DiscoverDW | Amharic - Newsየትግራይ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ዕለት ሲዘከር
የትግራይ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ዕለት ሲዘከር

የትግራይ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ዕለት ሲዘከር

Update: 2025-11-04
Share

Description

አቶ ብርሃነ ታፈረ ይባላሉ የምዕራባዊ ትግራይ ነዋሪ ነበሩ ። የትግራዩ ጦርነት ሲቀሰቀስ ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ሰዎች አንዱ ናቸው ። ብርቱ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ያስከተለውን ጦርነት ሲቀሰቀስ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ያስታውሳሉ ።



«በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው የነበረው በተለይ ምዕራብ ትግራይ አካባቢ ነበር የነበርነው፤ እዚያ የነበረው በጣም አስቸጋሪ ነበር ። ወዲያው ነበር የተከበብነው እኛ ፤ መውጫ መግቢያም አጥተን በጣም ከፍተኛ ችግር ነው የነበረው።»



ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ በኋላ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እነሆ አሁን አምስት ዓመት ሞላው ። በጦርነቱ እስካሁን በገለልተኛ ወገን የተረጋገጠ ይፋዊ መረጃ ባይወጣም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በጦርነቱ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ። ቁጥራቸው በውል ያልተለየ ሰዎች የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው ፤ በርካታ ሴቶች የመደፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የሚያመለክቱ ዘገባዎችም ሲወጡ ቆይተዋል።



በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አሁንም ድረስ መቋጫ ላልተገኘላቸው ግጭቶች መባባስ ምክንያት የሆነው የትግራይ ጦርነት በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች ጋር በፕሪቶሪያ በተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊገታ ችሏል። ምንም እንኳ ከዚያ በኋላ በተለይ በትግራይ ክልል ሰላምም ጦርነትም ያልነበረበት ሁኔታ ቢቀጥልም።



ተፈናቃዩ አቶ ገብረማሪያም አምስቱ ዓመት ለእርሳቸው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ኹኔታ ውስጥ ነው ያለፈው።



« በጣም ከባድ ኑሮ ነው ያሳለፍነው ። እስከስድስት ወር እህልም የሚባል ነገር አልመጣልንም ። በቃ ዝም ብለን ህዝብ እያዋጣ ነው የሰጠን። የሽሬ ህዝብ እያዋጣ ነው ያቆየን። ከስድስት ወር በኋላ ለአንድ ወር ይመጣል ፤ ሁለት ወር ይጠፋል። ቆየና በጣም ተቸገርን። ብዙ ችግር አሳልፈን ከላይ ብርድ ከታች ዉሃ መጠለያ አጥተን ወደ ትምህርት ቤት ገብተን በስንት ችግር ነው ያሳለፍነው »



ተፈናቃዩ ብርሃነ ታፈረ በበኩላቸው ያለፉትን አምስት ዓመታት በርዳታ ማለፋቸውን እያስታወሱ መጪው ጊዜ ግን የበለጠ ያሳስባቸዋል።



«እንግዲህ አምስት ዓመት ያው መቼም እንዳያልፍ ሆኖ አልፏል። ቀጣዩ ነው እንጂ ችግሩ። እስካሁን መቼም አንዳንድ የሰብአዊ ድርጅቶች እያገዙን እንደምንም ብለን እስካሁን አልፈናል። እንግዲህ ከአሁን በኋላ ምን እንደሚውጠን እንጃ እንጂ »



ጦርነቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ካስከተለው ሰብአዊ እና ማህባራዊ ቀውስ ባሻገር በአማራ እና አፋር ክልሎችም ተመሳሳይ ውድመት አስከትሏል። በአማራ ክልል በሌላ የግጭት ምዕራፍ የቀጠለው ሰብአዊ ቀውስ ብርቱ ጉዳት እያደረሰ ቢቀጥልም በትግራዩ ጦርነት የደረሰው ጥፋት ግን ለተጎጂዎች ዘላለማዊ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።



የደቡብ ወሎ ነዋሪዋ ዘውድነሽ በጦርነቱ ወቅት የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ አባቱን በውል የማያስታውሱትን ልጅ ያሳድጋሉ ። ጦርነቱ ካደረሰባቸው የስነ ልቦና ጉዳት ለማገገምም ብርቱ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።



« በጣም በጣም ከባድ ነበር የደረሰው ። እኔ ሳስበው በጣም ይከብደኛል። ልጅን ያክል ነገር መውለድ በጣም ከባድ ነው። ወልዶ ማሳደግ ይከብዳል። ከተወለደ በኋላ ደግሞ አባት መጠየቅ ከባድ ነው። ያንን ሁሉ ሰቆቃ አሳልፈን እዚህ የደረስነው። »



ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 የተካሔደውን ጦርነት የተቀሰቀሰበትን ዕለት ተሳታፊ የነበሩ ወገኖች በተለያየ መልኩ ዘክረዋል ። የጦርነት ገፈት ቀማሹ ህዝብግን ለደረሰበት የጦር እና በሰብአዊነት ላይ ለተፈጸመበት ወንጀል ፍትህ ሳያገኝ ሌላ ጦርነት እየተጎሰመለት መሆኑ ያሳስበዋል። የደቡብ ወሎዋ የጥቃት ሰለባ ያለፈው ጦርነት ጠባሳ ሳይደርቅ በአማራ ክልል ሌላ ሰብአዊ ጉዳት እያደረሰ ያለው ጦርነት በእንቅርት ላይ እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት።



«ድምጹ ቢሰማንም ትንሽ ራቅ ብሎ ሰሜን መስመር ላይ በጣም ከባድ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ። ትምህርት ያላገኙ ልጆች አሉ። ወጥተህ መመለስ የለም። ሰላም የለም አሁን ምን ያጋጥማቸዋል ፣ ልጆቻችን ምን ይሆናሉ ፤ እናስ ምን እንሆናለን እያልን የጭንቅ ኑሮ ነው የምንኖረው። »



እንደዚያም ሆኖ ግን የመደፈር ጥቃት ሰለባዋ ዘውድነሽ የትግራዩ ጦርነት ላደረሰባቸው በደል ፍትህ ይረጋገጥላቸው ዘንድ መጠየቃቸውን ግን አልተውም።



« እንደው በቃ እግዚአብሔር የሽግግር ፍትህ እና መልካም ነገር እንዲያደርግልን እና እነዚህ ሰዎች ፍትህ ቢገኝ ነው የምለው እኔ።»



ያለፈው ጦርነት በሀገሪቱ ላይ በአጠቃላይ ካስከለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ሳያገግግም የፕሪቶሪያውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለአደጋ የሚያጋልጡ ኹኔታዎች እየታዩ መሆናቸው ያለፈው ጦርነት ሰለባዎችን እያሳሰበ ነው።ያለፈው ይብቃን መልዕክታችን ይሰማልንም ይላሉ።



«አሁን ጦርነት ምንም ጥቅም አይኖረውም። ጉዳት ካልሆነ በቀር። ሰው ማለቅ ካልሆነ በቀር። የሀገር ሽማግሌዎች ፖለቲከኞች ስክን እንዲሉ ቢመክሩ ይሻላል እንጂ»



«ጦርነት ሀገር ያጠፋል ፣ ልጅ ያጠፋል። ንብረት ያጠፋል ፤ስለዚህ ምናልባት የኢትዮጵያ መንግስትም የትግራይን ጥያቄ መልሶ በሰላም በጠረጴዛ ዙሪያ ቢፈቱ መልካም ነው።»



የአውሮጳ ህብረት እና የህብረቱ አባል ሃገራት በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከምርጫ በፊት ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀምሩ ባለፈው እሁድ ባወጡት መግለጫ መጠየቃቸው ይታወሳል።



ታምራት ዲንሳ



እሸቴ በቀለ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የትግራይ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ዕለት ሲዘከር

የትግራይ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ዕለት ሲዘከር

Tamirat Dinssa Geleta ታምራት ዲንሳ ገለታ