የጥቅምት 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
Description
አርሰናልን የሚያስቆመው አልተገኘም ። ሊቨርፑል ከተደጋጋሚ የሽንፈት አባዜው የተላቀቀ ይመስላል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ነውጠኛ ደጋፊዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች እንዲሰማሩ አስገድዷል ። በዋናው ቡንደስሊጋ ባዬርን ሙይንሽን በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ አነጋጋሪ ውሳኔ አሳልፏል ።
በኒው ዮርክ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አልቀናቸውም
በኒው ዮርክ ማራቶን ኬንያውያን አትሌቶች ትናንት በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጁ ። የኒው ዮርክ ማራቶን አሸናፊዎች እያንዳንዳቸው 100 ሺህ ዶላር ተሸልመዋል ። ሁለተኛ የወጡት 60 ሺህ ሦስተኛ ደግሞ 40 ሺህ ዶላር ሰብስበዋል ። ለክብረወሰን ሰባሪ የተዘጋጀውን 50ሺ ዶላርም ኬንያውያኑ ወስደዋል ።
ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ኬኒያዊ የዘመናት ተቀናቃኙ ኤሊውድ ኪፕቾጌ በተሳተፉበት የትናንቱ ፉክክር ኬንያውያን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው ገብተዋል ። ኬኒያዊው አትሌት ቤንሰን ኮፕሮቶ በአንደኛነት ድል ለመቀዳጀት የፈጀበት ጊዜ(02፡08፡09) ነው ። ኬኒያዊው ለድል የበቃው ከአገሩ ልጅ አሌክሳንደር ሙቲሶ ጋር በአጀብ ሲሮጡ ቆይቶ በመጨረሻዎቹ ሴኮንዶች አፈትልኮ በመውጣት ነው ። ለጥቂት በሽርፍራፊ ሰከንዶች ድል ከእጁ ላፈተለከችው አሌክሳንደር እጅግ የሚያስቆጭ ሽንፈት ። በ2021 አሸናፊ የነበረው ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት አልበርት ኮሪር ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን ሳያጠናቅቅ ቀርቷል
የቀድሞው የዐለም ክብረወሰን ባለቤት ኤሊውድ ኪፕቾጌ (02፡14፡36) ሮጦ በመግባት 17ኛ ደረጃ አግኝቷል ። የ40 ዐመቱ አትሌት ከ25 ኪሎ ሜትር በኋላ ከዘመነኞቹ ባለድሎች ተገንጥሎ ቀርቷል ። የለንደን እና የቤርሊንን ጨምሮ በሰባት ታላላቅ ማራቶኖች ባለድል በመሆን ታሪክ ያስመዘገበው ኬኒያዊ የማራቶን ንጉሥ በኒው ዮርክ ማራቶን ውድድር ከሩጫው ተሰናብቷል ።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን ሳያጠናቅቅ ቀርቷል ። የኦሎምፒክን ጨምሮ የበርካታ የብር ሜዳሊያዎች ባለድሉ ትውልደ ሶማሊያ የኔዘርላንዱ ሯጭ አብዲ ናጌዬም ውድድሩን ሳያጠናቅቅ አቋርጧል ። አውሮጳውያን እና አሜሪካውያን ሯጮች ኬንያውያንን ተከትለው እስከ ዐሥረኛ ደረጃ በተደረደሩበት ፉክክር የኤርትራው ሯጭ ጸጋዬ ወልደሊባኖስ (02:10:36 ) በዘጠነኛ ደረጃ አጠናቅቋል ።
በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር የ35 ዐመቷ ኬኒያዊት አትሌት ሄለን ኦቢሪ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር (02፡19፡51) በአንደኛነት አሸንፋለች ። ክብረወሰኑ በአገሯ ልጅ ማርጋሬት ኦካዮ (02፡22፡31) እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2023 የተያዘ ነበር ። የውድድሩ የቀድሞ አሸናፊ ሼላ ቼፕኪሩይ (02:20:24 )ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ሌላኛዋ ኬኒያዊት ሻሮን ሎኬዲ (02:20:07 )በመሮጥ ሁለተኛ ወጥታለች ። ይጠበቁ ከነበሩ አትሌቶች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያ ኔዘርላንዳዊቷ አትሌት ሲፋን ሐሠን 6ተኛ ደረጃ ስታገኝ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጎይተቶም ገብረሥላሴ እንደ ቀነኒሳ ውድድሩን አቋርጣለች ።
አርሰናልን የሚያስቆመው አልተገኘም
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥን ሊቀያይር የሚችል ወሳኝ የእግር ኳስ ግጥሚያ ዛሬ ማታ በሰንደርላንድ እና ኤቨርተን ይከናወናል ። በሠንደርላንድ ስታዲየም ኦፍ ላይት ሜዳ በሚደረገው ግጥሚያ አስተናጋጁ ማሸነፍ ከቻለ ከሰባተኛ ደረጃ በቀጥታ ወደ ሁለተኛ መወርወሩ አይቀርም ። ሠንደርላንድ የሰበሰበው 17 ነጥብ ከቀዳሚዎቹ ቸልሲ እና ቶትንሀም እንዲሁም ከበታቹ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ተመሳሳይ ነው ። ልዩነታቸው የግብ ክፍያ ብቻ ነው ። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም፤ ስድስተኛው ቸልሲ እንዲሁም ስምንተኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው ማንቸስተር ዩናይትድ በአጠቃላይ ተመሳሳይ 17 ነጥብ አላቸው ።
ሠንደርላንድ የምሽቱን ተስተካካይ ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ በ20 ነጥብ ከማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ በልጦ ሁለተኛ ላይ ይሰፍራል ማለት ነው ። በዚህም መሠረት ማንቸስተር ሲቲ ወደ ሦስተኛ፤ ባለ18 ነጥቡ ሊቨርፑል ወደ አራተኛ፣ ተመሳሳይ 18 ነጥብ ያለው በርመስ ወደ አምስተኛ፣ ቶትንሀም ወደ ስድስተኛ እንዲሁም ቸልሲ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ይንሸራተታሉ ማለት ነው ። 11 ነጥብ ሰብስቦ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኤቨርተን ካሸነፈ ግን ብዙም የሚቀየር ነገር የለም ። የሚቀየረው ነገር ቢኖር በ14 ነጥቡ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ብሬንትፎርድን ቦታ ማስለቀቁ ነው ። ዌስትሀም ዩናይትድ 7 ነጥብ፣ ኖቲንግሀም ፎረስት 6 ነጥብ እንዲሁም ዎልቭስ 2 ነጥብ ብቻ ሰብስበው ከ18ኛ እስከ 20 የመጨረሻ ደረጃ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ተደርድረዋል ።
ኧርሊንግ ኦላንድ በ13 ግቦች ለብቻው እየገሰገሰ ነው
ትናንት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ ማንቸስተር ሲቲ በርመስን በጨዋታ በልጦት 3 ለ1 አሸንፏል ። የግብ ቀበኛው ኧርሊንግ ኦላንድ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ የግብ ብዛቱን ያለተቀናቃኝ 13 አድርሷል። በሁለተኛነት እና በሦስተኛነት የሚከተሉት የበርመሱ አንቱዋን ሴመንዮ እና የብራይተኑ ዳኒ ዌልቤክ ስድስት ግብ አላቸው ። ዌስትሀም ኒውካስል ዩናይትድን ትናንት 3 ለ1 አሸንፏል ። በደጋጋሚ ሽንፈት አስተናግዶ ግራ ተጋብቶ የነበረው ሊቨርፑል ከሽንፈት አባዜው የታደገውን የ2 ለ0 ድል አስቶን ቪላ ላይ ተቀዳጅቷል ። ግቦቹን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው አንድ ደቂቃ ላይ መሀመድ ሣላኅ እንዲሁም ከረፍት መልስ በ58ኛው ደቂቃ ራይን ግራቬንቤርሽ አስቆጥረዋል ። የጥቅምት 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሔርታ ቤርሊን በሜዳው ዖሎምፒያ ስታዲየም ድሬስደንን 2 ለ0 ባሸነፈበት ግጥሚያ ፖሊስ 30 ነውጠኛ ደጋፊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገለጠ ። በሁለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ የሚገኙት ቡድኖች ደጋፊዎች የረዥም ጊዜ ባላንጦች ናቸው ። ቅዳሜ እለት ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ፖሊስ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ ያላቸው የሁለቱ ደጋፊዎችን ለመለየት በሺህዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ አባላትን አሰማርቷል ። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ጠብ እና አነስተኛ ግርግር በተፈጠረበት ዖሎምፒያ ስታዲም ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ አባላት ተሰማርተው ነበር ።
ከሰአት በኋላ ቤርሊን ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሌላኛው ቡድን ዑኒዮን ቤርሊን በዋናው ቡንደስሊጋ ቆይው ወቅት ተቀናቃኙ ከነበረው ፍራይቡርግ ጋር ተጋጥሟል ። ያለምንም ግብ በተጠነናቀቀው ጨዋታ በደጋፊዎች ዘንድ አንዳችም ችግር አለመከሰቱ ተጠቅሷል ።
በቅዳሜው የዋና ከተማዪቱ ግጥሚያዎች ከቤርሊን ፖሊሶች በተጨማሪ ከዛክሰን፣ ከዛክሰን አንሀልት እና ከባደን ቩቴምበርግ ግዛቶች ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል ተሰማርቶ ነበር ። ጀርመን ውስጥ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡድኖች ነውጠኛ ደጋፊዎች የተነሳ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሁከት እና ብጥብጥ ብሎም ጉዳት ሲከሰት ይስተዋላል ።
በዋናው ቡንደስሊጋ ባዬርን ሌቨርኩሰንን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ0 ድል ያደረገው ባዬርን ሙይንሽን በ27 ነጥብ እየመራ ነው ። ሽቱትጋርትን 3 ለ1 ያሸነፈው ላይፕትሲሽ በ22 ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ20 ነጥብ ይከተላሉ ። በአውግስቡርግ ሜዳ የተጫወተው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ያሸነፈው በሴሩ ጊራሲ ብቸኛ ግብ እንደምንም 1 ለ0 ነው ።
በሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣርያ ውድድር አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ኬንያ፣ደቡብ ሱዳን እና ርዋንዳ ጋር ተደለደለች ። በምድብ «ለ» ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ብሩንዲ ተደልድለዋል ። ውድድሮቹ ከኅዳር 6 ጀምሮ ይከናወናሉ ተብሏል ። ለዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአራተኛ ቀን ልምምዱን ቅዳሜ ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አከናውኗል ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ለምን አነጋጋሪ ሆነ?
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአፍሪቃ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) አዳራሽ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ (ጥቅምት 20 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) አከናውኗል ። ስድስት አንቀፆች እንደተሻሻሉበት የተነገረለት የመተዳደሪያ ደንቡ አነጋጋሪ ሁኗል ። «አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ጊዜ የሥራ ዘመን በላይ መምራት አይችልም» የሚለው ሕግ ተሽሮም ለሦስተኛ ጊዜ መመረጥና መምራት እንደሚችል መጽደቁ ተሰምቷል ።
በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰ ጉባኤውን ከስፍራው ተከታትሏል ። ምስጋናው የመተዳደርያ ደንብ አንቀጾች እና የምርጫ ማስፈጸምያ ረቂቅ ለጉባኤው ቀርቦ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁ ታውቋል ። ለመሆኑ አነጋጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ























