የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስር የውጪ ምንዛሪ ጨረታዎች ምን አሳኩ?
Description
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትላንት ማክሰኞ ባካሔደው የውጪ ምንዛሪ ጨረታ ለ31 ባንኮች 150 ሚሊዮን ዶላር አከፋፍሏል። በአስረኛው ዙር ጨረታ አንድ የአሜሪካ ዶላር በአማካኝ በ148 ብር ከ10 ሣንቲም እንደተሸጠ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የውጪ ምንዛሪ “እየጨመረ በመምጣቱ” የዋጋ እና የውጪ ክፍያ መረጋጋት ዓላማዎቹን ለመደገፍ ከፊሉን ለባንኮች እንደመደበ አስቀድሞ ገልጾ ነበር።
የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ጨረታው በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረውን የትይዩ ገበያ የምንዛሪ ተመን ለመቆጣጠር የተደረገ ጥረት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም ከታዩት አኳያ የተሳተፉ ባንኮች ቁጥር 31 መድረሱን ያስታወሱት ዶክተር አብዱልመናን “በመደበኛው ገበያ የውጪ ምንዛሪ እጥረት እንዳለ ያመለክታል” ሲሉ አስረድተዋል።
ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 28 ቀን 2017 ባካሔደው ጨረታ 28 ባንኮች ሲሳተፉ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ138 ብር ከ25 ሳንቲም ተመንዝሯል። በሁለቱ ጨረታዎች የታየው የዶላር የምንዛሪ ተመን ልዩነት “በጣም ከፍተኛ ጭማሪ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ይኼ ምንአልባት ይፋዊ ተመኑ ላይ በቀጥታ ላይንጸባረቅ ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ባንክ በዘጠነኛው ጨረታ ለባንኮች 150 ሚሊዮን ዶላር ያከፋፈለው የትይዩ ገበያው የምንዛሪ ተመን ከፍተኛ ዕድገት ማሳየት ሲጀምር ነበር። በወቅቱ ማዕከላዊው “ባንክ ሕገ-ወጥ እና የጥቁር ገበያ ተዋንያን ያላቸው ላይ እርምጃ” በመውሰዱ የውጪ ምንዛሪ ገበያው የመረጋጋት አዝማሚያ አሳይቷል። ዶክተር አብዱልመናን “የውጪ ምንዛሪ ተመኑ በትይዩ ገበያ በከፍተኛ መጠን ሲጨምር መንግሥት እንደዚሁ እሳት የማጥፋት እርምጃ ላይ ነው ያተኮረው” ሲሉ ይተቻሉ።
አስረኛው ዙር ጨረታ የተካሔደው ዶክተር እዮብ ተካልኝ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከሆኑ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ጨረታ ማከፋፈል የጀመረው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ተግባራዊ ከተደረገው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ በኋላ ነው። ብሔራዊ ባንክ የገበያውን “የውጪ ምንዛሪ ፍላጎት በማገናዘብ” በሁለት ሣምንት አንድ ጊዜ መሰል ጨረታ እንደሚያካሒድ ያስታወቀው ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ገዥ እያሉ በመጋቢት 2017 ነበር።
ባንኩ “ቢያንስ” እስከ 2017 መጨረሻ ድረስ “መደበኛ” እና “ተከታታይ” የዶላር ጨረታዎች ለማካሔድ ማቀዱን የቀድሞው ገዥ በወቅቱ ገልጸዋል። መሰል ጨረታዎች ብሔራዊ ባንክ በሁለት ሣምንት አንድ ጊዜ ለማካሔድ የያዘውን ውጥን ሳይተወው እንዳልቀረ የሚያምኑት ዶክተር አብዱልመናን “ምን አልባትም ከመጀመሪያው ጀምሮ መደበኛም አልነበረም” የሚል ዕምነት አላቸው።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ በኋላ የመጀመሪያው የብሔራዊ ባንክ “ልዩ የውጪ ምንዛሪ ጨረታ” የተካሔደው ነሐሴ 2016 ነበር። የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ በተደረገ በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ በተካሔደው ጨረታ አንድ ዶላር በአማካኝ በ107 ብር ከዘጠኝ ሣንቲም ተመንዝሯል። በጨረታው 27 ባንኮች መሳተፋቸውን ያስታወቀው ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ያከፋፈለው የዶላር መጠን ምን ያክል እንደሆነ ሳይገልጽ ቀርቷል።
ብሔራዊ ባንክ መስከረም 23 ቀን 2017 ባካሔደው ሌላ ጨረታ 175 ሚሊዮን ዶላር የሸጠ ቢሆንም ገንዘቡ ከነዳጅ ግዥ ጋር ለተያያዙ ክፍያዎች ብቻ የተመደበ ነበር። በወቅቱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት ማሞ ምህረቱ በባንኮች በሚከወነው እና በትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያዎች መካከል ያለው ልዩነት ወደ አምስት በመቶ መውረዱን ጠቅሰው የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ “እጅግ አዎንታዊ ጅማሮ” እንዳሳየ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚያ በኋላ ባካሔዳቸው ዘጠኝ ጨረታዎች በአጠቃላይ 690 ሚሊዮን ዶላር ለባንኮች አከፋፍሏል። ባንኩ ይፋ ባደረጋቸው መረጃዎች መሠረት በአንድ ጊዜ ለጨረታ የቀረበው ዝቅተኛ የገንዘብ መመጠን 50 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ከፍተኛው 150 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ጨረታዎቹ በትይዩ ገበያ ተዋንያን ላይ ከተወሰዱ እርምጃዎች ጋር በተደማመሩባቸው ወቅቶች በአንጻራዊነት የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱን ማረጋጋት ችለዋል።
ይሁንና “የማዕከላዊ ባንኩን የተረጋጋ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ግብ ለማሳካት” የቻሉ አልሆኑም። “ጨረታዎቹ ያመጡት ለውጥ የለም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ለዚህም በመደበኛውም ይሁን የትይዩ ገበያው የውጪ ምንዛሪ ተመን እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል። “በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት አሁን 15% አካባቢ ነው። ይኸ ደግሞ ለረዥም ጊዜ የነበረ ልዩነት ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ምንም ማሳካት አልተቻለም” የሚል አቋም አላቸው።
“ምክንያቱ [ጨረታዎቹ] ወጥ በሆነ መልኩ አለመቀጠላቸው ሊሆን ይችላል። ያንን ለማድረግ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ሊኖረው ይገባል” ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጪ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት የተሸጋገረችው የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማረቅ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ በማሰብ ነው። ሽግግሩ የብር የመግዛት አቅምን በማዳከም የዜጎችን ደመወዝ እና ቁጠባ ቢሸረሽርም የብሔራዊ ባንክን የውጪ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ አግዟል።
በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት ባለፈው ዓመት የውጪ ምንዛሪ ፍሰት ወደ 32 ቢሊዮን ዶላር ያደገ ሲሆን ከወጪ ንግድ ሸቀጦች 8.3 ቢሊዮን ዶላር፣ ከአገልግሎቶች የወጪ ንግድ 8.5 ቢሊዮን ዶላር፤ ከግል ሐዋላ 7.1 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቶ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት በ2018 ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሪ ወደ 9.4 ቢሊዮን ዶላር የማሳደግ ዕቅድ አለው።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ በ2018 ከወጪ ንግድ “በአንደኛ ሩብ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ 2.48 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች” ሲሉ ትላንት ማክሰኞ ተናግረዋል። የተገኘው ገቢ ከ2017 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር “የ980 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብልጫ አለው” ያሉት ዶክተር ካሳሁን “ይኼ በሀገር ደረጃ እያደረግን ያለንው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤት ማሳየት መጀመሩን ብቻ ሳይሆን የአንድ ጊዜ ብቻ ውጤት አለመሆኑን” እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስረኛ ጨረታ ያካሔደው በትይዩ ገበያ የብር የምንዛሪ ተመን ዶላር እና ፓውንድን ከመሳሰሉ መገበያያ ገንዘቦች አኳያ በከፍተኛ መጠን በተዳከመበት ወቅት ነው። አንድ ዶላር ሰሞኑን ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም በትይዩ ገበያ እስከ 180 ብር ሲሸጥ ቆይቷል። በትይዩ ገበያው ፓውንድ እስከ 217 ብር፤ ዩሮ እስከ 187 ብር ገደማ እየተመነዘረ እንደነበር ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጪ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን በሐምሌ 2016 ሲወስን ለአጭር ጊዜ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ቢቃለልም በባንኮች እና በትይዩ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት መስፋት የጀመረው በጥቂት ወራት ልዩነት ውስጥ ነበር።
የመደበኛው ግብይት በዋናነት መንግሥት በሚቆጣጠረው ንግድ ባንክ ተመን እንደሚመራ ዶክተር አብዱልመናን መሐመድን የመሳሰሉ ባለሙያዎች ያምናሉ። ንግድ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር 141 ብር ከ60 ሣንቲም ገደማ ገዝቶ 144 ብር ከ43 ሣንቲም ገደማ የሚሸጥ ቢሆንም በገንዘብ መላኪያ መተግበሪያዎች በኩል ለሚፈጸም ዝውውር አንድ ዶላር “ከጉርሻ ጋር” በ154 ብር ከ43 ሳንቲም ገደማ ብር ይመነዘራል።” የምንዛሪ ተመናቸው ከንግድ ባንክ ጥቂት ልዩነት ቢኖረውም አዋሽ ባንክ እና አቢሲኒያ ባንክ ዘጠኝ በመቶ ጉርሻ ይሰጣሉ።
ዶክተር አብዱልመናን የሀገሪቱ የምትከተለው የገንዘብ ፖሊሲ እና የወቅቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለትይዩው ገበያ መነቃቃት የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ 18 በመቶ የነበረው የባንኮች የብድር ምጣኔ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማድረጉ ለትይዩ ገበያው መፋፋት ሌላ ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
“ይኸ ማለት ብዙ ሰዎች ብድር ያገኛሉ። ብድር የማግኘት ዕድል ሲኖር ኢምፖርት የማድረግ ፍላጎትም ይኖራል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን በባንኮች የፈለጉትን የውጪ ምንዛሪ “በበቂ ሁኔታ” ማግኘት ያልቻሉ አስመጪዎች ወደ ትይዩ ገበያው ማማተራቸው እንደማይቀር አስረድተዋል።
ሌላው ለትይዩ ገበያ ተመን ዕድገት ገፊ ምክንያት “የካፒታል አካውንት ዝግ መሆን ነው።” ኢትዮጵያ የገጠማት ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ጨምሮ “ሰዎች በተለያየ ምክንያት ንብረታቸውን ከሀገር ለማውጣት ይፈልጉ ይሆናል።” ይሁንና “በመደበኛው ገበያ ማውጣት አይችሉም።” ይህ ከሕግ እና ሥርዓት ውጪ የሚከወነውን የምንዛሪ ገበያ እንደ አማራጭ እንዲጠቀሙ ያስገድዳል።
መንግሥት ትይዩ ገበያውን ለመቆጣጠር ባለፉት ወራት ተከታታይ እርምጃዎች ለመውሰድ ሙከራ አድርጓል። እርምጃዎቹ በተወሰዱባቸው ወቅቶች በትይዩ ገበያ የምንዛሪ ተመን ለአጭር ጊዜ ቢረጋጋም ተመልሶ ሲያንሠራራ በተደጋጋሚ ታይቷል። በዘመቻ መልክ የሚወሰዱት እርምጃዎች “የተወሰነ ድንጋጤ” ፈጥረው የጎንዮሽ ገበያው በተወሰነ መልኩ ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ ግን ሊጠፋ እንደማይችል ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል።
ዶክተር አብዱልመናን ሁነኛው መፍትሔ በባንኮች በሚከወነው ይፋዊ ገበያ በቂ የውጪ ምንዛሪ ማቅረብ ብቻ እንደሚሆን ይሞግታሉ። ለዚህ ደግሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የተሻለ የወጪ ንግድ ሸቀጦች አምራች መሆን ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ የምትሸጣቸው ቡናን መሰል ሸቀጦች የወጪ ንግድ የገባበትን ቅርቃር እና ለውጪ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍትሔ ማበጀት አይችሉም።
የትይዩው ገበያ ከፍተኛ የምንዛሪ ተመን የግል ሐዋላን ከመደበኛው ሥርዓት የበለጠ የሚያሸሽ ይሆናል። በመደበኛ እና በትይዩ ገበያዎች መካከል የሚፈጠር ሰፊ ልዩነት ሀገሪቱ ለምትፈልገው ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ እንቅፋት የሚሆን ነው። ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ፣ የንብረት ባለቤትነት አስተማማኝ አለመሆን እና የመንግሥት አገልግሎት ያሉበት ችግሮች “ተደራርበው ለውጪ ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ የሚመቹ አይደሉም።”
በባንኮች እና በትይዩ ገበያው መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን ልዩነት የሚያስከትለው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለኢንቨስትመንት እንቅፋት እንደሚሆን ከጥቂት ሣምንታት በፊት የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከባቢ መግለጫ ይጠቁማል። ለአሜሪካውያን ኩባንያዎች እና ባለወረቶች የተሰናዳው መግለጫ በመላ ኢትዮጵያ በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች፣ ሥጋት የፈጠረው የትግራይ የፖለቲካ ውጥረት፣ ደካማ የንብረት ባለቤትነት መብት የመሳሰሉ ጉዳዮች ለባለወረቶች ችግር እንደሚሆኑ ያሳየ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ በውጪ ኩባንያዎች ላይ የሚጣል ብዙ እና ጥያቄ የሚያስነሳ ግብር፣ ደካማ መሠረተ-ልማት እና ሎጂስቲክስ እንዲሁም ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚያደላ ሥርዓት ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጪ ባለወረቶች ገበያውን አመቺ እንደማያደርገው ሰነዱ አትቷል።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ