የኦሮሞ ነጻነት ግንባር  ለምርጫው አስቻይ ኹኔታ እንዲኖር  ጠየቀ
Description
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ በድርጅቱ ሥራ ላይ ብርቱ ተግዳሮት እንደደቀነ አስታወቀ። ግንባሩ ይህን ያለው በድርጅቱ ወቅታዊ እና መጻኢ ጊዜ ላይ ከአባላቱ ጋር ተወያይቶ ባወጣው የአቋም መግለጫ ነው። 
ኦነግ  ለቀጣዩ ምርጫ የሚያደርገውን ዝግጅት ጨምሮ ግንባሩ ያለበትን ወቅታዊ ኹኔታ መገምገሙን  የግንባሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። መንግስት በክልሉ ሰላም እንደረጋገጥ እና ለቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ አስቻይ ኹኔታዎች እንዲኖሩም ኃላፊው ጠይቀዋል። 
የኦሮሞ ህዝብ በክልሉ ውስጥም ሆነ ክልሉን ከአማራ እና ሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑ አካባቢዎችየተፈጸሙ ግድያዎችን እና ህዝቡን ለእንግልት የዳረጉ ጉዳዮችን እናወግዛለን ያለው የኦነግ መግለጫ የግንባሩ ኹነኛ ሰው የነበሩትን የአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ጨምሮ በክልሉ የተፈጸሙ ጥቃቶች በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ የክልሉ ሰላም መረጋገጥ የሚያስችል እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳ በመጥበቡ ድርጅታዊ ስራዬን ለመስራት ብርቱ ተግዳሮት ገጥሞኛል ያለው ኦነግ ከሕዝቡ ጋር ተገናኝቼ ለመምከር የሚያስችል ኹኔታ ውስጥም አይደለሁም ብሏል። 
የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ኦነግ ወቅታዊ ኹኔታውን የገመገመበትን አንድምታ በተመለከተ በተለይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት የግንባሩ ጽ/ቤቶች አለመከፈታቸው እና የአባላት እስራት እና እንግልት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
« በስብሰባው ያለንበት ብለን ያስቀመጥነው ፤ እስራቶች ፣ ግድያዎች እንደዚሁም ደግሞ የድርጅቱ አባላት በተዋረድ ሲደርስባቸው የነበረ ፣ የድርጅቱ ቢሮዎች መዘጋት ፤ እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩ እንደ አንድ አንኳር ጉዳይ ያነሳንበት እንዲሁም የኦሮሞ ሰላም እጦት ፣ በየቦታዎ ሲገደል ፣ እንዲሁም ሲፈናቀል ፣ ለፖለቲካዊ ረሃብ ሲደረግበት ስለነበር ይህ ሁሉ ከአባላት ሲነሳ ነበር» 
የግንባሩ አመራር በህዝቡ ውስጥ መንቀሳቀስ እንዳልቻለ የተናገሩት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አሁንም ድረስ አንድ መቶ ሃያ ገደማ የግንባሩ ጽ/ቤቶች እንዳልተከፈቱ ነው የገለጹት ። ቢሮዎቹ ተከፍተው ስራ እንዲጀምሩ አሁንም ጥያቄ ማቅረብ መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
« የድርጅቱ አመራር በህዝቡ መሃል እየሄደ ድርጅታዊ ስራ እንዲሁም የትግሉን ዓላማ እና አካሄድ ህዝቡን ማወያየት ባልቻልንበት አንድ ቢሮ በቅርብ ወር ውስጥ የተከፈተው ታሪካዊ የድርጅታችን ቢሮ ውስጥ ነን። ያቺን ይዘን ነው የተሻለ ምህዳሩ እንዲከፈትልን እና በተዋረድ ያሉ ከ120 በላይ ቢሮዎቻችን ተመልሰው እንዲከፈቱልን ስንጠይቅ የነበረው አሁንም እየጠየቅን ያለነው »
በቀጣዩ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ፓርቲያቸው ዝግጁ መሆኑን የገለጡት አቶ ለሚ ነገር ግን በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ያለውን ችግር« ስናሳውቅ ቆይተናል » ይላሉ።
«ሁሌ ዝግጁ ነን ፤ ዝግጅ ነን የምንለው ግን ፤ እነዚህ ተግዳሮቶች አሁንም እንቅፋት ናቸው። እኛ ብቻ አይደለንም። የኛ ጎልቶ ቢታይም ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተዘጋ ምህዳር ውስጥ ነው  እየተንቀሳቀሱ ያሉት። በጋራ ምክር ቤቱም ሆነ በተዋረድ ስናነሳ እንደነበረው ሁሉ እኛም ችግር ውስጥ ነው ያለነው። »
ኦነግ ባቀረበው የአመራሩ መንቀሳቀስ አለመቻል ፣ የበርካታ ቢሮዎቹ ያለመከፈት እና ለምርጫው ገጥሞኛል ያለውን ተግዳሮት በተመለከተ  መልስ እንዲሰጡበት ለብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ የእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ልናገኛቸው አልቻልንም ። አቶ ዮሴፍ መርጉ የተባሉ የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ የሆኑ ሰው ጥያቄዎቻችንን በዋትስ አፕ የመልዕክት መላኪያ እንድንልካቸው ከነገሩን በኋላ መልዕክቱን ልከን ለምላሹ በተደጋጋሚ ብንደውልላቸውም ስልክ ሳያነሱልን ቀርተዋል።
በያዝነው የ2018 ዓመት አጠቃላይሀገራዊ ምርጫእንደሚደረግ ይጠበቃል። ይሕንኑ በተመለከተ ለህዝብ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የመንግስትን አቋም በንግግር ያቀረቡት ፕሬዚደንት ታዬ አጽቀ ስላሴ ምርጫው በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ተአማኒ እንዲሆን መንግስት በኃላፊነት እንደሚሰራ ተናግረው ነበር። 
«በያዝነው ዓመት በሃገራችን የሚካሄደው ሰባተኛው ሃገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ ፣ ሰላማዊ ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ተአማኒ ይሆን ዘንድ መንግስት በሃላፊነት ይሰራል።  » 
ኦነግ በኦሮሚያ ክልል አሁንም ድረስ መቋጫ አልተገኘለትም ባለውና « በህዝብ ላይ እየደረሰ ነው» ላለው «ግድያ እና እንግልት» የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን መልስ እንዲሰጥበት ለኃላፊው አቶ ኃይሉ አዱኛ ብእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ስልካቸው ሳይነሳ ቀርቷል። 
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት በጨፌ ኦሮሚያ በአራተኛው ዓመት ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በክልሉ ህዝብ ላይ እየደረሰ ነው  የተባለውን ለመከላከል የክልሉ መንግስት ጥብቅ ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል። 
«የክልላችን ህዝብ ለሰላም ትልቅ መሰዋዕትነት ከፍሏል። አሁንም እየከፈለ ይገኛል። በግራ እና በቀኝ በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚቃጡ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመከላከል ወሳን ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፤ አሁንም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ይህን በማድረግም የህዝባችንን ፍላጎት በማስከበር የምንቀጥል መሆኑንን ለተከበረው ምክር ቤት ማረጋገጥ እፈልጋለሁ »
 
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ
 























