ እና ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ነጋዴዎች ለመገንዘብ ችሏል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምንዛሪ ተመኑን ባለፉት ቀናት በከፍተኛ መጠን ቢያሳድግም አሁንም ከብሔራዊ ባንክ አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን በታች ነው።



ዛሬ ረቡዕ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያያደረገው አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን 150 ብር ከ90 ሳንቲም ደርሷል። ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ የባንክ ባለሙያነት ያገለገሉት የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ቢሮ ዳይሬክተር ወርቁ ለማ ንግድ ባንክ በሚያገኘውም ይሁን በሚያቀርበው የውጭ ምንዛሪ “ኢንዱስትሪውን ሊያንገጫግጭ የሚችል ሚና” እንዳለው ይናገራሉ።



“ገበያው ራሱ የአቅርቦት እና የፍላጎት የተመጣጠነ ሚዛን ላይ የመድረስ እና መረጋጋት ገና የሚቀረው ይመስለኛል” የሚሉት አቶ ወርቁ “ንግድ ባንክም ቢሆን በዚሁ ምህዋር ውስጥ ነው ሊጫወት የሚችለው። ለብቻው ከአቅርቦት እና ከፍላጎት ውጪ በሆነ ሁኔታ manipulate ማድረግ ይችላል ብዬ አላስብም” የሚል አቋም አላቸው።



ባለፈው ሣምንት እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ የግል ባንኮችም በዶላር መግዣ እና መሸጫ ተመናቸው ላይ ማሻሻያዎች አድርገዋል። የግል ባንኮች ዶላር የሚገዙበትን እና የሚሸጡበትን ለመወሰን የንግድ ባንክን ተመን ጨምሮ የተወዳዳሪዎቻቸውን ዋጋ ያጠናሉ። በአብዛኞቹ ባንኮች መካከል ያለው የተመን ልዩነት ከአንድ ብር የበለጠ አይደለም።



ለምሳሌ ያክል በዛሬው ዕለት አንድ ዶላር አቢሲኒያ ባንክ በ148.2034 ብር፣ አዋሽ ባንክ በ147.4999 እንዲሁም አማራ ባንክ በ147.5003 ይመነዝራሉ። የመሸጫ ተመናቸውም እንዲሁ ተቀራራቢ ነው።



ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሲያወጣ አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን “ብዙ ጊዜ” እንደመነሻ ሆኖ ያገለግላል። የጠየቁትን ማግኘት የሚችሉት ለብሔራዊ ባንክ አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን የተጠጋ ዋጋ የሰጡ ባንኮች ናቸው። የግል ባንኮች “ወደዱም ጠሉም ከብሔራዊ ባንክ አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን ጋር የተቀራረበ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማውጣት ስለሚጠበቅባቸው ንግድ ባንክ ባሻሻለ ቁጥር” ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርባቸው አቶ ባህሩ ተናግረዋል።



የግል ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ለሚሰጡት አገልግሎት “ከአራት በመቶ በላይ ማስከፈል አትችሉም” የሚል ሕግ ብሔራዊ ባንክ እንዳወጣ የሚናገሩት አቶ ባህሩ የግል ባንኮች ተመናቸውን ከንግድ ባንክ ጋር ካላስተካከሉ በገበያው ከሚኖር የውጭ ምንዛሪ ብዙውን ንግድ ባንክ ሊወስድ የሚችልበት ዕድል እንደሚፈጠር አስረድተዋል። ይህ ባንኮቹ መንግሥታዊውን ተቋም እየተከተሉ የውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ተመናቸውን እንዲያስተካክሉ ያስገድዳል።



ባንኮቹ በውጭ ምንዛሪ ገበያው በሚያደርጉት ፉክክር የተለያየ መጠን ያለው ጉርሻ ለመስጠት ቃል ይገባሉ። በጉርሻ መልክ የሚሰጡት የገንዘብ መጠን በአብዛኛው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብ በሚልኩባቸው የበዓላት ወቅቶች የሚዘወተሩ ቢሆንም ፉክክሩ በመርታቱ ይመስላል እስከ ዛሬ ዘልቀዋል። አቢሲኒያ ባንክ ሁለት በመቶ፣ አዋሽ ባንክ ዘጠኝ በመቶ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 10 በመቶ ጉርሻ ለመስጠት ቃል ይገባሉ።



ንግድ ባንክ በገንዘብ ማዘዋወሪያ መተግበሪያዎች እና በዓለም አቀፍ አስተላላፊዎች በኩል ሐዋላ ለሚቀበሉ ደንበኞቹ “10 ብር ተጨማሪ ጉርሻ” እንደሚሰጥ ቃል ይገባል። በዚህም መሠረት ባንኩ “ከጉርሻ ጋር” ዶላር የሚመነዝርበት ተመን 5 ብር ከ80 ሣንቲም ገደማ ጨምሮ ዛሬ 159.5306 ብር ደርሷል። አቶ ባህሩ ግን የዶላር ትክክለኛ ዋጋ የባንኮቹ መደበኛ የምንዛሪ ተመን ቃል ከሚገቡት “ጉርሻ ጋር” ተደምሮ እንደሆነ ይሞግታሉ።



የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ አሁንም እንዳልተረጋጋ ያስታወሱት አቶ ወርቁ “በቀጣይነትም የብር መዳከም ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል” የሚል እምነት አላቸው። ይህ ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ በምትሸምታቸው ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት ሊያስከትል የሚችል ነው።



የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ “በሀገር ደረጃ በጣም ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አለ” በማለት ገበያውን ለማረጋጋት ሞክረዋል። የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ክምችት “አቅም በጣም እየጨመረ” መሆኑን የገለጹት ዶክተር እዮብ ማዕከላዊው ባንክ “በተከታታይ” በሚያካሒዳቸው የውጭ ምንዛሪ ጨረታዎች ለባንኮች እንደሚያከፋፍል ቃል ገብተዋል።



ዶክተር እዮብ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ የሐዋላ አስተላላፊዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የውጭ ምንዛሪ ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥታቸው ትይዩ ገበያው ላይ እርምጃ ለውሰድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። “ሽብርተኝነትን በገንዘብ የሚደግፉ” ወይም “በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሠማሩ የተወሰኑ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት እንዳሉ ደርሰንበታል” ያሉት እዮብ “በጣም የተናበበ፣ የተቀናጀ ሰፊ እርምጃ” እንደሚወሰድ ተናግረዋል።



ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም በትይዩ ገበያ ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ሲወስድ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ የሚያዘዋውሩ አራት ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ውንጀላ አቅርቦ ነበር። አራቱ ድርጅቶች ሸጊ፣ አዱሊስ፣ ራማዳ ፔይ (ካህ) እና ታጅ የተባሉ የሐዋላ አስተላላፊዎች ናቸው።



ማስጠንቀቂያያቸው “የመጨረሻ” መሆኑን በአጽንዖት የተናገሩት የብሔራዊ ባንክ ገዥ “የኢትዮጵያ መንግሥት ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ የሚቆጠብ አይሆንም” ሲሉ ተደምጠዋል። ብሔራዊ ባንክ የሐዋላ አስተላላፊዎች የሚጠቀሙባቸውን አካውንቶች “በመዝጋት ብቻ የሚመለስ እንዳልሆነም” የተናገሩት ዶክተር እዮብ ላኪ እና ተቀባዮችን “ያካተተ ሰፊ የማጥራት ሥራ ሠርተናል። ወደ ተቀናጀ እርምጃ እየገባን ነው። ገንዘብ በእነዚህ ሕገ-ወጥ ተቋማት በኩል የሚልኩ ዜጎቻችንም ከዚህ እንዲቆጠቡ ማሳሰብ እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።



ማሳሰቢያቸው ከሐዋላ አስተላላፊዎች ጋር የሚሠሩ አስመጪዎች እና ላኪዎች እንደሆነ ጠቅሰው “የምንወስደው እርምጃ የማያዳግም የኢትዮጵያን ሕግ የጠበቀ፤ የዓለም አቀፍ ሕግን የጠበቀ የተናበበ” እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።



በመደበኛ እና ትይዩ ገበያዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ “ዋና መፍቻ መንገዱ” የውጭ ምንዛሪ “አቅርቦትን መጨመር” እንደሆነ አቶ ባህሩን የመሳሰሉ የባንክ እና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ይህ በቀጥታ በሀገሪቱ የወጪ ንግድ አቅም ላይ የሚወሰን ይሆናል።



ከገንዘብ ሚኒስቴር ወደ ብሔራዊ ባንክ ገዥነት ከተዘዋወሩአንድ ወር ገደማ የሆናቸው ዶክተር እዮብ መንግሥታቸው ከወጪ ንግድ ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ተስፋ እንዳለው ተናግረዋል። የባንክ ባለሙያው አቶ ባሕሩ ግን ነጋዴዎች ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበትን የአሠራር ሥርዓት ማቅለል እና የአገልግሎት ክፍያዎችን መቀነስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።



አርታዒ አዜብ ታደሰ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የዶላር ምንዛሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ሣምንት ብቻ ከአምስት ብር በላይ ጨመረ

የዶላር ምንዛሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ሣምንት ብቻ ከአምስት ብር በላይ ጨመረ

Eshete Bekele