DiscoverDW | Amharic - Newsየአልጀርስ ሥምምነት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለበረታው ውጥረት መፍትሔ ያመጣል?
የአልጀርስ ሥምምነት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለበረታው ውጥረት መፍትሔ ያመጣል?

የአልጀርስ ሥምምነት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለበረታው ውጥረት መፍትሔ ያመጣል?

Update: 2025-12-12
Share

Description

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ለዘላቂ ሰላም” እና አንዳቸው የሌላውን “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት” ለማክበር ለተፈራረሙት የአልጀርስ ሥምምነት እንደገና ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥሪ አቅርበዋል።



በሁለቱ ሀገራት መካከል “አዲስ ውጥረት” በነገሰበት በዚህ ወቅት ጉቴሬዝ “መልካም ጉርብትና ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር” እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።



ሥምምነቱ በአልጄሪያ ዋና ከተማ የተፈረመበትን 25ኛ ዓመት በማስመልከት በቃል አቀባያቸው ስቴፈን ዱጃሪች በኩል ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ለሁሉም የሚጠቅም የልማት ትብብርን ለማጠናከር ከቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር መስራታቸውን እንዲቀጥሉ” አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥሪ አቅርበዋል።



የዋና ጸሀፊው ጥሪ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለበረታው ውጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ “እውቅና” የሰጠ መሆኑን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ አብዱራሕማን ሰዒድ ይናገራሉ። አቶ አብዱረሕማን እንደሚሉት በሁለቱ ሀገራት መካከል የበረታውን ውጥረት “በአልጀርስ ሥምምነት መሠረት በሰላም እንዲፈቱት” ጉቴሬዝ ያሳሰቡበት በመሆኑ ከፍ ያለ ትርጉም አለው።



ለሁለት ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተካሔደውን ጦርነት ያቆመው ሥምምነት ዋና ይዘት በድንበር አካባቢ የሚገኙ ግዛቶች ላይ የነበረውን ይገባኛል ውዝግቦችን መፍታት ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሥምምነቱን የተፈራረሙት ታኅሳስ 3 ቀን 1993 ነበር።



የሰላም ሥምምነቱ “በቅኝ ግዛት ሥምምነቶች እና ዓለም አቀፍ ሕግ ላይ በመመሥረት ድንበር የመወሰን እና የማካለል ሥልጣን” የተሰጠው አምስት አባላት ያሉት ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁሞ ነበር።



ለጦርነቱ መነሻ የሆነው ባድመ እና የኢሮብ አካባቢ በኮሚሽኑ ለኤርትራ መወሰኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይቀበል በመቅረቱ የድንበር ማካለል ሥራው ተግባራዊ አልሆነም። ሥምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ለ17 ገደማ ዓመታት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበት ሆኖ ቆይቷል።



የኢትዮጵያ መንግሥት እና የቀድሞው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥምምነቱን እና የድንበር ማካለል ውሳኔውን “ሙሉ በሙሉ” መቀበላቸው ይፋ የተደረገው በግንቦት 2010 ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሐምሌ 2 ቀን 2010 የአስመራ መግለጫን ሲፈራረሙ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዓመታት የዘለቀው ፍጥጫ አብቅቶ “አዲስ የሰላም እና የወዳጅነት ዘመን” መከፈቱን አወጁ።





በትግራይ ጦርነት የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ቢዋጋም ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ግጭት የማቆም ሥምምነት ሲፈራረሙ ወዳጅነታቸው ተፋረሰ። ከጦርነቱ በኋላ የተቀየረው የኃይል አሰላለፍ በኢሳያስ እና ዐቢይ መንግሥታት መካከል የተፈጠረውን መቃቃር አክርሮታል።



ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ ባለፈው ጥቅምት ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፉት ደብዳቤ “ህወሓት እና የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለማወጅ እየተዘጋጁ ነው” ሲሉ ከሰው ነበር። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ወደብ ማግኘት አለባት የሚል አቋም የሚራምደው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት አሰብ ላይ የሚያነሳው የባለቤትነት ጥያቄ ውጥረቱን አባብሶታል።



ለኢትዮጵያ ባሕር በር “የኅልውና ጉዳይ ነው” የሚል አቋም ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይናን ጨምሮ መፍትሔ ለማፈላለግ ለተለያዩ ሀገራት “ሸምግሉን” የሚል ጥያቄ እንዳቀረቡ ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረው ነበር።



የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተመሰረተበት 118ኛ ዓመት በቢሾፍቱ ሲከበር “30 ዓመት ተኝተናል፤ አሁን ነቅተናል። ጥያቄያችንን እንቀጥላለን” ሲሉ የተደመጡት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በበኩላቸው “ሰላምም፣ ልማትም ባሕር በርም እናሳካለን” ብለው ነበር።



የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ በኩል በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ኢትዮጵያ የምታደርገው ግፊት “አደገኛ” እንደሆነ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል። ጉዳዩን የኢትዮጵያ “የግዛት ማስፋፋት” ፍላጎት አድርጎ የተቸው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ለሀገሪቱ “ሉዓላዊነት ሥጋት” እንደሆነ ባለፈው ወር ገልጾ ነበር።



አቶ አብዱረሕማን ግን ከኢትዮጵያ በኩል የሚነሳውን የይገባኛል ጥያቄ የአልጀርስ ሥምምነት “ፈትቶታል” የሚል አቋም አላቸው። “የአልጀርስ ሥምምነት ሁለቱ መንግሥታት የተስማሙበት የመጨረሻ እና አስገዳጅ ስለሆነ አሁን ላለው በተለይ በኢትዮጵያ በኩል ለሚነሳው የይገባኛል ጥያቄዎች ይመልሰዋል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።



መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው ቻታም ሐውስ ሁለት ባልደረቦች በጋራ በጻፉት ሐተታ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሊቀሰቀስ የሚችልን ጦርነት ማቆም አስቸኳይ ትኩረት እንደሚሻ ጽፈዋል። “ውጥረቶችን ለማርገብ እና ሰላማዊ መፍትሔዎች” ለማፈላለግ የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዶክተር አቤል አባተ እና አሕመድ ሱሌይማን ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማሸማገል ጥያቄ እንዳቀረበች ምንጮች እንደገለጹ አትተዋል።



የቀጠናው ውጥረት በአዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ደሕንነት ፖሊሲ ጭምር ትኩረት ያገኘ ነው። ባለፈው ሣምንት ይፋ የሆነው የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የብሔራዊ ጸጥታ ስትራቴጂ አሜሪካ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እና በሶማሊያ መካከል “አዳዲስ ግጭቶች እንዳይቀሰቀሱ” ማድረግ ላይ እንደምታተኩር ያሳያል።



አርታዒ ታምራት ዲንሳ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የአልጀርስ ሥምምነት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለበረታው ውጥረት መፍትሔ ያመጣል?

የአልጀርስ ሥምምነት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለበረታው ውጥረት መፍትሔ ያመጣል?

Eshete Bekele