DiscoverDW | Amharic - Newsከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የተባለው የሱዳን ጦርነት
ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የተባለው የሱዳን ጦርነት

ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የተባለው የሱዳን ጦርነት

Update: 2025-11-05
Share

Description

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አንስቶ ከሱዳን ጦር ጋር የሚዋጋው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በምህጻሩ RSF ባለፈው ሳምንት ኤልፋሸርን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ አድማሱን እያሰፋ በኮርዶፋን ላይ ጥቃቱን እያጠናከረ ነው። በሰፊው ምዕራብ ዳርፉር፣ የሱዳን ጦር የመጨረሻው ጠንካራ ይዞታ በሆነችው በኮርዶፋን ትናንት በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 40 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤በርካቶችም ቆስለዋል ።



የአካባቢው ምንጮች ለተመድ የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ በምህጻሩ OCHA እንደነገሩት ሰዎቹ የሞትቱትና የቆሰሉት በሰሜን ኮርዶፋን ዋና ከተማ በኤል ኦቤይድ ይካሄድ በነበረ የቀብር ስነስርዓት ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ነው። RSF ባለፈው ሳምንት ሰሜን ኮርዶፋን የሚገኘውን ባራንና የሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤልፋሸርን ጨምሮ ሌሎች ስልታዊ የሚባሉ ከተሞችን መልሶ ከያዘ በኋላ የሁለቱ ኃይሎች ውጊያ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ እየተነገረ ነው።



RSF ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤልፋሸርንና በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ 71 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ከአካባቢው ሸሽቷል። አብዛኛዎቹም ከኤልፋሸር40 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው ታዊላ በተባለው ከተማ ውስጥ ወደሚገኙ በሰዎች እጅግ በተጨናነናነቁ መጠለያዎች ውስጥ ነው የሚገኙት። በውጊያዎቹ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም ከአካባቢዎቹ ሸሽተው ያመለጡ እንደሚሉት በመንገዳቸው ላይ በርካታ አስከሬኖችን አይተዋል።



«ከአካባቢያችን ተፈናቅለን በሸሸንበት መስመር ላይ በርካታ አስከሬኖችን አይተናል፤ የሴቶችና የወጣቶች። ማንም የሚቀብራቸው የለም። » ያሉት ውጊያውን ሸሽተው በአልታዊ መጠለያ የሚገኙት ዛሀራ መሐመድ ናቸው። ፋውዚያ ሀሰን የተባሉት ሌላዋ ተፈናቃይ እንደተናገሩት የሟቾች ቁጥር ብዙ ነው።« በኤልፋሸር የተሰዋውን ወታደሩን ወንድ ልጄን ጨምሮ ፣ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች ተገድለዋል። ሌላው ወንድ ልጄ ደረቱና ዓይኑ ላይ ቆስሏል። በዘፈቀደ በሚካሄድ ድበደባ በየቀኑ ቢያንስ ከ30 እስከ 40 ሰዎች ይገደላሉ። » ያሉት ፋውዚያ በየአካባቢው ስርዓተ አልበኝነት ሰፍኗል ሲሉም ተናግረዋል።



«በኤልፋሸር ብዙ ተሰቃይተናል ይሁንና ከህጻንነታችን አንስቶ እንዲህ ዓይነት ነገር አይተን አናውቅም። መንገዶቹ በሞተር ብስክሌቶችና ግመሎች በሚንቀሳቀሱ ወሮበላዎች ተሞልቷል። ሰዉን ይደበድባሉ፤ የያዙትን ገንዘብ ይሰርቁባቸዋል፤ ያላቸውን ብርድ ልብሳቸውን ሳይቀር ይወስዳሉ።»



በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለውና ሚሊዮኖችን ያፈናቀለው የሱዳን ጦርነት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ አዳዲስ አካባቢዎችም መስፋፋቱ ሰብዓዊውን ቀውስ እንዳይባባስ ፍርሀት አሳድሯል። እየተባባሰ የሄደው የሱዳኑ ጦርነት ትኩረት በሳበበት በዚህ ወቅት ላይ የተመድ ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ ሲያቀርብ ኳታር ደግሞ ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቃለች።ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ ለሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ሀሳብ አቅርባለች።



እንደተፈናቃዮቹ ሰብዓዊው ቀውስም እጅግ ተባብሶ ቀጥሏል። RSF አሁን የዳርፉርን ግዛትና የደቡብ ሱዳንን አንዳንድ ክፍሎች ተቆጣጥሯል። በናይልና በቀይ ባህር መስመር የሚገኙ የሱዳን ሰሜን ፣ምሥራቅና ማዕከላዊ ግዛቶች ደግሞ በሱዳን ጦር ስር ናቸው። የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለRSF የጦር መሣሪያ በማቅረብ ስትከሰስ ቆይታለች። ሆኖም ይህን ክስ በተደጋጋሚ አስተባብላለች። የሱዳን ጦርም በበኩሉ ከግብጽ፣ ሳዑዲ አረብያ ቱርክና ኢራን ድጋፍ እንደሚያገኝ ታዛቢዎች ይናገራሉ።





ከውጭ በሚገኝ ድጋፍ በሱዳን ሁለቱ ኃይሎች የሚያካሂዱት ውጊያ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የተመድ አስታውቋል። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬሽ ትናንት ኳታር ውስጥ በተካሄደ የተመድ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት በሀገሪቱ የሚካሄደው ውጊያ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል። ይህ እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።



«ንግግሬን መጀመር የምፈልገው ከቁጥጥር ውጭ በሆነው በአሰቃቂው የሱዳኑ ቀውስ ነው። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ባለፈው ሳምንት ኤል ፋሸር ከገባ ወዲህ ሁኔታዎች ከቀን ወደቀን ተባብሰዋል። ሰዎች በምግብ እጥረት በበሽታ እና በጥቃት እየሞቱ ነው። ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግና ሰብዓዊ መብቶች መጣሳቸው መቀጠሉን የሚጠቁሙ መረጃዎችን እንሰማለን። በዘፈቀደ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሲቭሎችና ሆስፒታሎችን ጨምሮ የሲቪል ተቋማት ጥቃቶች ይካሄዳሉ። ፆታና ዘርን መሰረት ያደረጉ አሰቃቂ ጥቃቶችም ይፈጸማሉ። አሁን ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ከተማይቱ ከገባ በኋላ ደግሞ መጠነ-ሰፊ ግድያዎች እንደሚፈጸሙ የታማኝ ምንጮች ዘገባዎችያሳያሉ። ይህ ለግምት አስቸጋሪ የሆነው ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም ዳግም ጥሪ አቀርባለሁ »



የኳታር ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን አህመድ አል ታኒ በበኩላቸው በኤልፋሸር ፣ዳርፉር የተፈጸሙትን ግፎች ዶሀ ኳታር በተካሄደው የተመድ ጉባኤ ላይ ዘርዝረው፣ ድርጊቱንም አውግዘዋል። መፍትሄውንም ጠቁመዋል።





«ይህን ንግግር በኤልፋሸር ከተማ በዳርፉር የተፈጸመውንና የጋራ ድንጋጤያችንን እንዲሁም በጥብቅ ማውገዛችንን ሳልጠቅስ መዝጋት አልፈልግም። የአገሮችን ደህንነት፣ ሉዓላዊነታቸውንና መረጋጋትን ማዛባት፣ የእርስ በርስ ጦርነቶችንና ጭካኔዎቻቸውን ወደ ኋላ የመመለስ ቀላልነት ችላ ማለት እንዲህ አይነት ድንጋጤዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ለመገንዘብ ተጨማሪ ማስረጃ ያስፈልገን ነበርን?ሱዳን ለሁለት ዓመታት ተኩል በዚህ አስከፊ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች። ጦርነቱን ለማስቆም እና የሱዳንን አንድነት፣ ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነት የሚያስከብር የፖለቲካ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ጊዜው ደርሷል።»



ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ለሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁም ሀሳብ ማቅረቧ ተሰምቷል። በጉዳዩ ላይ የሱዳን ጦር የፀጥታና የመከላከያ ምክር ቤት ትናንት ተነጋግሮ ነበር። ከንግግሩ በኋላ የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር የትራምፕ አስተዳደር በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ለሚያደርጋቸው ጥረቶች አመስግነው ጦራቸው ከRSF ጋር የሚያካሂደው ጦርነት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ይሁንና ሚኒስትሩ ዩናይትድ ስቴትስ ስላቀረበችው የተኩስ አቁም ሀሳብ በዝርዝር የተናገሩት ነገር የለም።



ኂሩት መለሰ



እሸቴ በቀለ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የተባለው የሱዳን ጦርነት

ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የተባለው የሱዳን ጦርነት