የጀርመን መራሄ መንግሥት ለምን የሶርያ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አሳሰቡ?
Description
እንደ መራሄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ ከሆነ በጀርመን ተገን የጠየቁ ሶርያውያን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል።
« በሶርያ የእርስ እርሱ ጦርነት አብቅቷል፣ እናም ይህቺ ሀገር፤ ለመልሶ ግንባታ በተለይም የሶርያውያንን ሙሉ ጉልበት ትሻለች። »
ጀርመን መልሶ ግንባታውን እንደምታግዝ የገለፁት ሜርስ በርካታ ሶርያውንም በፍቃደኝነት «ወደ ሀገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ ይህንንም እናበረታታለን» ብለዋል። ይህ ብቻ አይደለም። በሜርስ እምነት ለሶርያውያን በአሁኑ ወቅት በጀርመን ጥገኝነት የሚያስጠይቅ ምንም ምክንያት የለም። ስለሆነም ጀርመን ተገን ጠያቂዎቹን «ወደ ሀገራቸው መመለስ መጀመር ትችላለች» ሲሉ ተደምጠዋል።
« በ ጀርመን 950,000 የሚጠጉ የሶሪያ ስደተኞች ይኖራሉ። ከእነሱም 920 ያህሉ በወንጀልም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች ጀርመንን ለቀው እንዲወጡ የተፈረደባቸው ናቸው። ሜርስ ሰኞ ዕለት ይህን ይበሉ እንጂ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሃን ቫደፑል ባለፈው ሐሙስ በጦርነት የተጎዳችው ሶሪያን በጎበኙበት ወቅት ከታዘቡት ከፍተኛ ውድመት አንጻር ብዙ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በአጭር ጊዜ በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። « እንደሚመስለኝ በአሁኑ ሰዓት ውስን አጋጣሚ ነው ያለው ። ምክንያቱም በሀገሪቱ ያለው መሠረተ ልማት በአብዛኛው ወድሟል።»
የመራሄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስን ንግግር ተከትሎ በሶርያ ስደተኞች ላይ ስላላቸው አቋም የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ወደ ጀርመን ለተሰደዱት ሶርያውያን ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። «በቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ህይወቴ ብዙ ጊዜ ቀውስ እና አደጋዎች ወደነበሩባቸው አካባቢዎች ተጉዤያለሁ። ሁኔታውን አውቀዋለሁ። አንድ በጦርነት የፈራረሰ ቦታ ላይ የቆመ ሰው ፤ ስላለው ስጋት ሲገልፅ እና እዚህ ውስጥ ሰው መኖር ይችላል ወይ? ብሎ ሲጠይቅ፤ ለዚህ ስጋት ጊዜ መስጠቱ ተገቢ ይመስለኛል።»
የመጀመርያዎቹ የሶርያ ስደተኞች በጀርመን
ዶይቸ ቬለ የሶርያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኤጀንሲ(UNHCR) የጀርመን ቢሮ ቃል አቀባይ ክሪስ ሜልዘርን አነጋግሯል። እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ውድመት ከተስቷል። እንዲያም ሆኖ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች ቱርክ እና ሊባኖስን ከመሳሰሉ የሶርያ ጎረቤቶች ወደ ሀገራቸው እስካሁን ተመልሰዋል። «ሀገሪቱ ከጥቅም ውጪ ሆናለች። እንደዛም ሆኖ ሰዎች እየተመለሱ ነው። እኛ እነዚህን ሰዎች እናግዛለን። ቢሆንም ሰዎች ወደሀገሪቱ እንዲመለሱ አናበረታታም። በርግጥ የሚመለሰው ሰው ፈርጠም ያለ ወጣት ወንድ ነው? ወይስ ቤተሰብ ያለው? እድሜ ፤የጤና ሁኔታ እና የመሳሰሉት ይወስናሉ። የሚመለሱበትም አካባቢ ይወስነዋል። እኛ ግን እንደ UNHCR በአጠቃላይ ወደ ሶርያ መመለስን አናበረታታም። በፍቃደኝነት የሚያደርግ ካለ ግን እገዛችንን እንለግሳለን። »
መራሄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ ለመልሶ ግንባታው በጀርመን ያሉት ሶሪያውያን ጉልበት አስፈላጊነትን ቢያሳስቡም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኤጀንሲው ቃል አቀባይ ክሪስ ሜልዘር ግን «እያንዳንዱ እጅ በአሁኑ ወቅት ለሶርያ ወሳኝ ቢሆንም ሀገሪቷ በአሁኑ ሰዓት ባዶ አይደለችም ይላሉ። ይልቁንስ የገንዘብ እና ሰብአዊ ርዳታ በአሁኑ ወቅት ወሳኝ እንደሆነ አሳስበዋል።
አርታኢ እሸቴ በቀለ























