DiscoverDW | Amharic - Newsበታንዛኒያ ከምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ
በታንዛኒያ ከምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ

በታንዛኒያ ከምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ

Update: 2025-11-01
Share

Description

በታንዛኒያ ባለፈው ረቡዕ ከተካሔደው ምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ከ700 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ተቃዋሚው ቻዴማ ፓርቲ አስታውቋል። የፓርቲው ሊቀ-መንበር ጆን ኪቶካ በዳር ኤ ሰላም 350 ገደማ፣ ምዋንዛ በተባለችው ከተማ ከ200 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ትላንት አርብ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።



በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተገደሉ ሰዎችን ጨምሮ የሟቾች ቁጥር ከ700 በላይ እንደሚሆን የተናገሩት ጆን ኪቶካ “ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል” የሚል ሥጋት አላቸው።



የታንዛኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሕሙድ ታቢት ኮምቦ መንግሥታቸው በተቃዋሚዎች ላይ “ያልተመጣጠነ ኃይል አልተጠቀመም” በማለት አስተባብለዋል። ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ የሚጠቁም ቁጥር በመንግሥት እጅ አለመኖሩን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአልጀዚራ ገልጸዋል። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በሦስት ቀናት ብቻ እስከ 100 ሰዎች መገደላቸውን የሚጠቁም ሪፖርት እንደተቀበለ አስታውቋል።



“አጋሮቻችን በአውራ ጎዳዎች አስከሬኖች መመልከታቸውን ነግረውናል” የሚሉት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የታንዛኒያ እና የዩጋንዳ ጉዳዮች ተመራማሪ ሮላንድ ኢቦሌ “መንግሥት ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ በግልጽ ለማሳወቅ አልፈለገም። የደረሰውን ጉዳት መጠንም ለማሳነስ እየሞከሩ ነው” ሲሉ ተችተዋል።



“አጋሮቻችን የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ መቶ መቃረቡን ነግረውናል። ትክክለኛውን ቁጥር እስክናረጋግጥ ድረስ ይኸ ነው ማለት አንችልም” ያሉት ሮላንድ ኢቦሌ ውጤቱ ይፋ ሲሆን ውጥረቱ የበለጠ ሊባባስ እንደሚችል ተናግረዋል።



ባለፈው ረቡዕ በተካሔደው ምርጫ የፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሉሑ ዋንኛ ተፎካካሪዎች አልተሳተፉም። የታንዛኒያ ትልቅ ከተማ በሆነችው ዳር ኤ ሰላም ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ እና የምክር ቤት ምርጫ ድምጽ በተሰጠበት ዕለት ነው።



አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች የሳሚያ ሱሉሑን የምረጡኝ ዘመቻ ፖስተሮች በመቅደድ፣ በፖሊሶች እና በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ተቃውሟቸውን እንዳሰሙ ሬውተርስ እና የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግበዋል። መንግሥት የሰዓት ዕላፊ ገደብ በመጣል እና የኢንተርኔት አገልግሎት በመዝጋት ምላሽ ሰጥቷል።



በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ከምርጫው በኋላ የተቀሰቀሰው ኹከት እና መንግሥት የወሰደው እርምጃ እጅግ እንዳሳሰበው ትላንት አርብ አስታውቋል። የቢሮው ቃል አቀባይ ሳይፍ ማጋንጎ የጸጥታ አስከባሪዎች በዳር ኤ ሰላም፣ ሺንያጋ እና ሞሮጎሮ ተቃዋሚዎችን ለመበተን በተኮሷቸው ጥይቶች እና አስለቃሽ ጭስ ቢያንስ አስር ሰዎች መገደላቸውን የሚጠቁም ተዓማኒ መረጃ ለመሥሪያ ቤታቸው እንደደረሰ ተናግረዋል።



ሳይፍ ማጋንጎ “የጸጥታ አስከባሪዎች ገዳይ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ አላስፈላጊ እና ያልተመጣጠነ ኃይል በተቃዋሚዎች ላይ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ውጥረቱን ለማርገብ ሁሉንም ጥረት እንዲያደርጉ እናሳስባለን። ተቃዋሚዎች በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ ማድረግ መቻል አለባቸው” የሚል መልዕክት ትላንት አርብ አስተላልፈዋል።



የምርጫው ውጤት ዛሬ ቅዳሜ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የታንዛኒያ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሑሉ እየመሩ እንደሚገኙ አሳይቶ ነበር። ሳሚያ ካሸነፉ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ሥልጣን ላይ ይቆያሉ።



ይሁንና በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን የምርጫው ተቀባይነት ማጣት ሌላ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል። የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አባላት “እነዚህ ምርጫዎች ነጻ እና ፍትኃዊ ተብለው ሊቆጠሩ አይችሉም” በማለት አውግዘዋል።



“ዋና ዋና ተቃዋሚዎች ታፍነው፣ የመሰብሰብ፣ እና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ተከልክለው፤ ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን ማስፈራሪያ እና ሳንሱር እየገጠማቸው የሚካሔድ ምርጫ ተዓማኒ ሊሆን አይችልም” በማለት የምክር ቤቱ አባላት ነቅፈዋል።



በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ቃል አቀባይ ሳይፍ ማጋንጎ የሱሉሑ መንግሥት የምርጫ ሒደቱ የበለጠ ተቀባይነት እንዳያጣ የዜጎቹን መብት ማክበር እንደሚኖርበት አሳስበዋል።



“ባለሥልጣናቱ ታንዛኒያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የተጣለባትን ግዴታ በሙሉ እንዲወጡ አጥብቀን እንመክራለን” ያሉት ሳይፍ ማጋንጎ “በአፋጣኝ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀምር፣ የዜጎች ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት እና በሰላም የመሰብሰብ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ ማመቻቸት አለባቸው። የመገናኛ ዘዴዎችን መገደብ በምርጫ ሒደቱ ላይ ሕዝብ ያለው እምነት የበለጠ እንዲሸረሸር ያደርጋል” ሲሉ አሳስበዋል።

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

በታንዛኒያ ከምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ

በታንዛኒያ ከምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ

Eshete Bekele