ጀርመን በሰሜን ኢትዮጵያ ለሰላም ግንባታ፣ ለማረጋጋት እና ለግጭት መከላከል ጥረቶች የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
Description
ጀርመን ጦርነት ጉዳት ባደረሰባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች ለሰላም ግንባታ፣ ለማረጋጋት እና ለግጭት መከላከል ጥረቶች የሚውል ተጨማሪ የ5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ። ይህ ድጋፍ ጀርመን በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም እንዲፀና የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ ግብር ለሚያከናውነው ሥራ የለገሰችውን የገንዘብ መጠን ከ22 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ያደረገ ነው። በሌላ በኩል ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው በኩል ሰሞኑን የሦስት ዓመታት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በዚህም ጀርመን ለኢትዮጵያ 206 ሚሊዮን ዩሮ አዲስ የድጋፍ ቃል ኪዳን መግባቷ ተነግሯል።
የጀርመን ድጋፍ በጎ አድራጎት ብቻ ሳይሆን "ብልህ ልማት ነው"
ጀርመን የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ ግብር (UNDP) "የሰሜን" የሚባለውና በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ብርቱ ውድመት ላደረሰ ጦርነት የሰላም መልሶ ግንባታ ሥራ ለሚያከናውነው ዘርፍ ብዙ የሰላም ድጋፍ ተቋም (PSF) ትናንት ተጨማሪ የ5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል። ዩኤንዲፒን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የተቋሙ የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ጋይዲ ዶ፤ ጀርመን ያደረገው ድጋፍ የተቀናጀ እና ቀድሞ የሚተነበይ ድጋፍ ማኅበረሰቦች ከቀውስ ዐውድ ወደ ሰላም እንዲመለሱ መተማመኛ እንደሚሰጥ ግልጽ መልዕክት ያለው ነው ብለዋል።
"ይህ ድጋፍ በጎ አድራጎት ብቻ አይደለም። ብልህ ልማት ነው። ወቅታዊና ተለዋዋጭ ሀብቶችን ወደ አካባቢያዊ ሥርዓቶች በማዘዋወር፣ ተቋሙ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ፣ የአካባቢ መስተዳደሮችን እንደገና ለማንቀሳቀስ እና በሰሜን ኢትዮጵያ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የማህበረሰብ እምነትን እንደገና ለመገንባት ይረዳል።"
ድጋፉ የቀድሞ ተዋጊዎች "ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ" አግዟል
ጀርመን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ክፉኛ የጎዳቸው ሦስት ክልሎች ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርሐ ግብር ለሚያከናውነው የሰላም ግንባት፣ የማረጋጋት እና ግጭት የመከላከል ጥረት ድጋፍ በማድረጉ ሀገራቸው ደስተኛ መሆኑን አዲስ አበባ ያለውን የጀርመን ኤምባሲ እየመሩ ያሉት ዶ/ር ፈርዲናንድ ቮን ዋይሄ ተናግረዋል። ሰሜን ኢትዮጵያን በአካል ተጉዘው መመልከታቸውን የጠቀሱት ፈርዲናንድ፤ ድጋፉ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ማገዙን በጀርመን ኤምባሲ ቅጥር ግቢ በተደረገው የፊርማ ሥና ሥርዓት ላይ ጠቅሰዋል።
"ሰላም ያለ ውጊያ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ሰላም በልብ ውስጥ እንዲሆን ለማድረግ አዎንታዊ ሰላም ያስፈልጋል። ይህ ምን ማለት ነው? ሕይወት ወደ ትክክለኛው መንገድ እየተመለሰች ነው፣ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ይችላሉ፣ ሰዎች ወደ ገበያ መሄድ ይችላሉ፣ የፍርድ ቤት ሥርዓት ይመለሳል፣ የፖሊስ ጣቢያዎች እየሰሩ ነው፣ የኑሮ ሁኔታ እንደገና ሊቀጥል ይችላል ማለት ነው። ስለዚህ በዚህ መርሐ ግብር በጣም ደስተኞች ነን። ለዚህም ነው ይህንን ድጋፍ እና ትብብር ለመቀጠል በሙሉ ልብ የወሰንነው።"
በማገገሚያእናበማረጋጋትላይያተኮረሥራንእናስቀጥላለን
የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ ግብር ልማት ላይ የሚያተኩር ተቋም ነው ያሉት የተቋሙ የኢትዮጵያ ተወካይ፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን ጥጥቅ አስፈትቶ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ በዚህ ዓመት ብቻ 60 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን ገልፀዋል። "በሰሜን በኩል፣ አሁን ፈሰስ የምናደርገው በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦች ሕይወታቸው እንዲያገግም ለመርዳት በማገገሚያ እና በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ነው።"
የሀገርውስጥሰላምበዋናነትየመንግሥታትኃላፊነትነው
የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ማገዝ እንጂ የውስጥ ሰላምን ማፅናት የሀገራት መሠረታዊ ኃላፊነት መሆኑን ግን ዶ/ር ፈርዲናንድ ገልፀዋል። "በአገር ውስጥ ሰላም ለመፍጠር ከውጭ መደገፍ በጣም ከባድ ነው። መሞከር እንችላለን፣ የእርዳታ እጅ መስጠት እንችላለን፣ ከአጋሮቻችን እና ከወዳጆቻችን ጋር መወያየት ያንን ማድረግ እንችላለን። ነገር ግን በመጨረሻ ለኅብረተሰቡ ሰላም ማምጣት፣ ለሕዝብ ሰላም መስፈን፣ የአገር ውስጥ ግጭት ሲሆን ከአገር ውስጥ መምጣት ያለበት ነገር ነው።"
ጀርመንለኢትዮጵያ 206 ሚሊዮንዩሮአዲስድጋፍአድርጓል
በሌላ በኩል የጀርመን ፌዴራላዊ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር በዚሁ ሳምንት ኢትዮጵያ ጎብኝተዋል። በሚኒስትሯ የተመራው ልዑክ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር የሦስት ዓመታት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን፣ በዚህም ጀርመን ለኢትዮጵያ 206 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 36.2 ቢሊዮን ብር አዲስ የድጋፍ ቃል መግባቱን የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። ጀርመን እና ኢትዮጵያ የ60 ዓመታት የልማት ትብብር እንዲሁም የ120 ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ























