መግለጫ፤ ዶቸ ቬለ ኢትዮጵያ የሚገኙ ዘጋቢዎቹ ከሥራ መታገዳቸዉን ይቃወማል
Description
መግለጫ፤ ዶቸ ቬለ ኢትዮጵያ የሚገኙ ዘጋቢዎቹ ከሥራ መታገዳቸዉን ይቃወማል
ዶቸ ቬለ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን (EMA) ሀገር ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ዘጋቢዎቹ ከሥራ መታገዳቸዉን ይቃወማል። የመገናኛ ብዙኀን ተቆጣጣሪዉ ባለሥልጣን ሐሙስ ዕለት DW -ለዶቼ ቬለ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል በደብዳቤ እንዳሳወቀዉ፤ በኢትዮጵያ የዶቼ ቬለ ዘጋቢዎች የጋዜጠኝነት ሥራ «ለጊዜው» አግዷል።
የDW ዋና ዳይሬክተር ባርባራ ማሲንግ «ከኢትዮጵያ በሚሠራዉ ዘገባ ላይ የተጣለው እገዳ በጣም ያሳስበናል» ብለዋል። «የአሜሪካ ድምፅ የቋንቋ አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ ከዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን ዶቸ ቬለ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ተደራሽነት ያለዉ የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም ያቀርባል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ነፃ እና ገለልተኛ መረጃን ለማግኘት እኛ ላይ መታመናቸዉን ቀጥለዋል። የሥራ ባልደረቦቻችን ያለምንም ገደብ ሥራቸውን አሁኑኑ ይቀጥሉ ብለን ሙሉ በሙሉ እንጠብቃለን።»
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን (EMA) የላከዉ ደብዳቤ የ DW ዘገባ በተናጠል የተለየ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ክስ አልያዘም። ይልቁንም የተላከዉ ደብዳቤ DW የጥላቻ ንግግር እና የሐሰት መረጃ ስርጭትን የሚያግደውን የመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን ደንቦችን እና አዋጆችን ጥሷል ሲል በሰፊው ይከሳል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከላይ የተገለጹትን የመገናኛ ብዙኀን አዋጆች ጥሰዋል ስለተባሉት ዘገባዎች ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ እና እገዳው በአስቸኳይ እንዲነሳ ዶቼ ቬለ DW ይጠይቃል። በኢትዮጵያ የሚገኙት ዘጠኙ የዶቼ ቬለ DW ሠራተኞች ቀጣይ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስ የጋዜጠኝነት ሥራቸውን አቁመዋል። የአማርኛዉ ቋንቋ ስርጭት በቦን እና በሌሎች የዓለም ክፍል በሚገኙት የዶቼ ቬለ ሠራተኞች ዝግጅቱ ይቀጥላል። የዶቼ ቬለ DW የሬዲዮና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ዕድሜያቸው ከ 14 ዓመት በላይ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 10 በመቶ ለሚሆነው ይደርሳል።
የዶቼ ቬለ DW ጋዜጠኞች እገዳ በሰኔ 2026 ሊካሄድ ከታቀደው ምርጫ በፊት በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ በሆነችዉ ሀገር የመገናኛ ብዙሃን ይዞታ የበለጠ እያሽቆለቆለ መሆኑን ያሳያል። በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓ.ም. በትግራይ ክልል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነፃነት በእጅጉ ቀንሷል። ባለፉት ወራት እንደ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ CPJ እና ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ያሉ ነጻ ተቋማት በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ደጋግመው ጠይቀዋል። ሀገሪቷ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከፍተኛ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ከሚደረግባቸው የሚመገናኛ ብዙኀን ገበያዎች አንዷ ስትሆን በአሁኑ ወቅት ከ 180 አገሮች መካከል 145 ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ድርጅት ይፋ አድርጓል።























