ህወሐት ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ያቀረበው ጥሪ
Description
የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ የፕሪቶርያ ውል እንዲፈፀም ሓላፋነታቸውን እንዲወጡ ህወሓት ጠየቀ። ህወሓት የሰላም ስምምነቱ ባለመከበሩ ህዝባችን አደጋ ላይ ነው ብሏል።
ህወሓት ያሰራጨው እና ለዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ጥሪ የሚያቀርበው መግለጫ እንደሚያመለክተው፥ የፕሪቶርያ ስምምነት ባለመተግበሩ የትግራይ ህዝብ በተለይም ተፈናቃዮች ለከፋ ሁኔታ ተዳርገዋል ሲል ይዘረዝራል።  የኢትዮጵያ መንግስት የገባውን ውል አለማክበር ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው እየተንቀሳቀሰ ነውም ብሏል። ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ፣ የውሉ አደራዳሪ ሀገራት እና ተቋማት፣ በተለይም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የአፍሪካ ሕብረት ውሉ ባለመተግበሩ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ድብቅ እልቂት ይገንዘቡ ብሏል ህወሓት። 
ጥሪ ለዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ
የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት አፈፃፀም የሚገመግም የአፍሪካ ሕብረት ፓነል እንዲጠራ በተደጋጋሚ መጠየቁን ያወሳው ህወሓት፥ ለዚህ ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ እንዲሰጠውም ጥሪ አቅርቧል። ህወሓት የምሁራን መድረክ ብሎ ባዘጋጀው ስብሰባ የተናገሩት የፖርቲው ስራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር አብርሃም ተከስተ፥የፕሪቶርያ ውል እንዲፈረም ሚና የነበራቸው አካላት ውሉ እንዲፈፀም ጫና በመፍጠሩ ረገድ የሚጠበቅባቸውን አልተወጡም ብለዋል። ፍትሓዊ ያልሆነ ሁኔታ እየቀጠለ እንደሆነ ለዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ አባላት ስንገልፅላቸው ይረዱታል ያሉት ዶክተር አብርሃም ተኸስተ ይሁንና ይበልጥ ጫና ለመፍጠር እና ትኩረት ለማግኘት የውስጥ አንድነት ያስፈልጋል ሲሉ ተደምጠዋል።
«ዶክተር አብርሃም ተኸስተ "ፍትሓዊ ያልሆነው ሁኔታ ስንነግራቸው ይረዱታል። ስለዚህ መፍትሔው ታድያ ምንድነው ካልን የእኛ ጥንካሬ ነው የሚወስነው። ከውስጥ ስንጠነክር እነሱም ያነጋግሩናል፣ ሁኔታውን ለመረዳት ይመጣሉ፣ እናግዛለን ይላሉ። ለዚህ ነው የውስጥ አንድነት መፍጠር አለብን የምንለው፥ ትልቅ ትርጉም ስላለው" ብለዋል።
የአሰላለፍ ለውጥ
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው እና ከህወሓት የተለየው ቡድን በዲፕሎማሲው ይሁን ሌላ ዘርፍ ከኢትዮጵያ መንግስት በላይ ችግር እየፈጠረብን ነው ሲሉም ዶክተር አብረሃም አክለው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ትግራይ ላይ ያነጣጠረ የጦርነት ዛቻ ስለመቀጠሉ የተናገሩት ዶክተር አብርሃም ተከስተ ይህ አደጋ ለማስቀረት ዝግጅት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል። እንደ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባሉ ዶክተር አብርሃም ተከስተ አገላለፅ፥ ከዓመታት በፊት የነበረ የሐይል አሰላለፍ እና አሁን የተለያየ ነው የሚሉ ሲሆን፥ 'ወዳጅ ማብዛት ላይ ተጠምደን እየሰራን ነው' ሲሉም ተናግረዋል።
ዶክተር አብርሃም "የህልውና አደጋ አጋጥሞናል፤ ወዳጆች ማብዛት ይጠበቅብናል። በትግራይ ህልውና ዙርያ አብረውን ሊሰሩ ከሚችሉት ጋር መግባት መፍጠር አለብን። ከኤርትራ ጋር የተጀመረዉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አለ። መደገፍ ነው ያለብን። ከአማራ ጋር እንዲሁ መደረግ አለበት። የኢትዮጵያ መንግስት ከአማራ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳይኖር እያደረገ ነው። ግን የግድ ከአማራ ህዝብ ጋርም ግንኙነት ዝምድና ልናጠናክር መቻል አለብን" ብለዋል።
ጦርነት ያስቆመ የሰላም ስምምነት የተፈራረሙት የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የውሉ አፈፃፀም የሚገመግም መድረክ በ2016 ዓመተምህረት አጋማሽ አድርገው የነበረ ሲሆን፥ ከዛ በኃላ ይህንኑ መድረክ በህወሓት በተደጋጋሚ ቢጠራም እስካሁን አልተደረገም።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ























