የትራምፕ «ክርስቲያኖችን የመታደግ» ወታደራዊ እርምጃ እና የናይጄሪያ ምላሽ
Description
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ የሽብር ጥቃቶች የናይጄሪያን ክርስቲያን ማኅበረሰብ ዒላማ አድርገዋል።የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም መንግስት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ክዷል ይላሉ። ያም ሆኖ ጥቃቱን የሚከታተሉ ቡድኖች ክርስቲያኖች ከሙስሊሞች በላይ እንደተገደሉ የሚያሳይ ማስረጃ የለም ሲሉ ይከራከራሉ።
የዶናልድ ትራምፕ ወታደራዊ እርምጃ ዛቻ
አሁን ዩናይትድ ስቴትስ የአቡጃ መንግስት «በክርስቲያኖች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ፈቅዷል» በሚል ክስ ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጄቷን ገልጻለች።የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያለፈው ቅዳሜ እንዳስታወቁት ለናይጄሪያ የሚሰጠውን እርዳታ እንደሚያቋርጡ እና ግድያዎቹ ካልቆሙ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ የመከላከያ ሚኒስትሩበናይጄሪያ ውስጥ ለሚሰነዘረው ወታደራዊ እርምጃ እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ትናንት እሁድ  ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አሜሪካ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ውስጥ ክርስቲያኖችን ኢላማ ያደረገ ግድያ ለማስቆም ወታደሮችን በናይጄሪያ ማሰማራት ወይም የአየር ድብደባ ማድረግ እንደምትችል ተናግረዋል።በአገሪቱ ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ እየጨመረ የመጣውን የሽብር ጥቃት  የናይጄሪያ መንግስት ማስቆም አልቻለም ሲሉም ይከሳሉ። 
የናይጄሪያ መንግስት ምላሽ
ይህንን ተከትሎ የናይጄሪያ መንግስት የትራምፕን ክስ ውድቅ አድርጓል። የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም መንግስት "የዘር እና የሃይማኖት ልዩነት ሳይለይ ሁሉንም ዜጎች መከላከሉን ይቀጥላል" ብሏል።
የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቢ ቃል አቀባይ ዳንኤል ብዋላ ባወጡት መግለጫ፣ ናይጄሪያ ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን ለአሜሪካ አስታውሰዋል።«ዩናይትድ ስቴትስ ከናይጄሪያ መንግስት ተሳትፎ እና ፈቃድ ውጭ የአንድ ወገን እርምጃ መውሰድ ተገቢ አይሆንም» ይላል መግለጫው ።ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አሜሪካ የምታደርገውን ድጋፍ የሚቀበል መሆኑን የገለጸው የናይጄሪያ መንግስት፤ ነገር ግን እርዳታው የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ መሆን እንዳለበትም አስጠንቅቋል።የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፁት ናይጄሪያ በትራምፕ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ልጥፍ እና ዛቻ ፍርሃት አልገባትም።
በትራምፕ ዛቻ የናይጄሪያውያን ድጋፍ እና ተቃውሞ
አንዳንድ ናይጄሪያውያን የትራምፕን ጣልቃ ገብነት ይቀበሉታል።
«ስለዚህ ክርስቲያኖች አሁን ለመንቀሳቀስ እየፈሩ ነው፣ ክርስቲያኖች በነፃነት ማምለክ ይፈራሉ። ካህናቱ፣ ምዕመናኑ የሀይማኖት መሪዎች እና ሌሎችም። ስለዚህ የሆነ ነገር መደረግ አለበት። መጥፎ ነው።»በማለት ገልፀዋል።
ሌላኛዋ ናይጀሪያዊም የትራምፕን ርምጃ ይደግፉታል። «ችግር የለብንም። የአሜሪካ ጦር ኃይል ርምጃ ቢወስድ። ቢያንስ ሰላም ይሰፍናል። ያ ለናይጄሪያ መፍትሄ የሚያመጣ ከሆነ፣ዝግጁ ነን።»ነው ያሉት።
ሌሎች DW ያነጋገራቸው ናይጄሪውያን ደግሞ የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ በሀገሪቱ ተጨማሪ የጎሳ ውጥረትን ሊያባብስ እንደሚችል ይናገራሉ።«ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ አሜሪካ ያገዘቻቸው አገሮች የረሰባቸውን ሁኔታ አይተናል። ከነበረው የባሰ ሁኔታ ፈጥረው ነው የተውት ።» ብለዋል።ሌላኛው ናሽጄሪያዊ በበኩላቸው በሽብርተኝነት ስም ሙስሊሞችን ለማጥቃት ሊውል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።«አንዳንድ ሙስሊሞች እውነተኛ ሙስሊሞች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በእስልምና ሽፋን አሸባሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ እዚህ መጥተህ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንደምትፈልግ ተናግረህ በመጨረሻ ሁሉንም ሙስሊሞች ማጥቃት ብትጀምርስ?»በማለት ገልፀዋል።
በናይጄሪያ የሽብር ጥቃት ከ15 ዓመታት በላይ ዘልቋል
ከ 200 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ናይጄሪያ ወደ 200 የሚጠጉ ጎሳዎች አሏት። በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በአብዛኛው ክርስቲያን ሲሆን ሰሜናዊ ክፍል ደግሞ አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ነው።እንደ ቦኮ ሃራም እና እስላማዊ መንግስት ባሉ የሽብር ቡድኖች ከ15 ዓመታት በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በናይጄሪያ በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ፣ መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል ታጣቂዎች በእርሻ በሚተዳደሩ ክርስቲያን ማህበረሰብ አባላት ላይ ባደረሱት ጥቃት እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል።.ይህ ጥቃት የተከሰተው በአገሪቱ ደቡብ ምዕራብ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ላይ በደረሰው አሰቃቂ የቦምብ ድብደባ እና በአስራዎቹ የሚቆጠሩ ምዕመናንን ከተገደሉ ከሶስት ዓመታት በኋላ ነው።
በጥቃቱ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ይገደላሉ
ተንታኞች እንደሚሉት በሽብር ጥቃት ክርስቲያኖች ቢገደሉም፣ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች በአገሪቱ ሰሜናዊ ምስራቅ የሚገኙ ሙስሊሞች ናቸው። ናይጄሪያ ከሃይማኖት ጥላቻ ውጪ ባሉ በጎሳ ግጭቶች እና በመሬት እና በውሃ ሀብቶች ላይ በተፈጠሩ ግጭቶች ላይ የተመሰረቱ ሌሎች የጥቃት ክስተቶችንም ታስተናግዳለች።
ዋይት ሀውስ ክርስቲያኖች ከሌሎች የጎሳ ወይም የሃይማኖት ቡድኖች በተለየ መልኩ ኢላማ መሆናቸውን የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረበም። ያም ሆኖ ያለፈው አርብ የትራምፕ አስተዳደር የተገደበ የሃይማኖት ነፃነትን በመጥቀስ ናይጄሪያን ከ"ልዩ አሳሳቢ አገሮች" ዝርዝር ውስጥ አካቷል።፣ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት ሌሎች አገሮች ፓኪስታን፣ ቻይና፣ ምያንማር፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያን ናቸው።
ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ























