DiscoverDW | Amharic - Newsማሕደረ ዜና፣ ኤል ፋሸር-የሱዳን እልቂት አዲስ ምዕራፍ
ማሕደረ ዜና፣ ኤል ፋሸር-የሱዳን እልቂት አዲስ ምዕራፍ

ማሕደረ ዜና፣ ኤል ፋሸር-የሱዳን እልቂት አዲስ ምዕራፍ

Update: 2025-11-03
Share

Description

የሰሜን ሱዳንዋ ሥልታዊ፣ የንግድ ማዕከል፣ የዘመናይ ተቋማት እምብርት ኤል ፋሻር ወድማለች።ከ300 ሺሕ ሕዝብ መኖሪያነት፣ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ወደ «ሰዎች ቄራነት» ተለዉጣለች።የኤል ፋሻር ዉድመት፣ የነዋሪዎችዋ እልቂትና ሰቆቃ ታዛቢዎች እንዳሉት ሁለት ዓመት ከመንቅ ያስቆጠረዉ የሱዳን የርስበርስ ጦርነት ወደ ዘግናኝ ምዕራፍ የመሸጋገሩ አብነትም ሆኗል።የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ኤል ፋሻርን መቆጣጠሩ ያስከተለዉ ተጨማሪ ቀዉስና ስጋት መነሻ፣ የሱዳን የጥፋት ጉዞ ማጣቃሻ፣ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰ አፀፋ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።



ኤል ፋሸር ከአንፀባሪቂ ከተማነት ወደ ዕልቂት ማዕከልነት



በ18ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ኃይል፣ ብልሕነታቸዉ በዳርፉሮች ዘንድ ሥም፣ ዝና ያተረፈላቸዉ ሡልጣን አብዱል ረሕማን ኤል-ረሺድ ያቺን በአዋራማ በረሐ የተከበበች ሥፍራን እንደ አማራጭ ርዕሠ ከተማነት የሠፈሩባት፣ ፀሐፍት እንዳሉት በሶስት ምክንያት ነዉ።ነፈሻ ናት።ለእርሻ ትመቻለች።ከሁለቱም በላይ ለፖለቲካ ርምጃና ለጦር ኃይል ንቅናቄ ሥልታዊ ናት።ፋሸር (ተለዋጭ ርዕሠ ከተማ) አሏትም።



የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት እስከ ተጫረበት እስከ ሚያዚያ 2023 ድረስ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሌሎች የሰሜን ሱዳን ከተሞች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ በመኪና መንገድ የሚገናኙት በኤል ፋሸር በኩል ነዉ።ከሱዳን የወደብ ከተማ ወደ ሰሜን ሱዳን ወይም በተቃራኒዉ ሸቀጥ ይሁን የርዳታ ቁሳቁስ በመኪና የሚጓዘዉም በዚችዉ ከተማ በኩል ነበር።ከሰሜንና ከምዕራብ ሱዳን ከተሞች ሁሉ ዘመናይ የሕክምና ማዕከላት፣የገንዘብ ተቋማት፣ የንግድ ማዕከላት፣ ትልቅ ዩኒቨርስቲ የሚገኙት ኤል ፋሻር ነዉ።



ጦርነቱ እስከተጀመረበት ጊዜ ድረስ ከ300 ሺሕ በላይ ሕዝብ ይኖርባትም ነበር።የሱዳን መከላከያ ጦርና የሐገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ኃይላት ሚያዚያ 2023 ካርቱም ላይ የገጠሙት ዉጊያ ወደ ሰሜንና ምዕራብ ሱዳን ከተስፋፋ ወዲሕ ግን አቅሙ የፈቀደ ነዋሪ ወደ ሌላ አካባቢ ሸሽቷል።



ኤል ፋሸር የመከራ ማግሥት መከራ ማዕከል



የሰብአዊ ርዳታ አቀባዮችና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የፈጥኖ ደራሹ ጦር ከተማይቱን ለ500 ቀናት ከብቦ የርዳታ እሕል እንዳይገባ በመከልከሉ፣ መሸሽ ያልቻለዉ በሺሕ የሚቆጠር የከተማይቱ ነዋሪ በረሐብ፣ በኮሌራና በሌሎች በሽቶች አልቋል።ባለፈዉ መስከረም ከተማይቱን ለቅቀዉ የወጡ የሱዳን የመብት ተሟጋቾች እንዳሉት ኤል ፋሻር «ወደ ትልቅ ክፍት መቃብርነት» ተለዉጣለች።



የፈጥኖ ደራሹ ጦር ካንድ ሳምንት በፊት ኤል ፋሸርን ከተቆጣጠረ በኋላ የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያዎችን በከባድ መሳሪያ ይደበድብ ገባ።የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የፈጥኖ ደራሹ ጦር ባልደረቦችና ተባባሪዎቹ ሚሊሺያዎች ባደባባይ፣ አንዳዴ የቪዲዮ ካሜራ እየደቀኑ በሽተኛን ከሐኪም፣ ልጅ-ካዋቂ ሳይለዩ ሰላማዊ ሰዎችን ይረሽኑ ያዙም።ሴቶችን ይደፍራሉ።ግድያ፣ ጥቃት፣ግፉን የፈሩ 70 ሺሕ ያክል ነዋሪዎች ጠዊላ ወደተባለች አካባቢ ሸሽተዋል።ዛሕራ አሕመድ ኤል ፋሸር «ምንቀረኝ» ዓይነት ይሏሉ።



«የበኩር ልጄ ተገድሏል።በሽተኛ ባሌ ሞቷል።ሌላዉ ልጄ በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ቆስሏል።በመጨረሻ ለመሸሽ ወሰንኩ።ልቆይ ብልም ምግብ የለም።ገንዘብ ቢኖር እንኳ የሚሸጥ ምግብና መጠጥ የለም።ሌላዉ ቢቀር ለቁስለኞቹ ልጆች ለክረምቱ መከላከያ ብርድ ልብስ ይሰጡናል የሚል ተስፋ አለን።ልጄም ሕክምና አግኝቶ ይድናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»



ናጅዋ አደም ወጣት ናት።ሸሽታለች።እናቷ፣ወድሞችዋ፣ አክስቷ፣ አያቷ ያሉበትን ግን አታዉቅም።ዘመዶችዋን ለማጘኘት ትመኛለች።ጦርነቱ እንዲቆም ትፀልያለች።





«ጦርነቱ እንዲቆም እንመኛለን።እኔ ራሴ እናቴና ሶስት ወንድሞቼ ጠፍተዉብኛል።ያሉበትን አላዉቅም።ዛሬ ከከተማዉ ሥንወጣ ወዴት እንደ ሔዱ አጣኋቸዉ።ወደከተማዉ ይመለሱ ወደ ሌላ ሥፍራ ይሽሹ አላዉቅም።ተበታተንን።አላገኘኋቸዉም።እናቴ፣ ሶስት ወድሞቼ፣ አክስቴ፣ ሴት አያቴ አንዳቸዉም የሉም።»



የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም ሊዮ 14ኛም እንደነ ናዋጅ ሁሉ ኤል ፋሸር ዉስጥ ግፍ ለተዋለባቸዉ ሰዎች ይፀልያሉ።



«ዉድ ወድሞቼና እሕቶቼ፣ ከሱዳን በተለይም ከኤል ፋሻር፣ ብዙ ከተሰዉበት ከዳርፉር ግዛት የሚወጡ ዘገቦችን በታላቅ ሐዘን እየተከታተልኩ ነዉ።በሴቶችና በልጆች ላይ፣ መከላከያ በሌላቸዉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በመደዳ የሚፈፀመዉ የኃይል እርምጃና ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደረስ መከልከሉ ወትሮም ለበርካታ ወራት በተደረገዉ ግጭት የተሰቃየዉን ሕዝብ ተቀባይነት ለሌለዉ መከራ እየዳረገ ነዉ።»



የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የሱዳን የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ባለፈዉ አንድ ሳምንት ጠዊል ከደረሱ ተፈናቃዮች 700 ያክሉ ከወላጆቻቸዉ የተለዩ ወይም ዘመድ-ወላጆቻቸዉ የተገደሉባቸዉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ናቸዉ።



የዳርፉር ጦርነትና የኋላ መዘዙ



በ2003 ጀምሮ ለተከታታይዓመታት በሱዳን መንግሥት ጦርና በዳርፉር አማፂያን መካከል በተደረገዉ ጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠር የግዛቲቱ ሕዝብ አልቋል።ለዳርፉሩ ጦርነት መነሻ ናቸዉ ከሚባሉት ምክንያቶች ዋናዎቹ የብሪታንያና የግብፅ ቅኝ ገዢዎች የቀበሩት የልዩነት ፈንጂ-አንድ፣ የካርቱም ገዢዎች ለረጅም ዘመን የተከሉት የአረብ-የጥቁር ሱዳናዊ የበላይ-የበታችነት የአገዛዝ መርሕ-ሁለት፣ የኃያላን መንግሥታት ጥቅምና የሱዳንን የተፈጥሮ ሐብት ለመቆጣጠር የሚሹ የአካባቢዉ ኃይላት ጣልቃ ገብነት-ሶስት ናቸዉ።





ፈጥኖ ደራሽ ጦር፣ የጃንጃዊድ ግኝት



የፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አል በሽር መንግሥት የዳርፉር አማፂያንና ደጋፊዎቻቸዉን እንዲመቱለት ያደራጀዉ የጃንጃዊድ ሚሊሺያ ከጦርነቱ በኋላ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ RSF) በሚል ስያሜ በአዲስ ሥም ተደረጀ።



አል በሽር በለብለብ ሥልጠና በአዲስ መለያ (ዩኒፎርም)ና በጦር መሳሪያ ላጠናከሩት አዲስ ኃይል አዛዦች የጄኔራልነት ማዕረግ ሲለጥፉ፣ ቁጥራቸዉ ጥቂት ቢሆኑም የሱዳን የስለላና የወታደራዊ ባለሙያዎች የኋላ መዘዙን ገምተዉ አለቃቸዉን ሐሳባቸዉን እንዲቀይሩ ጠቁመዉ ነበር።የሱዳንን ፖለቲካ ለ30 ዓመት ያክል የዘወሩት አል በሽር ግን በጀመሩት ቀጠሉ።የሱዳን ጉዳይ አጥኚ ሻይና ሌዊስ እንደሚሉት ኋላ ፈ,ጥኖ ደራሽ በሚል አዲስ ሥም የተደራጀዉ ኃይል መጀመሪያዉኑ የተመሠ,ረተዉ ለጥፋት ነዉ።



«ሌሎች ኃይላት ከጀርባቸዉ እንዲህ ዓይነት (የጭካኔ) ዓላማ ያላቸዉ አይመስለኝም።RSF ግን ሁል ጊዜ ዘር የማጥፋት አላማ ያለዉ ኃይል ነዉ።መጀመሪያ በዑመር አል በሽር ሥርዓት ሲመሠረትም የ2003ቱን ዘር ማጥፋት እንዲፈፅም ነዉ።መሠረቱ አሁንም እንዳለ ነዉ።»



ዘመናዊዉን ትምሕርት ተከታትለዉ፣ ከመደኛ የጦር ትምሕርት ቤት ተመርቀዉ፣ በዉጊያና ልምድ ከክፍተኛዉ የጦር አዛዥነት ማዕረግ የደረሱት የሱዳን መደበኛ የጦር መኮንኖች የጠቅላይ አዛዣቸዉን እርምጃ ጠሉትም ወደዱት ተቀበሉት። ይሁንና ለእኒያ ባፍታ ከግመል አርቢ፣ ጋላቢ ወይም ነጋዴነት ወደ ጦር አዛዥነት ለተለወጡት አዳዲስ መኮንኖች ያላቸዉን ንቀት ቢደብቁ እንኳ እኩል ለማየት ይተናነቀቸዉ ነበር።



በ2018 የሱዳን ሕዝብ በአል በሽር አገዛዝ ላይ ላይ ሲያምፅ አመፁን ለማክሸፍ ቀድሞ የዘመተዉ የፈጥኖ ደራሽ ጦር ነበር።ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ) የሚያዙት ጦር የሚወስደዉን ርምጃ የካርቱም ምርጥ መኮንኖች አልጠሉትም።የአልበሽርን መንበር ለመቆጣጠር ግን የፈጥኖ ደራሹ ጦር እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል በግልፅ አዉቀዉት ነበር።



የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ፈጠኖ ደራሹ ጦር ባንድ በኩል የሕዝቡን አመፅ እንዲያዳክም፣ በሌላ በኩል ለአል በሽር የሚሰጠዉን ድጋፍ እንዲቀንስ የካርቱም ምርጥ መኮንኖች፣ እነ ሐምዲቲን በመሪነት ሥልጣን ጭምር ያባብሉ ገቡ።ተሳካ።ሚያዚያ 11፣ 2019 አልበሽር ከሥልጣን ተወገዱ።



ጄኔራል አሕመድ አዋድ ኢብን አሩፍ ላንድ ቀን ሥልጣን ከያዙ በኋላ እነ ሐምዲቲን በማግባባቱ ጥረት የተካፈሉት ጄኔራል አብዱልሐታሕ አል ቡርሐን የወታደራዊ ሁንታዊን የገዢነት ሥልጣን ተቆጣጠሩ።ጥቂት ቆይቶ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ምክትል ገዢ ሆኑ።



በ2019 «የጠላትሕ ጠላት» በሚል ፖለቲካዊ ሥልት የተወዳጁት ሁለቱ ጄኖራሎችና ተከታዮቻቸዉ ከፖለቲካዉ መመሰቃቀል፣ ከሥልጣን ሽሚያዉ ጋር የወትሮዉ መናናቅ፣ መታበይና የገጠር-ከተማ ተባለጥ ተጨምሮበት ተከፋፈሉ።ካርቱምን ያጋዩዋትም ገቡ።ሚያዚያ 2023።



የዉጪ ኃይላት አሰላለፍ



የሱዳን ጎረቤቶችና ወዳጆች ከሚባሉ መንግሥታት መካከል ጦርነቱን ለማብረድ ከጣሩት ይልቅ ያጋጋሙት ማየላቸዉ ዛሬም ድረስ ብዙ ተንታኞችን በተለይ ሱዳናዉያንን ግራ እንዳጋባ፣ እዳስተዛዘበም ነዉ።ዘገቦች እንደጠቆሙት ግብፅ፣ ኢራን፣ ቱርክና ሩሲያ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ጀኔራል አል ቡርሐን የሚመሩትን የሱዳን መከላከያ ጦርን ይደግፋሉ።



ከተባበሩት ኤምሬቶች እስከ ኬንያ፣ ከሊቢያ የጦር አበጋዝ እስከ ቻድ የሚገኙ መንግስታትና ኃይሎች በቀጥታ፣ ሌሎች በተዘዋዋሪ የፈጥኖ ደራሹን ጦር ይረዳሉ።የሱዳንን ሥልታዊ አቀማመጥ፣ በአፍሪቃና በአረቡ ዓለምን ያላትን ተፅዕኖ፣ የወርቅና የሌሎች ማዕድናት ሐብቷን ለመቆጣጠር የሚሹ የዉጪ መንግሥታት የተነከሩበት ጦርነት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ደፈነ።



የጦርነቱ ዉጤትና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ



በትንሽ ግምት ከ150 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ከ14 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተሰድዷል ወይም ተፈናቅሏል።51 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሱዳን ሕዝብ ከግማሽ የሚበልጠዉ ሰብአዊ ርዳታ ጠባቂ ነዉ።ርዳታዉም የለም።ዓለም ከአፍታ ዘገባ ባለፍ የዘነጋዉ ጦርነት በሁለት ዓመት ከመንፈቁ ኤል ፋሸር ላይ ዘግናኝ ዉጤቱ በድጋሚና በግልፅ ታየ።



ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የሚባለዉ ኃያሉ ዓለም የሱዳንን ጦርነት እንዲያስቆም፣ ተፋላሚዎችን እንዲቀጣና ለችግረኞች ርዳታ እንዲሰጥ የሰብአዊ ርዳታ አቀባዮች፣ የመብት ተሟጋቾችና ተንታኞች በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ቶም ፍልቸር ባለፈዉ ሐሙስ ደገሙት።ፍልቸር ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት እንደነገሩት የኤል ፋሻሩ ሰብአዊ ድቀት እንደሚደርስ በፊትም ይታወቅ ነበር።ከቁብ የቆጠረዉ የዓለም ኃይል ግን የለም።



«እዚሕ ያለ ማንኛዉም ሰዉ ይሕ እንደሚሆን አላዉቅም ነበር ማለት የሚችል አለ።የስቃይ ሰቆቃዉን ጮኸት እዚሕ አንሰማም።ሰቅጣጩ እርምጃ ግን ቀጥሏል።ሴቶችና ልጃገረዶች እየተደፈሩ፣ ሰዎች በማንአለብኝነት እየተከታተፉ፣ እየተገደሉ ነዉ።ትናንት ሳዑዲ አረቢያ እናቶች ሐኪም ቤት ዉስጥ ብቻ 500 ያክል ሕሙማንና አስታማሚዎቻቸዉ መገደላቸዉ ተዘግቧል።ይሕ በሕክምና ተቋማት ላይ ከሚፈፀሙ ጥቃቶች የቅርቡና ለጦርነቱ አስቀያሚ ገፅታዎች አንዱ ምሳሌ ነዉ።»



ፈጥኖ ደራሹ ጦር ኤል ፋሸርዉስጥ በሶስት ቀናት ዉስጥ ብቻ ከ1400 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መግደሉ ተዘግቧል።በርካታ ሴቶችና ልጃገረዶች ተደፍረዋል።ኤል ፋሸር ዉስጥ የተፈፀመዉን ጥቃት፣ ግድያና ግፍ የተለያዩ መንግሥታት፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት አዉግዘዉታል።በደሉን ባደረሱት ኃይላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመዉሰድ የቃጣ ኃይል መንግስት ግን የለም።



የጄኔራል ሐምዲቲ መግለጫ



ዓለም አቀፉ ዉገዝትና ጭኸት ከተደጋጋመ በኋላ ፈጥኖ ደራሹ ጦር ሠላማዊ ሰዎች ላይ ግፍ የዋሉ ያላቸዉን አባሉትን ማሰሩን አስታዉቋል።የጦሩ አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ሮብ እንዳሉት ጦራቸዉ ግድያና ግፉን የሚያጣራ የሕግ ኮሚቴ ሰይሟል።ይሁንና ጄኔራሉ እንዳሉት ቡድናቸዉ ኤል ፋሸርን መቆጣጠሩ (በሳቸዉ አገላለፅ) ነፃ ማዉጣቱ የጦርነቱን የኃይል ሚዛን ቀይሮታል።



«የኤል ፋሸር ነፃ መዉጣት የጦርነቱን ሥልታዊ ይዘት የሚቀይር ብቻ ሳይሆን፣ ለሱዳን አንድነትም ለዉጥ ያመጣል።አንድነቱ በሰላም (በድርድር) እንዲሆን ተስፋ እናደርጋለን።በሰላም ሆነ በጦርነት ለሱዳን አንድነት ለዉጥ ነዉ።»





ወዳጆች ጠላት የሆኑበት ጦርነት



የሱዳን መከላከያ ጦርና በጦሩየሚደገፈዉ መንግስት ግን «አሸባሪ» ከሚለዉ ከፈጥኖ ደራሽ ጦር ጋር ሠላም ለማዉረድ አልደራደርም እንዳለ ነዉ።የካርቱም ባለሥልጣናት ደጋግመዉ እንዳሉት ለሱዳኑ ጦርነት ተጠያቂዋ የፈጥኖ ደራሹን ጦር የምታስታጥቀዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናት።በካይሮ የሱዳን አምባሳደር ኢማደልዲን ሙስጠፋ አዳዊ ትናንት እንዳሉት ደግሞ አራትዮሽ ከሚባለዉ የሱዳን አስታራቂ ቡድን ዉስጥ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እስካልወጣች ድረስ መንግሥታቸዉ ከቡድኑ ጋር አይተባበርም።



«የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአራትዮሹ ጥላ ሥር እንደ አስታራቂ እስካለችበት ድረስ (በቡድኑ ዉስጥ) አንካፈልም።ቡድኑ እንደ ሥሙ ትክክለኛ ተልዕኮዉን የሚወጣ ከሆነ እንካፈላለን።አለበለዚያ ከነሱ ጋር መቀመጥም ሆነ እነሱን እንደ,ገለልተኛ አስታራቂ ማየት አይቻል።»



ዩናይትድ ስቴትስ የመሠረትችዉ አራትዮሽ የተባለዉ ቡድን ራስዋን ዩናይትድ ስቴትስን፣ ሳዑዲ አረቢያን፣ ግብፅና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን የሚያስተናብር ነዉ።ቡድኑ የሱዳን የወደፊት ሰላም በተመለከተ በተደጋጋሚ ቢሰበሰቡም በካይሮና በአቡዳቢዎች መካከል በሚፈጠረዉ ልዩነት ምክንያት እስካሁን የተከረዉ ነገር የለም።



የካይሮና የአቡዳቢ ገዢዎች የመንንን ለመደብደብ ጥብቅ ወዳጅ ነበሩ።ቀጠር በማዕቀብ ለመቅጣት ተባባሪ ነበሩ።የቀድሞዉን የሶሪያ መሪ በሽር አል አሰድን ለማስወገድ ተመሳጣሪ ነበሩ።ሱዳንና ሊቢያ ጦርነት ላይ ተቃራኒ ኃይላትን ይደግፋሉ።ሱዳንም የቀድሞ ወዳጆች የገጠሙት-ወዳጆችን ያቃረነ ጦርነት ማዕከል እንደሆነች ቀጥላለች።



ነጋሽ መሐመድ



እሸቴ በቀለ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ማሕደረ ዜና፣ ኤል ፋሸር-የሱዳን እልቂት አዲስ ምዕራፍ

ማሕደረ ዜና፣ ኤል ፋሸር-የሱዳን እልቂት አዲስ ምዕራፍ

ነጋሽ መሐመድ