የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት “ከ23 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም”?
Description
የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ “ዕዳ ከ23 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትላንት ማክሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል። ዐቢይ ይህን አሐዝ የጠቀሱት ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው።
በቀጥታ የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና የተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክለው የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ “ኢትዮጵያ ለፋይናንስ እና ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቷ ከፍተኛ ሥጋት የሆኑባት ከባድ እና ዘላቂነት የሌላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ዕዳ ፈተናዎች ተደቅነውባታል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ” እንደምትገኝ ያስታወሱት ዶክተር ደሳለኝ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የሚደረገውን ድርድር “ውስብስብ” ሲሉ ገልጸውታል።
ኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተበደረችበት ቦንድ ባለቤቶች ጋር ሲደረጉ የቆዩ ድርድሮች “መበላሸታቸው ተዘግቧል” ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል “በውጭ ምንዛሪ ገበያውም በባንክ እና በትይዩ ገበያው መካከል ያለው ክፍተት ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። “ከእነዚህ ተግዳሮቶች አኳያ መንግሥት ማኅበራዊ ወጪዎችን ሳይቀንስ ያሉብንን ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ለመክፈል እና የፋይናንስ ክፍተቱን ለመሸፈን እየሠራ ያለው ሥራ ምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በእርግጥም “ኢትዮጵያ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ” እንደምትገኝ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ ተስማምተዋል። “የእኛ ዕዳ ከ23 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በንጽጽር ሲታይ ያን ያክል አስደንጋጭ ባይሆንም የእኛ መጥፎ የሆነው ብድር የወሰድንበት መንገድ ነው። አብዛኛው ብድር የንግድ ብድር (commercial loan) ነው” በማለት አስረድተዋል።
“የንግድ ብድር ማለት በአጭር ጊዜ ብዙ መክፈል የሚጠይቅ የብድር ሥርዓት ስለሆነ የእኛ ጥያቄ የነበረው ያ የብድር ሁኔታ መሸጋሸግ አለበት ነው” በማለት የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከ23 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም” ያሉት የዕዳ መጠን የትኛውን ብድር እንደሆነ በግልጽ ሳያብራሩ ቀርተዋል። በዚህም ምክንያት ዐቢይ የጠቀሱት አሐዝ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የውጭ የዕዳ መጠን በትክክል የሚያሳይ አይደለም።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ስንት ነው?
ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በመስከረም ወር ይፋ ያደረጉት ትንተና የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አጠቃላይ ዕዳ እስከ ሰኔ 2016 መጨረሻ ብቻ 71.379 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አሳይቷል። የሀገሪቱ ዕዳ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ ያለው ምጣኔ 34.8 በመቶ ነው። ከዚህ ውስጥ 39.644 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው የሀገር ውስጥ ዕዳ ሲሆን ቀሪው 31.734 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ እንደሆነ የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ የኢትዮጵያ የዕዳ ዘላቂነት ትንተና ያሳያል።
የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዶክተር ሚኪያስ ሙሉጌታ “በእኔ ግምት ምን አልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 23 ቢሊዮን ዶላር ለማለት የፈለጉት ወይንም ደግሞ ለመጥቀስ የፈለጉት የፌድራል [መንግሥት] ቀጥታ የውጭ ዕዳ የሚመለከት ይሆናል” ሲሉ ይናገራሉ። ገንዘብ ሚኒስቴር በጥር 2017 ይፋ ባደረገው ሰነድ የመንግሥት የውጭ ዕዳ “28 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ” መድረሱን እንዳስታወቀ ያስታወሱት ዶክተር ሚኪያስ ዐቢይ በገለጹት አሐዝ “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወስደዋቸው የነበሩ ዕዳዎችን ያካተተ አይመስለኝም” በማለት አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ከፍተኛው ድርሻ የኦፊሴያል አበዳሪዎች ነው። በዓለም ባንክ ሥር የሚገኘው ዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር (IDA) 38 በመቶ፤ የፓሪስ ክለብ አባል ያልሆኑ ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች 33 በመቶ ድርሻ አላቸው።
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ የኢትዮጵያ የዕዳ ዘላቂነት ትንተና የፌድራል መንግሥት ዕዳ፣ ብሔራዊ ባንክ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎች ሁለት ሃገራት የተበደረውን ያካትታል። ከዚህ በተጨማሪ የፋይናንስ ተቋማት ያልሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በመንግሥት ዋስትና እንዲሁም ያለ መንግሥት ዋስትና የተበደሯቸውም በዕዳ ትንተናው ተካተዋል።
ድርጅቶቹ በመንግሥት ዋስትና ከሀገር ውስጥ የተበደሩትን 845.3 ቢሊዮን ብር መክፈል ሲያቅታቸው ገንዘብ ሚኒስቴር ቦንድ በማውጣት በአስር ዓመታት ዕዳቸውን ለመክፈል ተረክቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የመሳሰሉ ተቋማት ከውጭ የተበደሩት ገንዘብ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ውስጥ የሚካተት ነው።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ በመንግሥት ዋስትና የተሰጠው አሊያም ያልተሰጠው ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ-ቴሌኮም ያለባቸው የውጭ ዕዳ በመንግሥት ዋስትና የተሰጠው እንዳልሆነ የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የዕዳ ትንተና ያሳያል።
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድጅት ትንተና ኢትዮጵያ “በዕዳ ጫና ውስጥ የምትገኝ” ብቻ ሳትሆን ብድር የመክፈል አቅሟ “ዘላቂ” እንዳልሆነ አስጠንቅቋል። የዕዳ ክፍያ ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት ገደማ በቀሩት የጎርጎሮሳዊው 2025 ከወጪ ንግድ ያለው ድርሻ 5.6 በመቶ ነው። ይሁንና በሚቀጥለው ዓመት ይህ ወደ 36.6 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል የሁለቱ ተቋማት ሰነድ ትንበያ ያሳያል። የዕዳ ክፍያ በጎርጎሮሳዊው 2025 ከመንግሥት ገቢ ያለው ድርሻ 7.7 በመቶ ቢሆንም በሚቀጥለው ዓመት ወደ 37.7 በመቶ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
“ኢትዮጵያ አሁን ዕዳ ለመክፈል ምንም ዐይነት ችግር የለባትም”
የዕዳ ጫናውን ለመቀነስ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል ሲደረግ በቆየው ድርድር “ኢትዮጵያ የተበደረችው የንግድ ብድር ወደ ኮንሴሽናል ብድር መቀየር አለበት” የሚል አቋም መንግሥታቸው እንዳራመደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ “ምክንያት ከ4 እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ሽግሽግ ተደርጓል” ያሉት ዐቢይ “ይህ ታላቅ ድል ነው። የማሻሻያው ውጤት ነው። ኢትዮጵያ አሁን ዕዳ ለመክፈል ምንም ዐይነት ችግር የለባትም” ሲሉ ተደምጠዋል።
በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ሥር ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የሚደረገው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ከሥምምነት መደረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ባለፈው ሰኔ 2017 ነበር። መሥሪያ ቤቱ “ለዓመታት ሲደረግ ለነበረው ድርድር ስኬታማ መቋጫ” ያለው ሥምምነት “ለሀገሪቱ ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እፎይታ የሚሰጥ” እንደሆነ አስታውቋል። ተግባራዊ የሚሆነው “ከእያንዳንዱ የኮሚቴው አባላት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ ሥምምነቶች አማካኝነት” ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሣምንት “የቡድን 20 የብድር ሽግሽጋችን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አሕመድ በዋሽንግተን በተካሔደው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ ጉባኤ የኢትዮጵያ ልዑካን ስለነበራቸው ተሳትፎ ማብራሪያ ሲሰጡ “የመግባቢያ ሥምምነት ከአንድ ሀገር በስተቀር ከአብዛኞቹ ጋር ተፈርሟል” የዕዳ ሽግሽጉ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን አረጋግጠዋል።
ይሁንና የቦንድ ባለቤት ከሆኑ የግል አበዳሪዎች ጋር ሲደረግ የነበረው ድርድር የሚጠበቀውን ውጤት አላስገኘም። ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊት በተደረገው የመጨረሻ ድርድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ ተሳትፈዋል። የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ውስጥ ሞርገን ስታንሌይ ኢንቨስትመንት ማኔጅመንት፣ ፍራንክሊን ቴምፐልተን፣ ቪአር ካፒታል እና ፋራሎን የተባሉ ተቋማት እንደሚገኙበት ሬውተርስ ዘግቧል። ድርድሩ ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ኮሚቴው ጉዳዩን ወደ ሕግ መውሰድን ጨምሮ ሁሉንም እርምጃዎች እንደሚያጤን አስታውቋል።
የግል አበዳሪዎች ኮሚቴው አባላት “የኢትዮጵያ ኤክስፖርት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ስለሆነ፤ ኢኮኖሚያችሁ እያደገ ስለሆነ በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ መታቀፍ አንፈልግም” የሚል ክርክር በድርድሩ ማቅረባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን “አጋነው በማየት መክፈል ስለምትችሉ በነበረው መንገድ ቢቀጥል የሚል ሐሳብ” እንዳላቸው የገለጹት ዐቢይ አሁንም ድርድር እየተካሔደ መሆኑን ጠቁመው መንግሥታቸው ግን “ሁሉም ብድሮች በኮመንፍሬም ወርክ ማዕቀፍ ውስጥ ገብተው ሽግሽግ ይደረግላቸው” የሚል አቋም እንዳለው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተበደረችበት ቦንድ የመክፈያ ጊዜ ከማለፉ ባሻገር ሀገሪቱ አበዳሪዎቿን ዕኩል ለማስተናገድ ስትሞክር 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳትከፍል ቀርታለች። ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የሚደረገው ድርድር አንዳች ውጤት ላይ ሳይደርስ ከቀረ ዶክተር ሚኪያስ “በዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያ ተሳትፏችን ውስጥ በጣም ከባድ የሆነ ችግር ያመጣል” ሲሉ ተናግረዋል።
አርታዒ ሸዋዬ ለገሰ






















