DiscoverDW | Amharic - Newsኢትዮጵያ፤ ሁለት የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች ለዘለቄታው ታግደዋል
ኢትዮጵያ፤ ሁለት የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች ለዘለቄታው ታግደዋል

ኢትዮጵያ፤ ሁለት የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች ለዘለቄታው ታግደዋል

Update: 2025-12-12
Share

Description

ሁለቱ የዶይቸ ቬሌ ወኪሎች ትግራይ እና አማራ ክልሎች ውስጥ ሲዘግቡ ነበር። ዶይቸ ቬለ ሕጋዊ ርምጃዎች ላይ እያጤነ ነው።



የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ቀደም ሲል ሁሉንም ዘጠኝ የዶቼ ቬለ ዘጋቢዎች ጥቅምት 13 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በጊዜያዊነት አገደ። ሰባቱ በዚህ ሳምንት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተፈቅዶላቸዋል። ባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ በላከዉ ደብዳቤ ቦን የሚገኙ የDW የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ሠራተኞች ላይም ክስ ሰንዝሯል።



የዶይቸ ቬሌ ዋና አዘጋጅ ማኑዌላ ካስፐር ክላሪጅ፦ «ሁለቱ ዘጋቢዎቻችን ያለምንም ተጨባጭ ማብራሪያ ሥራቸውን እንዲያቆሙ መደረጉ ተቀባይነት የለውም» ብለዋል። «በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከመላ ሀገሪቱ በሚገባ ጥናት የተደረገባቸዉን ዘገቦችን ስለምናቀርብላቸው በአማርኛ ቋንቋ መርኃ-ግብራችን ይተማመናሉ። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ተቆጣጣሪ በሠራተኞቻችን ላይ የቀረቡትን ጥቅል ውንጀላዎች አጥብቀን ውድቅ በማድረግ ከዘጋቢዎቻችን እና ከኤዲቶሪያል ቡድናችን ጎን ሙሉ በሙሉ እንቆማለን» ብለዋል።



የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ሰኞ ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ሁለቱን ጋዜጠኞች ያገደበትን ጉዳይ ሲያስረዳ፦ «ለኢትዮጵያ ሕግጋት እና ለሞያዊ ሥነ-ምግባር አለመገዛት ቀጥሏል» በማለት ጥቅል ክስ አጣቅሷል። ይሁንና ከዶይቸ ቬሌ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቢቀርቡም ተቆጣጣሪው ጋዜጠኞቹ ስላቀረቡት ዘገባ ይሄ ነዉ የተባሉ ቅሬታዎችን አልገለጸም። ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል ተቆጣጣሪው ሁሉም የዶይቼ ቬለ ዘጋቢዎች ላይ የጣለውን ጊዜያዊ እገዳ ሲያስረዳ የትኛውንም ዓይነት የተለየ የዶይቼ ቬለ ዘገባዎችን ለይቶ ሳይጠቅስ ግልጽ ባልሆነ መልኩ ሁለት የመገናኛ ብዙኀን ደንቦች ተጥሰዋል ሲል ጠቅሷል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ደብዳቤ ቦን የሚገኘውን የአማርኛ ኤዲቶሪያል ቡድንንም ያለምንም ማስረጃ «አሳሳች መረጃ» በማተም እና «በአደገኛ ሁኔታ የተቀነበቡ ትረካዎች እና ጽሑፎች» ሲል በመጥቀስ «አመፅ ሊያነሳሱ ወይም ብሔራዊ ሰላምና ደኅንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ» ሲል ከስሷል። ዶይቼ ቬለ የቀረቡት የትኞቹም ክሶች ትክክል አይደሉም በሚለው ይጸናል፤ ብሎም ባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ ማናቸውንም ዓይነት ተጨባጭ ማሳያዎች የሚያቀርብ ከሆነ እንደሚገመግም ገልጿል።



ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይ ግጭት በጎርጎሪዮሱ 2020 ከተቀሰቀሰ በኋላ የፕሬስ ነፃነት እያሽቆለቆለ መጥቷል። የዶይቼ ቬለ እገዳ የመጣዉ በኢትዮጵያ ሰኔ 2018 ዓ.ም. ሊደረግ ከታቀደው ምርጫ በፊት በገለልተኛ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚደርሰው ጫና እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነዉ። ባለፉት ወራቶች የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (CPJ)፤ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF)ን ጨምሮ የመገናኛ ብዙኀን ቡድኖች በኢትዮጵያ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፤ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢዎችን እገዳም ተቃውመዋል።



ዶይቼቬለ (DW) የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የትኛውም ዓለም አቀፍ የስርጭት አገልግሎቶች በበለጠ ስፋት አገልግሎት የሚሰጥ እና 10 በመቶ የሚሆኑ ዕድሜያቸው 14 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሚደርስ ነዉ።

Comments 
loading
In Channel
loading
00:00
00:00
1.0x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ኢትዮጵያ፤ ሁለት የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች ለዘለቄታው ታግደዋል

ኢትዮጵያ፤ ሁለት የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች ለዘለቄታው ታግደዋል