ጀርመን ውስጥ በርካታ ሴቶች ከቤት ውጪ ደሕንነት አይሰማቸውም
Description
ጀርመን ውስጥ መጠይቅ የተደረገላቸው አብዛኛው ሴቶች ከቤት ውጪ ባሉ ቦታዎች ደኅንነት እንደማይሰማቸው በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት አመለከተ። ይህን ትናንት ይፋ ያደረገው የሕዝብ አስተያየት ጥናት የሚያደርገው ሲቬይ የተባለው ተቋም ለፉንኬ መገናኛ ብዙኃን ባጠናቀረው ጥናት ነው። ጥናቱ እንደሚጠቁመው 55 ከመቶ መጠይቅ የተደረገላቸው ሴቶች በመንገዶች፤ በሕዝብ ማመላለሻ ተቋማት እና በመናፈሻ ስፍራዎች ውስጥ ደኅንነት አይሰማቸውም። ሣንድራ ኪያላ በዶይቸ ቬለ ፖርቹጋል አፍሪቃ ክፍል ባልደረባ ናት ። እሷም ተመሳሳይ ስሜት ነው ያላት ።
«አዎ አዎ፤ በተለይ በባቡር ጣቢያዎች አካባቢ ብቻዬን መሄድ በጣም ይከብደኛል፣ ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ለሴቶች አደገኛ ናቸው ብዬ የምቆጥራቸው የአደንዛዥ ዕፅ ወይም የአልኮል ችግር ያለባቸው ወንዶች አሉ ። ለዚያም ነው ራሴን ለመከላከል ዐይን ላይ የሚረጭ የሚለበልብ ፈሳሽ የገዛሁት ። ያን ደግሞ በጣቢያው ውስጥ ባለፍኩ ቁጥር ይዤው ነው የምሄደው ።»
ቁጣ ያጫረው የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስ ንግግር
በጥናቱ ከተካተቱ ሰዎች መካከል ወንዶችን ጨምሮ ወደ 49 ከመቶ የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ውጪ በተጠቀሱት ቦታዎች በአጠቃላይ ደኅንነት አይሰማንም ማለታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት (dpa) ዘግቧል ። በምሽት የጭፈራ ቦታዎች እና በባቡር ጣቢያዎች ደግሞ ደሕንነቱ ይበልጥ የከፋ መሆኑ ተገልጧል ።
ጥናቱ ከመደረጉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስ ጀርመን ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ዜጎችን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ብርቱ ተቃውሞ አጭሮባቸዋል ። መራኄ መንግሥቱ ፍልሰተኞችን በተመለከተ ያለፈው መንግሥት ያሉትን ችግር ሲተቹ የራሳቸው መንግሥት ላይም ችግሩ መቀጠሉን ጠቅሰዋል ። «ከተማችን የያዘችውን መልክ በተመለከተ አሁንም ችግሮች አሉብን» ሲሉም ጀርመን ውስጥ ያሉ የውጭ ሃገራት ዝርያ ያላቸውን ሰዎች ከችግሩ ጋር አያያይዘዋል ። ላውራ ቬግነር የተባለች ጀርመናዊት ችግሩ ከሰዎች ማንነት ጋር እንደማይያያዝ ተናግራለች ።
«እርግጥ ነው ባሕሪያቸው ጥሩ ያልሆኑ ሰዎች አሉ፤ ያ ማለት ግን ከመጡበት ወይንም ከሌላ ነገር ጋር የሚያያዝ አይመስለኝም።»
ያን ክርስቲያን ራም የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የመራኄ መንግሥቱ ንግግርን በመተቸት የተለያዩ አገራት ዝርያ ያላቸው ሰዎች በተከማቸው መኖራቸውን መልካምነት እንዲህ አብራርተዋል ።
«ዝም ብለህ ዙሪያህን ተመልከት። ሰላም ስንባባል ራሱ እንዴት ደስ እንደሚል። እዚህ እኮ ሙሉ ለሙሉ ከኅብረተሰቡ ጋር የተዋሐዱ ግን ደግሞ በምሽት መውጣት የሚፈሩ ብዙ ፍልሰተኞች አሉን።»
የፖርቹጋል አፍሪቃ ክፍል ባልደረባዋ ሣንድራ ከነዚያ መካከል አንዷ ናት። ላለፉት አራት ዓመታት ግድም በጀርመን አገር ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋሕዳ ብትኖርም እሷ እንደምትለው አሁንም ድረስ ግን በተለይ በምሽት ብቻዋን ወደ ባቡር ጣቢያዎች እና ሌሎች ቦታዎች ለመውጣት ትሰጋለች።
የሴቶች ሥጋት በባቡር ጣቢያዎች እና የምሽት ጭፈራ ቤቶች
«እኔ በተለይ በምሽት ጭፈራ ቦታዎች ላይ ብዙ ልምድ የለኝም ። የእኔ ልምድ እነዚያ አደገኛ ያልኳቸው ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው በአብዛኛው በእነዚያ ባቡሮች እና ጣቢያዎቻቸው ላይ ነው ። ስለዚህ ባቡሮችን በተመለከተ የምር አደጋ እንደሚመስለኝ ፖሊስም ሆነ መንግስት ርምጃ ሊወስድ ይገባል ባይ ነኝ ።»
ለ5,000 ሰዎች ጥናቱን በበይነ መረብ ያከናወነው ሲቬይ የተባለው ተቋም እንደጠቀሰው ከሆነ፦ መጠይቁ የተደረገው ከባለፈው ሳምንት ጥቅምት 13 እስከ ሰኞ ጥቅምት 17 ድረስ ዕድሜያቸው ከ18 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች ነው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ






















