DiscoverDW | Amharic - Newsትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳኖች እልቂት፣ ወሳኝ ማዕድን በአፍሪቃ
ትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳኖች እልቂት፣ ወሳኝ ማዕድን በአፍሪቃ

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳኖች እልቂት፣ ወሳኝ ማዕድን በአፍሪቃ

Update: 2025-11-01
Share

Description



ሱዳን የዕልቂት አብነት



እንደ ጥሩ ወዳጅ ባንድ አብረዉ የጋራ አለቃቸዉን ከሥልጣን ያስወገዱት የሱዳን የጦር ጄኔራሎች በሥልጣን ሽሚያ ተጣልተዉ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት ዉጊያ ከጀመሩ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ደፈኑ።የሚያዟቸዉ የመከላካያ እና የፈጥኖ ደራሽ ጦር ኃይላት ዛሬም ይዋጋሉ።የሱዳንን ሥልታዊ አቀማመጥና ከነዳጅ ዘይት እስከ ወርቅ፣ ከብረት እስከ ሬር ኧረዝ የሚዘረዘር እምቅ ሐብቷን ለመቀራመት ያሰፈሰፉ የሩቅም-የቅርብም፣ ኃያልም-ሐብታምም መንግሥታት ተፋላሚዎችን ያስታጥቃሉ።

የደኸይቱ አፍሪቃዊት ሐገር ደኻ ሕዝብ መዓልት ወሌት ያልቃል፣ ይቆስላል፣ ይሰቃያል፣ የተሳካለት ይሰደዳል።የሰሞኑ የእልቂት ማዕከል ኤል-ፋሸር ናት።ፋትማ አብድረሕማን ከመዓቱ ተርፈዋል።ልጆቻቸዉን ግን



«በርካታ የከባድ ጦር መሳሪያ ጥቃት ነበር።እኔ እራሴ በጥቃቱ ተመትቻለሁ።ልጄ ተገድላለች።ሌለኛዋ ልጄ አይኗ ተመትቷል።ወንድ ልጄ ሽባ ሆኗል።እኔም በተኩሱ ተመትቻለሁ።ሰዉነቴ ቁስል ብቻ ነዉ።አብጧልም።ትናንትና የቁስሉን መሸፈኛ (ፋሻ) ቀይሬያለሁ።»



የሰማ እንጂ የመለሰ የለም



የመብት ተሟጋቾች ፣ ርዳታ አቀባዮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ለሰላማዊዉ ሰዉ ከለላ እንዲደረግለት፣ ርዳታ እንዲሰጠዉም ያልጠየቁ፣ ያላሳሰቡበት ጊዜ የለም።ጮኸት፣ ጥሪ ማሳሰቢያዉን የሰማ እንጂ ሁነኛ መልስ የሰጠ የለም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ዋና ፀሐፊ ማርታ አማ አክያ እንደሚሉት በተለይ ኤል ፋሸር ላይ ታላቅ ቀዉስ መከሰቱ በተደጋጋሚ ተዘግቦ ነበር ይላሉ።እርምጃ ግን አልተወሰደም።

«ኤል ፋሸር ዉስጥ ሥላለዉ ከፍተኛ ቀዉስ ለወራት ተዘግቦ፣ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያም ተሰጥቶ ነበር።እስካሁን ድረስ ሁኔታዉ እንዳይባባስ ለመከላከል የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የወሰደዉ ርምጃ የለም።አዉዳሚዉን ጦርነት ለማስቆም ሁላችንም የየራሳችንን ሚና መጫዎት አለብን።»



የጦርነቱ ያስከተለዉ ጥፋት



በሁለት ዓመት ከመንፈቁ ጦርነት ያለቀዉን ሕዝብ በትክልል የቆጠረዉ የለም።አንዳዶች ከ150 ሺሕ በላይ ሕዝብ ተገድሏል ይላሉ።ሌሎች የሟቹን ቁጥር ከ250 ሺሕ ያስበልጡታል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዓለም ትልቁ ሰብአዊ ቀዉስ ያለዉ ጦርነት ከ14 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አንድም አሰድዷል፣ ሁለትም ከቤት ንብረቱ አፈናቅሏል።



ሴቶች ተደፍረዋል።ቁስለኞች ሕክምና አጥተዉ በረሐ ላይ ወድቀዋል።ከርዕሠ ከተማ ካርቱም እስከ ሰሜን ኮርዶፋን የሚገኙ ከተሞች፣ መንደሮች፣የጤና፣ የኃይማኖት፣ የማሕበራዊ አገልግሎት መስጪያ ተቋሟት፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጋይተዋል፣ተመዝብረዋል።መንገዶች፣ ድልድዮች፣ አዉሮፕላን ማረፊያዎች ወድመዋል።



ትልቅ «ክፍት የመቃብር ሥፍራ»





ካለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ጀምሮየዓለምን ትኩረት የሳበዉ ምዕራባዊ ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሸር ላይ የተፈፀመና የሚፈፀመዉ ግፍ ነዉ።ከተማይቱን እንደ አብዛኞቹ አካባቢዎች ይቆጣጠር የነበረዉ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ነበር።ጦርነቱ ከተጀመረበት ከሚያዚያ 2015 ወዲሕ ግን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) በምሕፃሩ የኤል ፈሻር ከተማን ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ ሞክሮ ነበር።



ፈጥኖ ደራሹ ጦር በተለይ ባለፉት 18 ወራት የከተማይቱን መዉጪያ መግቢያ ዘግቶ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይገባ በማገዱ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ በረሐብና በመድሐኒት እጦት አልቋል።እልቂቱን ያዩ የሱዳን የመብት ተሟጋቾች «ክፊት ሰፊ መቃብር» እስከማለት ደርሰዉም ነበር።ፈጥኖ ደራሹ ጦር ከበባዉን እያጠበበና እያጠናከረ ቆይቶ የመከላከያ ኃይሉን መከላከያ ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ሰብሮ ዕሁድ ተቆጣጠራት።

ከዚያማ የመብት ተሟጋቾች «ክፍት፣ ሰፊ መቃብር» ያሏት ከተማ ልጅ-ካዋቂ፣ ሴት-ከወንድ፣ በሽተኛ ከጤነኛ ሳይለይ ባደባባይ የሚገደሉባት «የሰዎች ቄራ» ሆነች።መንበሩን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገዉ PAEMA ድርጅት የሱዳን ጉዳይ አጥኚ ሻይና ሊዊስ እንደሚሉት የRSF ታጣቂዎች ጭካኔ አቻ አይገኝለትም።

«በዓለም ላይ ሌላ ኃይል ከዚሕ የበለጠ ጭካኔ ወይም አረመኔነት ይፈፅማል ብዬ አላስብም።እንደሚመስለኝ ልዩነት ለRSF ይሕ (ርምጃ) ሆን ተብሎ የሚፈፀም የዘር ማጥፋት ፖሊሲያቸዉ መሆኑ ነዉ።ይሕ ቅጥ ያጣ ዉድመት፣ሆስፒታል ዉስጥ የተኙ በሽተኞችንና የሕክምና ባለሙያዎችን መግደል እነሱ ሁሌም የሚያደርጉት ሥልት ነዉ።»



ሕሙማንና ሐኪሞችም ሰለቦች ናቸዉ





ኤል ፋሸርን ከሌላዉ ዓለም ጋር የሚያገናኝ የሥልክ፣ የኢንተርኔት፣ የመንገድም ሆነ ሌላ መስመር በመዘጋቱ ካለ,ፈዉ ዕሁድ ጀምሮ የሚፈፅምባትን ግፍ በትክክል የሚያዉቅ የለም።የሳተላይት ምሥሎች ፣ ከተማይቱን የሚቆጣጠረዉ የፈጥኖ ደራሹ ጦር ባልደረቦች የሚያሰራጯቸዉን የቪዲዮ ምሥሎች፣ የቃል መረጃዎችና ከከተማይቱ ያመለጡ ሰዎችን ዋቢ የሚጠቅሱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት እንዳሉት ግን ካለፈዉ ዕሁድ እስከ ሐሙስ ድረስ ብቻ ወደ ሁለት ሺሕ የሚጠጉ ሠላማዊ ነዋሪዎች ተረሽነዋል።



በከተማይቱ ዉስጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግሎት በሚሰጠዉ የሳዑዲ አረቢያ ሆስፒታል ዉስጥ የተኙ በመቶ የሚቆጠሩ ሕሙማንና የሕክምና ባለሙያዎቻች ተገድለዋል።ከከተማይቱ ማምለጥ የቻሉ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሌላ ሥፍራ ሸሽተዋል።



የዓለም መንግሥታት ዉግዘት፤ ቃላት እንጂ እርምጃ የለም





ኤል ፋሸር ዉስጥ የተፈፀመዉንግፍ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቀጠር፣ ግብፅ፣ ብሪታንያ ሌሎች መንግሥታትና የአዉሮጳ ሕብረት አጥብቀዉ አዉግዘዉታል።የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈዉ ሐሙስ ባደረገዉ ጉባኤም የሠላማዊ ሰዎችን መገደልና መሰቃየት አዉግዟል።

የርዳታ አቅራቢ፣ የመብት ተሟጋቾችና የዓለም ፍርድ ባልደረቦች ግን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የግፈኞችን እርምጃ ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጠንካራ ርምጃ መዉሰድ አለበት እያሉ ነዉ።ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን መከላከያ ጦርና በጦሩ የሚደገፈዉ መንግሥት በበኩሉ ለኤል ፋሻሩ ግፍም ሆነ ባጠቃላይ ሱዳን ለሚያመሰቃቅለዉ ጦርነት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ተጠያቂ አ,ድርጓል።የተባበሩት አረብ ኤምሬት ገዢዎች ወቀሳዉን አልተቀበሉትም።

ወቀሳ፣ ዉግዘትና የተጨማሪ ርምጃ ጥሪ ካየለ በኋላ የፈጥኖ ደራሹ ጦር አዛዦች ኤል ፋሸር ዉስጥ ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል ወንጀል የተጠረጠሩ ተዋጊዎቻቸዉን ማሰራቸዉን አስታዉቀዋል።



ሬር-ኧርዝ ለአፍሪቃ ትሩፋት ይሆን፣ ርግማን





ዘመኑ የተንቀሳቃሽ ሥልክ፣ የሳተላይት፣ የኤሌክትሪክ መኪና የሰዉ አዉልባ አዉሮፕላ (ድሮን)--- ብቻ የቴክኖሎጂ ዕድገትና በዕድገቱ ዉጤት የሚዘወር ጊዜ ነዉ።ሁሉም ብዙና የተለያየ ነገር ይፈልጋሉ-ከሚፈልጉት አንዱ ግን ለሁሉም አስፈላጊ ደግሞም ወሳኝ ነዉ።ማዕድን።ለብዙ የቴክኖሎጂ ዉጤቶች ወሳኝ በመሆኑ አንዳዶች «ወሳኝ» (ክሪቲካል) ሲሉት፣ እንደልብ አለመገኘቱን ለስያሜ የሚመርጡት ደግሞ የአልፎ አልፎና መሬት አሉት-ሬድ።

ወሳኝ ማዕድን ወይም ሬር-ኧርዝ እያልን እንቀጠል።የዶቸ ቬለ የመረጃ ትንታኔ እንደሚያመለክተዉ ኮባልት፣ ፕላቲኒየም፣ታንታለምና ሌሎች ሬር ኧርዝ የሚያስተናብራቸዉ ማዕድናት አፍሪቃ ዉስጥ በሽ ነዉ።



ወሳኝ ማዕዳናት ለአፍሪቃ ፋይዳና ጠንቃቸዉ



እስኪ አብረን እንጠይቅ ወይም መልስ እንሻ።የኢትዮጵያ ቡና፣ ከብት፣ የኬንያ ሻሒ፣ የኮት ዲቯር ካካኦ፣የቡርኪና ፋሶ ጥጥ፣ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ ጋና የተነጠፈዉ ወርቅ፣ የቦትስዋና አልማዝ፣ የግብፅ ፒራሚድ፣ ከአንጎላ እስከ ናጄሪያ የሚዛቀዉ ነዳጅ፣ የዛምቢያ መዳብ፣ የኒዠር ዩራኒየም ለአፍሪቃ ሕዝብ ጠቅሞ ይሆን? የአፍሪቃ ሕዝብ ግን---ዓለም የመሰከረለት የድሆች-ደሐ መሆኑን ነዉ።ነባሮቹ የተፈጥሮ ሐብቶች ያልጠቀሙት አዲስ የሚፈለጉት ይጠቅሙት ይሆን?



የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ወሳኝ ከሚባሉት ማዕድናት አፍሪቃ ትጠቀማለች ባይ ነዉ።ደግነቱ ሕዝብ አላለም።የገንዘብ ተቋሙ እንደሚለዉ ማዕድናቱ ከሰሐራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ ሐገራትን ምጣኔ ሐብት በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ዉስጥ በ12 በመቶ ያሳድጋል።

ማዕድናቱ በብዛት ከሚገኝባቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ናት።የኮንጎዉ የሕግ ባለሙያና የተፈጥሮ ሐብት ጉዳይ ተጠሪ ጂሚ ሙንጉሪክ ልክ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሁሉ አፍሪቃ ትጠቀማለች ባይ ናቸዉ።



«ፍላጎቱ እየጨመረ ሲሄድና የአፍሪቃ ሐገራት ይህንን ማዕድን ሲያቀርቡ ማዕድኑ የእነዚሕ አፍሪቃ ሐገራትን ልማት ማሳደጉ የማይቀር ነዉ።ይሕ ተጠየ,ቃዊ ዕዉነት ነዉ። ማዕድኑ የሚያስገኘዉ በጎ ጥቅም ነዉ።በአካባቢ ደረጃም እድገት ያመጣል።በሐገር ደረጃ ደግሞ ለአፍሪቃ መንግሥታት ብዙ ማዕድናት ወደ ዉጪ በሸጡ ቁጥር ገቢያቸዉም ይጨምራል።»



የማዕድን ሐብት መዘዝ



ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሩዋንዳና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን በቀጥታም በተዘዋዋሪም፣ ተጓዳኞቻቸዉን እያከለም የሚያዋጋዉ ግን ከሁለቱ ሐገራት የፖለቲካ ጠብ ይልቅ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የማዕድን ሐብት እንደሆነ ያልተነገረበት ጊዜ የለም።

በ1990ዎቹ ብዙዎቹን የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራትን ኃይላት ያጋደለዉ የሴራሊዮን አልማዝ እንደነበር ዓለም ዘንግቶት ይሆን? ይሕም ይቅር በሱዳኑ የርስበርስ ጦርነት አቡዳቢ-ካይሮ፣ ሞስኮ-ለንደኖችና ሌሎች ተቀናቃኞችን የሚረዱት ለምን ይሆን? ለወርቅ።



የሕግ ባለሙያ ጂሚ ሙንጉሪክ ወሳኙ ማዕድንሌላም አሉታዊ ገፅታ አለዉ ይላሉ።የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃና ሰብአዊ መብት።

«ለአፍሪቃ ሐገራት አፅንኦት የምሰጠዉ አሉታዊ ዉጤቱ ከተፈጥሮ ሐብት ጥበቃና ከሰብአዊ መብት ይዞታ ጋር የሚገናኙ ናቸዉ።የብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት መንግሥታት ደካሞች ናቸዉ።ይሕ ማለት ማዕድን አዉጪ ኩባንዮች የተፈጥሮ ሐብትን እንዲጠበቁ ማድረግ ከፍተኛ ፈተና ነዉ።የተፈጥሮ ጥበቃ ሥንል የዉሐና፣የአየር መበከል፣የደን መመንጠር ነዉ።ቁፋሮ በሚደረግበት አካባቢ የሚኖረዉ ሕዝብ ከቀየዉ እንዲነሳ ይገደድ ይሆናል።»

የአፍሪቃ ሐገራት ካላቸዉ የሬር ኧርዝ ወይም ወሳኝ ማዕድን እስካሁን ለገበያ የሚያቀርቡት 40 በመቶዉን ብቻ ነዉ።



ማዕድናቱ የት ነዉ ያሉት?



የአዉሮጳ ሕብረት እንዳስታወቀዉለሕብረቱ የኤኮኖሚ ዕድገት 34 የማዕድን ዓይነቶች በጣም አስፈላጊ ናቸዉ።አብዛኞቹ ማዕድኖች ደግሞ በሕብረቱ አባል ሐገራት ዉስጥ አይገኙም።የዶቸ ቬለ ያገኘዉ መረጃ እንደሚያመለክተዉ ለኮምፒዉተር መስሪያ በጣም አስፈላጊ የሆነዉ ፕላቲኒየም ለዓለም ገበያ ከሚቀርበዉ 70 በመቶዉ የሚመረተዉ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ።



ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ደግሞ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ መኪኖች ባትሪና ከፀሐይ ለሚመነጭ ኃይል ወሳኝ የሆነዉን ኮባልት 70 በመቶ ያክል ታመርታለች።ታንታለም የሚወጣበት ኮናል በብዛት የሚመረተዉም ኮንጎ ዉስጥ ነዉ።መጠኑ አነስ ይበል እንጂ ጋና፣ ሞሪታንያ፣ አንጎላ፣ ዩጋንዳና ሌሎች ሐገራትም የተለያዩ ዉድ ማዕድናትን ይሸጣሉ።በ2023 የአፍሪቃ ሐገራት ለዓለም ገበያ ያቀረቡት ዉድ ማዕድን 266 ቢሊዮን ዶላር አዉጥቷል።አብዛኛዉን የሸመተቺዉ ቻይና ናት።



ነጋሽ መሐመድ





Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳኖች እልቂት፣ ወሳኝ ማዕድን በአፍሪቃ

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳኖች እልቂት፣ ወሳኝ ማዕድን በአፍሪቃ

ነጋሽ መሐመድ