ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ሶማሊላንድ ጥልፍልፍ
Description
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ባለፈዉ ሳምንት ዕሁድ አዲስ አበባንን ብኝተዋል። የጉብኝቱ አላማና ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉት ዉይይት በይፋ አልተነገረም።ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ፕሬዝደንት አብዲረሕማን መሐመድ አብዱላሒ (ኢሮ)ም አዲስ አበባን ጎብኝተዋል።ማክሰኞ።የኢሮን ጉብኝት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሚስጥር እንዳይሉት-ሚስጥር አላደረጉትም።ይፋ እንዳይሉት አልዘገቡበትም።ከፎቶ ጋር በአራት መስመር የተዘገበዉም፣ በዝም-ዝምታ የታለፈዉም የሞቃዲሾና የሐርጌሳ መሪዎች ጉብኝት የተደረገዉ ሁለቱም መሪዎች ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ገዢዎች ጋር ከተወያዩ፣ የግብፅ የጦር መኮንኖች ሞቃዲሹ በገቡ በሳምንታት ዉስጥ ነዉ።የሞቃዲሾ መሪዎች ከፑንትላንድ መሪዎች ጋር የገጠሙት ዉዝግብ በተባባሰበት ወቅትም ነዉ።ግጥምጥሞሽ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
የአፍሪቃ ቀንድ ተለዋዋጭ የኃይል አሠላለፍ
አምና ይኼኔ የአዲስ አበባና የሐ,ርጌሳዎች ወዳጅነት ጠንክሮ፣ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ መሪዎች ጠብ ከርሮ፣ የሞቃዲሾ-ካይሮ-አሥመራ ወደጅነት ንሮ፣ የቱርክ ሸምግልና ሒደት ዉጤት በጉጉት ይጠበቅ ነበር።ዓመት አጭር ነዉ ረጅም።አጠረም የዓመቱ ዑደት ለአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ «ያቀርቶ ሌላ---መጥቶ» ያሰኝ ይዟል።
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ዘንድሮ ከሳምንት በፊት የግብፅ የጦር መኮንኖችን ወደ ሞቃዲሾ ጋብዘዉ፣ ባለፈዉ ሳምንት ዕሁድ አዲስ አበባን ጎብኝተዉ፣ በሳልስቱ ሐሙስ ናይሮቢ «ለቅሶ» ደረሱ።ለቢቢሲ እና ለአል አረቢያ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተከታታይ በሰጧቸዉ ቃለ መጠይቆችም ሶማሊያ ከኢትዮጵያም ከግብፅም ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት አረጋግጠዋል።
«ሶማሊያ ከሁለቱም ጋር ጥሩ ግንኙነት አላት።ግብፅ ኢትዮጵያን ለማወክ ፍላጎት እንዳላት ምንም አላየሁም።ኢትዮጵያም ሶማሊያ የሚሰፍረዉ የግብፅን ሠራዊት የመዉጋት ወይም የማወክ ፍላጎት እንዳላት ምንም አላየሁም።ጦርነት አንገሽግሾናል።ሌላ አ,ዲስ ጦርነት አንፈልግም።ሌሎች እኛ ግዛት እንዲዋጉ አንፈልግም።አይሆንም።»
ሐሰን ሼኽ የአሥመራ-ግብፅ-ሞቃዲሾ አክሲስን ረገብ፣ የአዲስ አበባ-ናይሮቢ-አቡዳቢን ጉድኝት ጠበቅ ያደረጉት ወይም ያደረጉ የመሰሉት በአንካራ ሥምምነት፣ የአዲስ አበባና የሐርጌሳዎች ስምምነት መኖሩም-መሞቱም ባለመታወቁ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የጁባላንድ ጥልፍልፍና የኢትዮጵያ ሚና
ባለፈዉ ሳምንት ዕሁድ አዲስ አበባ፣ ሐሙስ ናይሮቢ ያጓዛቸዉ ዋናዉ ምክንያት ግን ከወደ ኪስማዩ የገጠማቸዉ ከባድ ፈተና ነዉ።በፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ መንግሥት፣ በፑንትላንድና በጁባ ላንድ ግዛቶች መሪዎች መካከል ያለዉ ልዩነት እንደተካረረ ነዉ።በተለይ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ከጁባላንድ ገዢ አሕመድ መዶቤ ጋር የገጠሙት ዉዝግብ አስጊ ደረጃ ደርሷል።
ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድና አሕመድ መዶቤ፣ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማሰር የእስር ዋራንት እስከ መቁረጥ ደርሰዋል።የሁለቱ ወገኖች ታጣቂዎች ተጋጭተዉም ነበር።የጁባላንድ ገዢ አህመድ መዶቤ የኬንያ ጥብቅ ወዳጅ ናቸዉ።ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ከኢትዮጵያ ጋርም ጥሩ ግንኙነት አላቸዉ።በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ከጁባላንድ ጋር ትዋሰናለች።የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አብዲ መሐመድ አብዲ ቡባል እንደሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር የጁባላንድን ሁለት አዉሮፕላን ማረፊያዎች ይቆጣጠራልም።
«ጁባላንድ እንደምታዉቀዉ ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር ያላትና የኢትዮጵያ ወታደርም በለድሐዌና ዶሎ ኤርፖርቶችን የሚቆጣጠርበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ።ሐሰን ሼኽ ከጁባላንድ ፕሬዝደንት ጋር የገቡት ቅራኔ (አንዱ ሌላዉ እንዲታሰር) እስከ እስራት ደብዳቤ (ዋራንት) ደርሰዋል።ወታደራዊ ግጭቶችም ነበሩ---»
የሐሰን ሼኽ ሥልት-ሲሆን በስምምነት ካልሆነ በሴራ
የጁባላንድን እንቢተኝነትን ለማለዘብ በአሕመድ መዶቤ ላይ ተፅኖ የሚያሳድሩት የአቡዳቢና የናይሮቢ መሪዎች እንዲያማልዷቸዉ ሐሰን ሼኽ ያደረጉት ሙከራ ለፍሬ አልበቃም።ሐሰን ሼክ ከሁለት ሳምንት በፊት የጁባላንድ ርዕሠ-ከተማ ኪስማዩን ድንገት መጎብኘታቸዉም ዉጤት አላመጣም።ሐሰን ሼኽ የጁባላንድ መሪን ከቻሉ ለማስገበር ካልሆነም ከፖለቲካዉ ጨዋታ ለማስፈንጠር እንደ ሶስተኛ አማራጭ የቀየሱት አዲስ የጁባላንድ አስተዳደር መመሥረት ነዉ።
ከመዶቤ ካፈነገጡ ወታደሮችና ከግብፆች ጋር ሆነዉ ሞከሩት። ነገር ግን የስምምነቱ ይሁን የሴራዉ ሥልት ገቢር እንዲሆን፣ ዶክተር አብዲ እንደሚሉት፣ሐሰን ሼኽ ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ትብብርና የኬንያዎች ይሁንታ ያስፈልጋቸዋል።
«(ሐሰን ሼኽ) አዲስ የጁባላንድ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ ጀምሮ ነበር።ግብጾችም ነበሩበት።እና የተጠበቀዉና ጁባላንድ አዲስ ክልላዊ መንግሥት ለመመሥረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እርዳታ ምግኘት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።»
የምርጫ ዋዜማ የሐሰን ሼኽ ሩጫ
ሶማሊያ ዉስጥ ዘንድሮ ምርጫ ይደረጋል።ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ከቀድሞዉ ሐይለኛ የጦር አበጋዝ አሕመድ መዶቤ ጋር የገጠሙት አተካራ ግን ዘመነ-ሥልጣናቸዉን እንዳያሳጥረዉ የአዲስ አበባ መሪዎችን ድጋፍ አጥብቀዉ ይሻሉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሐሰን ሼኽ ጥያቄን መቀበል-አለመቀበላቸ በግልፅ አይታወቅም።ይሁንና የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት ሐሰን ሼኽ ዐብይን ለማሳመን አዲስ አበባ የገቡት ባዶ እጃቸዉን አልነበረም።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ዐብይ ሐሰን ሼኽን ከደገፉ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የመንግሥትነት እዉቅና ከመስጠት በመለስ የሶማሊላንድ ወደብን ለመኮናተር ያደረገችዉን ወይም ወደፊት የምታደርገዉን ሌላ ሥምምነት ሞቃዲሾ አትቃወምም።ሁለቱ መንግሥታት ግን ይሕን አላረጋገጡም።
ባለፈዉ ሳምንት ዕሁድ የተደረገዉን ጉብኝትም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአንድ የጋራ ፎቶ ፣በሁለት መስመር፣ «ተወያዩ» በምትል ድፍን ቃል ነዉ የዘጉት።ሁለቱ መንግሥታት « ሾላ በድፍኑ» ያስመሰሉት የሐሰን ሼኽ ጉብኝትና ዉይይት ሲያነጋግር፣ ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ግዛት ፕሬዝደንት አብዲረሕማን መሐመድ አብዲላሒ (ኢሮ) አዲስ አበባ ገቡ።ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ።
ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ ጦር ሠፈር ትፈቅዳለች ግን---
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና የሚቆጣጠሯቸዉ መገናኛ ዘዴዎች ሥለ ኢሮ ጉብኝት የያዙት አቋም «ግመል ሠርቆ አጎብንሶ መጓዝ» የሚሉት አይነት ነዉ።ከኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እስከ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ያሉ ሹማምንት ከሶማሊላንድ መልዕክተኞች ጋር የተነሷቸዉ ፎቶዎች የሶማሊላንድና የሌሎች የዉጪ መገናኛ ዘዴዎች ዘገቦችን ሲያደምቁ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና መገናኛ ዘዴዎቻቸዉ የሆነዉ-እንዳልሆነ ዝም ብለዋል።ፀጥ።
አምና የተመረጡት የፕሬዝደንት አብዲረሕማን መሐመድ አብዲ ኢሮ መንግሥት የኢትዮጵያና የሶማሊላንድን የመግባቢያ ሥምምነት ሙሉ በሙሉ አይቀበለዉም።አዲሶቹ የሐርጌይሳ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ኢትዮጵያ የጦር ሠፈር ከፈለገች ግን የሥምምነቱ ይዘት ተቀይሮ መኮናተር ትችላለች።ዶክተር አብዲ መሐመድ አብዲ እንደሚሉት ለጦር ሰፈርም ቢሆን ሐርጌሳዎች የደረደ,ሩት መሥፈርት ብዙ ነዉ።
«ኢትዮጵያ የምትፈልገዉን ሚሊታሪ ቤዝ ለመስጠት ፈቃኛ ነን።ግን ሞዳሊቲዉ ልክ አሜሪካ፣ ቻይናዎችና ሌሎቹ ጅቡቲ ላይ እንዳላቸዉ አንድና ሁለት ኪሎ ሜትር ዓይነት መስጠት እንችላለን።ለዚሕም በዶላር ኪራይ መከፈል አለበት--ከኢትዮጵያ ድንበር እንደፈለጋችሁ ወጥታችሁ መግባት እማትችሉበት ሁኔታ---»
የሶማሊላንድ የነፃ ሐገርነት ጥያቄ የገጠመዉ ፈተና
የመግባቢያ ሥምምነቱን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር የተፈራረሙት የቀድሞዉ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ አብዲ ቢሒም ሥምምነቱ የሶማሊላንድን የነፃ ሐገርነት ጉዳይ የሚያጣቅስ በመሆኑ በርካታ ተቃዉሞ እንደገጠመዉ አስታዉቀዋል።
ቢሒ ባለፈዉ ታሕሳስ እንዳሉት የአፍሪቃ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የዓረብ ሊግ፣ የሙስሊም ሐገራት ድርጅት ሁሉም በመቃወማቸዉ፣ የሶማሊላንድ የነፃ ሐገርነት ምኞት፣ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብን የመኮናተር ጉጉትም ባጭር ጊዜ ዉስጥ የሚሳካ አ,ይመስልም።
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅም የሶማሊላንድ የነፃ ሐገርነት ጥያቄ በኢትዮጵያ ዓይደለም በዩናይትድ ስቴትስ ቢደገፍ እንኳ ተቀባይነት የለዉም።የሶማሊያ አንድነት የማይደፈር ቅዱስ ነዉ-እንደ ሐሰን ሼኽ።
«ይሕ የአፍሪቃ ህብረት ደንብን መጣስ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደንብን መጣስ ነዉ።ሶማሊላንድ የሶማሊያ አካል ናት።እርግጥ ነዉ ቅሬታዎች አሏቸዉ።ይሁንና ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያስተሳስሩን ብዙ ጉዳዮች አሉ።የሶማሊያ አንድነት የማይነካ ቅዱስ ነዉ።»
ኢሮ አዲስ አበባን ለመጎብኘት ለምን ዘገዩ
የቀድሞዉ አንጋፋ የሶማሊያ ዲፕሎማት አብዲረሕማን መሐመድ አብዲላሒ ኢሮ እንደ ብዙ ቀዳሚዎቻቸዉ ሁሉ ሥልጣን እንደያዙ አዲስ አበባን ለመጎብኘት ፈልገዉ ነበር።ከኢትዮጵያ ፈጣን ግብዣ አላገኙም።ከዚሕም በተጨማሪ የመረጣቸዉን ሕዝብ ፍላጎት፣የኢትዮ-ሶማሊያን ጠብ-ወዳጅነት፣ የጅቡቲ፣ የኬንያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን አቋም እያወጡ ሲያወርዱ እስካለፈዉ ሳምንት ቆዩ።
ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባን የጎበኙት በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ ነዉ።ኢሮና የመሯቸዉ ባለሥልጣናት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድና ከሌሎች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ያደጉትን ዉይይት ዝርዝር ይዘት አልተነገረም።
የኢሮ ጉብኝት እዉን «የተሰካ ነበር?»
የኦማሊላንድ ባለሥልጣናት«የተሳካ ባሉት ጉብኝት» ሁለቱ ወገኖች በአፍሪቃ ቀንድ ሠላም፣መረጋጋትና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን ለረጅም ጊዜ የያዙትን አቋም ለማጠናከር ተስማምተዋል።የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አብዲ መሐመድ አብዲ እንደሚሉት ግን የጉብኝቱ መሠረታዊ ምክንያት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግና ሥምምነት መሠረት የሶማሊላንድ ወደብን እንድትኮናተር ከፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ የተገኘዉ የይሁንታ ፍንጭ ነዉ።
«አሁን ሐሰን ሼኽ የኢትዮጵያ እገዛ ሥላስፈለጋቸዉ፣ በቀድሞዉ ሥምምነት ላይ የተወሰነ ለዉጦች ተደርጎ፣ እዉቅናዉ ይቅር እኛ ደግሞ ዓለም አቀፍ ሥምምነት ከኛ ጋር ተደርጎ ሶማሊላንድ ደግሞ እንደ ኦፕሬሽን እንድታደርግ እንስማማለን የሚል ሲገኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ነዉ (ኢሮን) ወደ አዲስ አበባ የጋባዘዉ።»
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሚና
የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት አዲስ አበባን የጎበኙት ከአቡዳቢ ሐርጌሳ በተመለሱ ማግሥት ነዉ።የኢሮ ጉብኝት ባለፈዉ ሐሙስ ሲጠናቀቅ ደግሞ የበርበራ ወደብን የሚገነባዉ፣ DP ወርልድ የተባለዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያ መርከቦች፣ ከርበራ ወደብ ጀበል ዓሊ ወደተባለዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ እና በተቃራኒዉ መጓዝ መጀመራቸዉን አስታዉቋል።
በኢትዮጵያ-ሶማሊያና ሶማሊላንድ መሪዎች ጉብኝት፣ ዉይይት፣ የፖለቲካ ጥልፍልፉ የአቡዳቢና የካይሮ ገዢዎች በቀጥታም በተዘዋዋሪም ጫና ማድረጋቸዉ የተሠወረ አይደለም።ይሁንና የሶማሊላንድ ዲፕሎማቶች በግል እንዳሉት ኢሮ የመሩት የልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ በኩል የቀረበለትን የሶማሊያ ፕሬዝደንትን ሥልት አልተቀበለዉም።ጉብኝቱም ባጭሩ ተጠናቅቋል።ምናልባት እስከሚቀጥለዉ ጊዜ።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ