የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች እግድ
Description
የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች እግድ
ለሥራ ማስኬጅያ ከመንግሥት የተሰጠውን 2.7 ሚሊዮን ብር ከታለመለት ዓላማ ውጪ ማዋሉ እና ከፍተኛ ገንዘብ ለፓርቲው አመራሮች እና ሌሎች አባላት የግል ጥቅም አውሏል የተባለው አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግበት ተጠየቀ።
በፖርቲው አመራሮች ተፈጽሟል የተባለው የወንጀል ተግባር ተጣርቶ እስከሚቀርብ ድረስ ፓርቲው እና አመራሮቹ እንዲታገዱ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድአስታውቋል። በቀረበበት ክስ ዙሪያ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ በጽሑፍ ማስገባታቸውን ለዶቼ ቬለ የገለፁት የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሲሳይ ደጉ "ገቢና ወጪያችን ግልጽ በሆነ በሒሳብ አያያዝ የመጣ ፓርቲ ነው" ሲል የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገዋል። የዚህ ዓመት የፓርቲው በጀት እንዳይለቀቅ "ሆን ተብሎ እንቅፋት በመፍጠር ፓርቲው ተራማጅ እንዳይሆን" ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው ያሉት ሊቀመንበሩ "ምርጫ ቦርድ ማገድ አይችልም" በማለት የቦርዱን እርምጃ ተቃውመዋል።
ምርጫ ቦርድ በፓርቲው ላይ ያቀረበው ዝርዝር መግለጫ
የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ ለተባለው የፖለቲካ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ፓርቲው ለ2015 ዓ. ም የተሰጠው 2.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ከእንቅስቃሴዎቹ ጋር የሚመጣጠን፣ የሒሳብ አሠራር ሥርዓት ያልዘረጋ ፣ የቼክ እና የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ሥርዓት የሌለው መሆኑን ጠቅሷል።
በቦርዱ የተደረገለትን የበጀት ድጋፍ ለታለመለት አላማ አላዋለም የተባለው ፓርቲው ባቀረበው የኦዲት ሪፓርት ለ2015 የተሰጠውን ገንዘብ በዓመቱ ያደረጋቸው የሂሳብ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ቢሆኑም ከእንቅስቃሴዎቹ ጋር የሚመጣጠን የሂሳብ አሰራር ሥርዓት እንዳልዘረጋም ተጠቅሷል።
ይህንን ተከትሎ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠያቂነት የፓርቲውን የሒሳብ እንቅስቃሴ ለመመርመር ወደ ፓርቲው የሄደው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት "ፓርቲው የበጀት ድጋፍ አጠቃቀምን በተመለከተ የግልጽነት ተጠያቂነት ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ የድጋፍ ወጪን ዘርዝሮ የማይዝ መሆኑ፣ ደጋፊ ሰነድ የሌላቸው እና በሚመለከተው የፓርቲው አመራር እውቅና ያላገኙ እና ያልፀደቁ ወጪዎች መገኘታቸውን" ብሎም በብድር እና በስልጠና ስም ገንዘብ ላልተገባ ዓላማ ወጪ መደረጉን አረጋግጧል ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅሷል። የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሲሳይ ደጉ የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለዋል።
ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የሚደለድለው ገንዘብ መዋል ያለበት ለምን ጉዳይ ነው ?
ፓርቲው የተሰጠውን ገንዘብ የፓርቲውን አላማ ለሕዝብ ለማስተዋወቅ፤ ዜጎች በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳዮች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማድረግ፤ የመራጩን ሕዝብ የፖለቲካ ግንዛቤና እውቀት እንዲዳብር ለማድረግ እና ለመሳሰሉት ተግባራት መዋል እያለበት ገንዘቡ ለግል ጥቅም ሲውል እንደነበር ከቀረበለት የኦዲት ግኝት መረዳቱን ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር፣ የለ አግባብ ወጪ የሆነው ያለው ገንዘብ የፍትሃብሔር ክስ እንዲመሰረት እና ገንዘቡ ለቦርዱ ተመላሽ እንዲደረግ እንዲሁም የፖርቲው አመራሮች ታግደው እንዲቆዩ ወስኗል።
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ሲሳይ ደጉ ከ 2 ወር በፊት መታሰራቸውን ፣ ከዚያ በኋላ ይህ የኦዲት ጉዳይ መምጣቱን እና አዝማሚያው የዚህ ዓመት የፓርቲው በጀት እንዳይለቀቅ "ሆን ተብሎ እንቅፋት በመፍጠር ፓርቲው ተራማጅ ፓርቲ እንዳይሆን" ለማድረግ የሚደረግ ጥረት መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር























