ጀርመን ለኢትዮጵያ በምትሰጠው ድጋፍ ለጸጥታ ጉዳዮች ትኩረት እየሰጠች ነው?
Description
ኢትዮጵያ እና ጀርመን ባለፈው ሣምንት የሦስት ዓመታት “የትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት” መፈራረማቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ሥምምነቱ የተፈረመው የጀርመን የኢኮኖሚ እና ልማት ትብብር ፌድራል ሚኒስትር ሬም አላባሊ ራዶቫን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መግለጫ መሠረት ጀርመን ለኢትዮጵያ የ206 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ቃል ገብታለች። ከዚህ ውስጥ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የሚጣጣም 100 ሚሊዮን ዩሮ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ ተመድቧል። የበጀት ድጋፉ የመንግሥትን የወጪ እና የግብር ፖሊሲዎች (macro-fiscal stabilization) ለማረጋጋት እና ለመዋቅራዊ ማሻሻያዎች የሚውል ነው።
የተቀረው 106 ሚሊዮን ዩሮ በአንጻሩ “ጀርመን ቅድሚያ ለምትሰጣቸው የትብብር ዘርፎች” የተደለደለ ነው። ይህ “በፕሮጀክት እና በፕሮግራም ላይ የተመሠረተ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ትብብር” እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ ያሳያል።
“ሰላማዊ እና አካታች ማኅበረሰቦች መገንባት” ፣ “የግብርና ሽግግርን መደገፍ” እና “ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትን ማበረታታት” በድጋፍ ሥምምነቱ ሁለተኛ ክፍል ውስጥ የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው። ሥምምነቱ የተፈረመው ባለፈው ኅዳር የኢትዮጵያ እና የጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በርሊን ላይ ተገናኝተው ካደረጉት ድርድር በኋላ ነው።
በጎርጎሮሳዊው ከ2025 እስከ 2027 በሚዘልቀው የትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት ጀርመን ለኢትዮጵያ ልትሰጥ ቃል የገባችው የገንዘብ መጠን ከቀደመው ማዕቀፍ “በ30 ሚሊዮን ዩሮ ያነሰ” እንደሆነ መቀመጫቸውን በርሊን ላይ ያደረጉ አንድ የዓለም አቀፍ ልማት ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይህ አንድም ጀርመን ለኦፊሴያል የልማት ርዳታ የምትመድበውን ገንዘብ በመቀነሷ ምክንያት የተከሰተ ነው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የዓለም አቀፍ የልማት ባለሙያ ከገንዘብ መጠኑ መቀነስ ባሻገር ጀርመን በምትሰጠው ድጋፍ ትኩረት የምታደርግባቸው ዘርፎች ጭምር መቀየራቸውን አስረድተዋል። “ከዚህ በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ እና የጀርመን የሁለትዮሽ የድጋፍ ማዕቀፎች የማሻሻያ ሒደቱን መደገፍ ላይ ያተኮሩ ነበሩ” የሚሉት ባለሙያው “ጦርነት ቢከሰትም ‘የኢትዮጵያን ማሻሻያ ማጠናከር ይቻላል’ የሚል ተስፋ በጀርመን ዘንድ” እንደነበር አስረድተዋል።
“በድኅረ ጦርነት ለግጭት የማቆም ሥምምነቱ፣ ለሽግግር ፍትሕ፣ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ በማስፈታት አሰልጥኖ ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበት ሒደት ድጋፍ በቀደመው ማዕቀፍ” የተካተቱ መሆናቸውን የገለጹት የዓለም አቀፍ ልማት ባለሙያ “አሁን እየተመለከትን ያለንው ነገር ግን የበለጠ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ትኩረት መሰጠቱን ነው” በማለት ተናግረዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት አሰልጥኖ ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሒደት ለመደገፍ ጀርመን ከተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ-ግብር (UNDP) ጋር የተፈራረመችው የአምስት ሚሊዮን ዩሮ ሥምምነት ለዚህ ማሳያ ነው። ሥምምነቱን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ቻርጅ ደ አፌር ፈርዲናንድ ፎን ቬይኸ እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ግባይደ ናቸው። ባለፈው ሣምንት የተፈረመው ሥምምነት ጀርመን በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በኩል ለኢትዮጵያ የሰላም ድጋፍ መርሐ-ግብር (PSF) የመደበችውን ገንዘብ ወደ 19.5 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ አድርጎታል።
ዶክተር ፈርዲናንድ ፎን ቬይኸ ተማሪዎች መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲጀምሩ ብቻ ሳይሆን “የቀድሞ ታጣቂዎች ምሽጎቻቸን ጥለው ወደ ማኅበረሰቡ እና ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ እንዲችሉ ያቀልላቸዋል” ሲሉ የፕሮግራሙን ፋይዳ አስረድተዋል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ክፉኛ ቢሻክርም ጀርመን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር የተከተለችውን ስልት በሒደት የመለወጥ አዝማሚያ አሳይታለች። በጦርነቱ ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የተመደበ 90 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍ አግዶ ነበር። የኢትዮጵያ እና የጀርመን የልማት ትብብር በጦርነቱ ወቅት በሰብአዊ ርዳታ ላይ እንዲያተኩር ቢሆንም ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ መሻሻል አሳይቷል።
በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ በአውሮፓ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሻሻል ቀዳሚ እርምጃ የወሰዱት የጀርመን እና የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ናቸው።
ግጭት የማቆም ሥምምነቱን አተገባበር እና በግጭት የተጠቁ አካባቢዎችን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት ጀርመን በመደገፍ ላይ እንደምትገኝ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት በማስመልከት መሥሪያ ቤቱ ያወጣው መግለጫ እንደሚለው ጀርመን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሔዱ “ፖለቲካዊ ግጭቶችን ለማሸማገል” ትረዳለች።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚካሔዱ ግጭቶች እስካሁን መቋጫ አላገኙም። ኢትዮጵያ በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የበረታው ፍጥጫ ሌላ ጦርነት እንዳይቀሰቅስ አስግቷል።
ከግጭቶቹ ባሻገር ለሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ በምትዘጋጀው ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ፣ የነጻ እና ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን መገፋት የመሳሰሉ ጉዳዮች ለመንግሥት አስተዳደር ይደረጉ የነበሩ የልማት ድጋፎች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣታቸው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ልማት ባለሙያ “የጀርመን የውጭ ጉዳይ እና የልማት ፖሊሲ [አውጪዎች] ከትግራይ ጦርነትም በኋላ ቢሆን በኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የነበራቸው ተስፋ እየበነኑ መሆናቸውን የተገነዘቡ ይመስለኛል” ሲሉ ይናገራሉ።
“በኢትዮጵያ የተቋማት የአቅም ግንባታ በሲቪል ድርጅቶች ላይ በተወሰደው እርምጃ ምክንያት አስቸጋሪ እንደሆነ፤ የሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትኅ ሒደቶች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መውደቃቸውን እየተገነዘቡ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ወደብ እንድታገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የሚያደርገው ግፊት ከኤርትራ ጋር የፈጠረው ውጥረት የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረትን የመሳሰሉ ተቋማትን እንዳሰጋ ባለፈው ሣምንት ታይቷል።
ጀርመን የምትገኝበት የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ማንኛውንም ውጥረት ወይም አለመግባባት በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ” ጥሪ አቅርቧል። ጀርመንን የመሳሰሉ ሃገራት እና እንደ አውሮፓ ኅብረት ያሉ ተቋማት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሥጋታቸውን ከመግለጽ ባሻገር ሌላ ዙር ግጭት እንዳይቀሰቀስ ለመግታት የሚያስችል መሳሪያ በእጃቸው ያለ አይመስልም።
ጀርመንን የመሳሰሉ ሀገራት ባለሥልጣናትት በኢትዮጵያ “ሁኔታዎች አስቸጋሪ አንደሆኑ ያውቃሉ።” “በተለይ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከህወሓት ጋር ያለው ግንኙነት የተወሳሰበ እንደሆነ ይገነዘባሉ” የሚሉት የዓለም አቀፍ ልማት ባለሙያ “ነገር ግን እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ እንዴት እንደሚቋጭ መመልከት አይችሉም” የሚል እምነት አላቸው።
“ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን መቀጠል እና ለመዋዕለ-ንዋይ ዕድሎች መኖራቸውን ማየት አለባቸው። ነገር ግን ውስጣዊው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሻሻል ለማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው ብዬ አላምንም” ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በፈረንሳይ እና በጀርመን በተካሔዱ የኢንቨስትመንት ስብሰባዎች የአውሮፓ ባለወረቶችን ቀልብ ለመግዛት ጥረት አድርጋለች። የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታ ግን መረጋጋትን አጥብቀው የሚሹ ምዕራባውያን ኩባንያዎች እና ባለወረቶችን ከኢትዮጵያ የማሸሽ አቅም አለው።
አርታዒ ሸዋዬ ለገሰ























