የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ከምርጫ በፊት ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ ቀረበ
Description
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በተያዘው ዓመት ይካሔዳል ተብሎ ከሚጠበቀው አጠቃላይ ምርጫ በፊት ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀምሩ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት ተልዕኮ፣ የኅብረቱ አባል አገራት እና የኖርዌይ ኤምባሲዎች ጥሪ አቅርበዋል። ጀርመንን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ 22 የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ኤምባሲዎች ከአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ጋር በጥምረት ባወጡት መግለጫ “በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሰፊው ቀጠና ሰላምን ማዝለቅ እና ማጠናከር አስፈላጊ” እንደሆነ በአጽንዖት አሳስበዋል።
አውሮፓውያኑ ጥሪውን ያቀረቡት የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት የተፈረመበትን ሦስተኛ ዓመት በማስመልከት እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2018 ይፋ ባደረጉት የጋራ መግለጫ ነው። ሥምምነቱ “አሳዛኝ እና አውዳሚ ግጭት” እንዳቆመ ያስታወሱት የአውሮፓ ሀገራት ባለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ተደረጉ ያሏቸውን አዎንታዊ እርምጃዎች በመግለጫቸው ጠቃቅሰዋል።
ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ ግልጋሎቶች ሥራ መጀመር፣ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት መሻሻል፣ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ አስፈትቶ በማሰልጠን ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበት ሒደት መጀመር እና የተወሰኑ ተፈናቃዮች ቀደ ቀያቸው መመለስ በበጎ የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው።
የተፈናቀሉ ሰዎችን “ከዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግ እና ምርጥ ተሞክሮዎች” በተስማማ መልኩ መሉ ወደ ቀያቸው መመለስ እና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ ተዓማኒ የሽግግር ፍትኅን ጨምሮ በፕሪቶሪያ ከተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት ሒደት ጋር በተያያዘ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳውቀዋል።
በሁሉም ክልሎች በግጭቱ ለተጎዱ ሰዎች ፈውስ እና ፍትኅ ለማስፈን፤ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ በተለይም የሴቶች እና የልጃገረዶችን እንዲሁም ዕርቅ አስፈላጊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እየተካሔደ በሚገኘው ብሔራዊ ምክክር ውስጥ ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲሳተፉ አበረታተዋል።
“ሁሉም ወገኖች ግጭት የማቆም ሥምምነቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና ቀሪ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በጋራ እንዲሰሩ” በኢትዮጵያ የሚገኘው የካናዳ ኤምባሲ ጥሪ አቅርቧል። ግጭት የማቆም ሥምምነቱ “ለትግራይ ሰላም ቁልፍ ነው” ያሉት በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጂን ሻሒን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት “የሥምምነቱን ድንጋጌዎች እንደታቀደው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ” እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት ግጭት የማቆም ሥምምነት በተፈራረሙት ወገኖች መካከል ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀመር የቀረበውን ጥሪ በተመለከተ ዶይቼ ቬለ ከኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት መልስ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ዶይቼ ቬለ ጥያቄውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ሥዩም በኢ-ሜይል እና ለመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በዋትስአፕ አቅርቧል።
የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ “እስካሁን የተጀመረ ፖለቲካዊ ውይይት የለም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ፓርቲው “በተደጋጋሚ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀመር” ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለአፍሪካ ኅብረት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱን የገለጹት አቶ አማኑኤል የአውሮፓ ኅብረት በአዲስ አበባ ከሚገኙ ኤምባሲዎች ጋር ያቀረበው ጥሪ “የዘገየ” ቢሆንም “በጣም አስፈላጊ” እንደሆነ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል።
“ህወሓት ሁሌም መግለጫ ሲያወጣ የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር በአጽንዖት ነበር ሲጠይቅ የነበረው” የሚሉት አቶ አማኑኤል “ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ወደዚህ ጉዳይ መግባት አልፈለገም” በማለት ይተቻሉ። “አሁን የአውሮፓ ኅብረት ከምርጫ በፊት የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ያወጣውን ጥሪ በጣም ትክክለኛ እና ጊዜውን የጠበቀ ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግጭት የማቆም ሥምምነቱን በማስመልከት የሰጡት ማብራሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 የተፈረመው ሥምምነት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ያሳበቀ ነበር።
“ፕሪቶሪያ የተደራደርንው ከጄኔራል ጻድቃን ጋር ነው። ከጌታቸው ረዳ ጋር ነው፤ ከአሰፋ አብርሀ ጋር ነው። ዋንኛ ተደራዳሪ ከትግራይ ወገን ጻድቃን፣ ጌታቸው እና አሰፋ ሌሎች ሰዎችም ይኖራሉ። ዋናዎቹ እነዚህ ናቸው፤ፈራሚዎቹ” ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በሥፍራው ያልነበሩ ሰዎች፤ አንዳንዶች ፕሪቶሪያን የማያውቁ ሰዎች ደግሞ ፕሪቶሪያን እናስከብር ይላሉ አሁን” ሲሉ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህ “ድምዳሜ” በመጋቢት 2017 የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት በምርጫ ቦርድ ከመሰረዙ ጋር ተደማምሮ በፕሪቶሪያ ለተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት እና ለአጠቃላይ የሰላም ሒደቱ “ታማኝነት ከባድ ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ አንድምነታ” እንደሚኖረው ህወሓት አስጠንቅቋል።
ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ በተፈራረሙት ሰነድ “መሠረታዊ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት ቃል ገብተዋል።” ሥምምነቱ ከተፈረመ ከሦስት ዓመታት በኋላ ግን ሁሉም ውሎች ተግባራዊ አልሆኑም። የውሉ ፈራሚዎችም እርስ በርስ በመወቃቀስ ላይ ናቸው።
አቶ አማኑኤል “የኢትዮጵያ መንግሥት በፕሪቶሪያው ሥምምነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥሰት ይፈጽማል” ሲሉ ይከሳሉ። “በፕሪቶሪያው ሥምምነት ውስጥ የተቀመጡ ግዴታዎቹን በአግባቡ ባለመፈጸም የሚፈጸሙ ጥሰቶች አሉ” ያሉት የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበር “በሁለተኛ ደረጃ የተከለከሉ ጉዳዮችን በመፈጸም፤ ለምሳሌ ከትግራይ ኃይሎች እየወሰደ በአፋር እና በተለያዩ ሌሎች አካባቢዎችም ትግራይን የሚወጉ ታጣቂ ኃይሎችን በማሰልጠን፤ በማደራጀት እንዲሁም ሥምሪትን በመስጠት እየሠራ ነው” በማለት ወንጅለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጦርነቱ ወቅት የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ሥራ ማስጀመርን ጨምሮ መንግሥታቸው በሥምምነቱ መሠረት ያከናወናቸውን ጉዳዮች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል። ማብራሪያቸው የሥምምነቱ ዓላባዎች እና አተገባበሮቻቸው ላይ ያተኮሩ ቢሆንም ደጋግመው በህወሓት ላይ ትችቶች ሰንዝረዋል።
ሁለቱ ወገኖች የትግራይ ኃይሎች “ትጥቅ በDDR ይፈታል” የሚል ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “መሣሪያ መደበቅ አልተስማማንም፤ ማሰልጠን ማስመረቅ አልተስማማንም” ሲሉ በተዘዋዋሪ ከሰዋል። “ሥምምነቱ የታጠቀው ያስረክባል ነው እንጂ መሣሪያ ደብቆ ማስቀመጥ ወይም በኮንትሮባንድ ለመግዛት መሞከር የሚል ሥምምነት ላይ አልነበረም” ሲሉ ወንጅለዋል።
በጦርነቱ ወቅት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ስልት፣ በትግራይ እና የአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄ የተነሳባቸው ቦታዎች ጉዳይ ገና መፍትሔ የሚሹ ናቸው። ሦስት ክልሎች ያዳረሰው አሰቃቂ ጦርነት ግጭት በማቆም ሥምምነት ከተገታ በኋላ የታየው የኃይል አሰላለፍ ለውጥ እና በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የበረታው ቅራኔ ዳግም ውጊያ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ሥጋት የፈጠረ ነው። ባለፉት ተከታታይ ወራት የታዩ የትግራይ ኃይሎች የሥልጠና እና የምረቃ መርሐ-ግብሮች ሥጋቱን የሚያጠናክሩ ናቸው።
አቶ አማኑኤል ግን “አንድም አዲስ ኃይል የሰለጠነ የለም” በማለት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። “በTDF ውስጥ ያሉ ታጋዮች ሥልጠና ማካሔድ routine ሥራቸው ነው” ያሉት አቶ አማኑኤል “ትግራይ ውስጥ ያሉ ችግሮች ከተፈቱ እና የሕዝቡን ደሕንነት በሚጠብቅ መልኩ የፕሪቶሪያ ሥምምነቶች ሲፈጸሙ ትግራይን የወረሩ ኃይሎች ሲወጡ DDR በሥርዓቱ እንደሚፈጸም በፕሪቶሪያው ሥምምነት ላይ ተቀምጧል” በማለት አብራርተዋል።
አርታዒ ኂሩት መለሰ























