የኮትዲቫር ምርጫ እና የዴሞክራሲ ጥያቄ
Description
30 ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ኮትዲቫር በዛሬው ዕለት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አካሂዳለች ። ለአራተኛ ጊዜ የተወዳደሩት ፕሬዚደንት አላሳን ዋታራ ያሸንፋሉ የሚል ቅድመ ግምት ተሰጥቷል ።
በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ዲቫር ዛሬ (ቅዳሜ፤ ጥቅምት 15 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) አገር አቀፍ ምርጫ ተጀምሯል ። የ83 ዓመቱ አዛውንት የአገሪቱ ፕሬዚደንት አላሳን ዋታራን ጨምሮ አምስት ተፎካካሪዎች ቀጣይ የአገሪቱ ፕሬዚደንት ለመሆን የምርጫ ዘመቻቸውን ባለፈው ሐሙስ አጠናቅቀዋል ። የዛሬ ዐሥራ አምስት ዓመት ግድም፤ እንደ ጎርጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 እና 2011 የድኅረ ምርጫ ቀውስ ውስጥ ገብታ ለነበረችው ኮት ዲቫር ይህ ምርጫ እጅግ ወሳኝ ነው ። በያኔው ድኅረ ምርጫ ብጥብጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ።
የ83 ዓመቱ አዛውንት የአገሪቱ ፕሬዚደንት አላሳን ዋታራም ለ4ኛ ዙር ተሳትፈዋል
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የቀድሞ ኢኮኖሚስት አላሳን ዋታራ በዛሬው ምርጫ ያሸንፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ። በእርሳቸው አመራር፣ ኮት ዲቫር በዋና ዋና የመሠረተ ልማት መዋእለ ንዋያት የተደገፈች ከአፍሪቃ እጅግ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገቡ ከሚባሉት አንዷ ሆናለች ። አላሳን ዋታራ ኮት ዲቫር ገብታበት ከነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በማውጣትም በአንዳንዶች ይወደሳሉ ።
ስለ ሰውዬው የዓለም ባንክ ያወጣው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል ። ኮት ዲቫር፦ «ከሰሐራ በስተደቡብ ከታዩ የአፍሪቃ ፈጣን የእድገት ደረጃዎች መካከል አንዱ የሆነውን ከዐሥር ዓመታት በላይ አስቀጥለዋል ።» የዓለም ባንክ ስለ አላሳን ዋታራ ተጨማሪ አለው ። «በ2012 እና 2019 መካከል ትክክለኛው የአገሪቱ አጠቃላይ ምርትን በ8.2% አሳድገዋል ።»
የዳሎአ ነዋሪ የሆኑት ዳንኤላ ዛሁኢ፦ «ፕሬዝዳንቱ ለዳሎአ ላደረጉት አስተዋጽኦ ለማመስገን ሰብሰብ ወጥተናል » ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።
«እዚህ በብዛት የመጣነው የሪፐብሊኩን ፕሬዝዳንት ለማመስገን ነው ። ለዳሎአ ስላደረጉልን ነገር ሁሉ እናመሰግናለን እንላለን ።»
እንዲያም ሆኖ ግን ተግዳሮቶች የሉም ማለት አይደለም ። ከአገሪቱ መጋቢ መንገዶች 25 በመቶ ብቻ ነው ጥርጊያ የተደረገላቸው ። በዳሎዋ፣ ቫቮዋ፣ ሴጉዌላ እና ካኒ መካከል የሚገኙ 191 ኪሎ ሜትር አውራ ጎዳናዎች በመጥፎ ይዞታ ላይ ይገኛሉ ። የቫቮዋ ከተማ ልብስ ሰፊው ያያ ሳኖጎ በመንገዶቹ ብልሽት ከተማረሩት መካከል ናቸው ።
«መንገዱ በጣም መጥፎ ነው፤ ሌላው ቀርቶ መንገዱ ላይ መገኘት በራሱ አስቸጋሪ ነው ። ሥራችንን በአግባቡ ማከናወን አልተቻለንም ። እንደምታየኝ ዛሬ ነጭ ነው የለበስሁት፤ እናም ልነዳ ነው፣ ግን መንገዱ መጥፎ ነው ። እጅግ በዝግታ መንዳት አለብኝ ።»
አላሳን ዋታራ በምርጫው መቃረቢያ ተጨማሪ እድገት እንደሚኖር በመግለጥ ዳሎዋን ከያሞሶኮ ጋር በሰፊ አውራ ጎዳና ለማገናኘትም ቃል ገብተዋል ። አላሳን ዋታራ በምርጫው እንደገና ለመወዳደር የወሰኑት «የሃውፎውቲስቶች ለዲሞክራሲ እና ሰላም ግስጋሴ» የተሰኘው ፓርቲያቸውን ወክለው ነው ። ዘንድሮም ለውድድር ለመቅረብ መወሰናቸው ስለ ሥልጣን ዘመን ገደብ እና የዴሞክራሲያዊ ተዓማኒነት ላይ የተለመደ ክርክር አጭሯል ።
በርካታ ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ከምርጫው ታግደዋል
በርካታ ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ከምርጫው ታግደው ቆይተዋል ። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሎውረን ባግቦ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጊሊያም ሶሮ፣ የአይቮሪያን ሕዝባዊ ግንባር አባሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓስካል አፊ ንጉሳን፣ የቀድሞ የወጣቶች መሪ ቻርልስ ብሌ ጎውዴ እንዲሁም የስዊስ ባንክ አበዳሪ ስዊሴ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቲጃን ቲያም ከታገዱት ውስጥ ይገኙበታል ። የእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ከምርጫው መገለል ትችት አስነስቷል ብሎም በምርጫው ሂደት ፍትኃዊነት ላይ ስጋት አጭሯል ።
በኮት ዲቫር ለአራተኛ ዘመን ምርጫ ብቅ ያሉት ፕሬዝዳንት አላሳን ዋታራ ስለ ቀጣይ የአምስት ዓመታት ዕቅዳቸው በምርጫው ማግስት ተናግረዋል ።
«ለኮትዲቫር ብዙ አስተዋጽኦ በሚያበረክተው ለኑሮም ተስማሚ በሆነው በዳሎአ ክልል [እቅዳችን] በማስጀመራችን ደስ ብሎናል ። ካለፈው የተሻለ እንደምንሠራ እርግጠኛ ነኝ ። እድገቱ ጠንካራ ሆኖ እንደሚቀጥል በመተማመንም የ2025-2030 ዘመንን በከፍተኛ አቅም ጀምረናል ። ተጨማሪ መሠረተ ልማት፣ ተጨማሪ ምርት ብሎም ለእያንዳንዱ ዜጋ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ይኖራል ። እዚህ በዳሎአ ሁሉም ሰው ሊረዳው ይገባል በማለት ቀጣዩን ማለት እሻለሁ፦ እኛ ከፍታው ወደሚጨምረው መንገድ ላይ ነን ። ነገሮች በተሻለ ሁኔታ ይቀጥላሉ፤ እናም በትክክለኛው ጎዳና ላይ ነን ።»
በምርጫው የረዥም ዘመኗ ሴት ፖለቲከኛ ኤኺቬት ግባግቦም ይገኙበታል
ከአአላሳን ዋታራ ጋር ከሚፎካከሩት እጩዎች መካከል የባለአቅሞች ትውልድ ንቅናቄ ፓርቲን የሚወክሉት የረዥም ዘመኗ ሴት ፖለቲከኛ ኤኺቬት ግባግቦም ይገኙበታል ። የእሳቸው ፓርቲ በምርጫው ዋነኛ ትኩረቱ ያልተማከለ አስተዳደር፤ የትምሕርት እና የማኅበረሰባዊ ለውጦች ላይ መሆኑን ዐሳውቋል ።
«በዲሞክራሲ ነው የጀመርነው ። የዲሞክራሲ ትግሉ ዛሬም ቀጥሏል ። የታገልነው ላልተማከለ አስተዳደር ነው ። ምክንያቱም ያ ገና ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁም እኛ እንቀጥላለን ። ሦስተኛው ፕሮጀክት በተለይ በልባችን ልዩ ሥፍራ አለው፦ ጤና፣ ደህንነት፣ ጡረታ... የትምህርት ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ እንዲስተካከል ከስር ከስር ክትትል እናደርጋለን ።»
የአፍሪቃ ዲሞክራቲክ ንቅናቄ (PDCI-RDA) የተሰኘው የኮትዲቫር ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ቲያም የአላሳን ዋታራ ብርቱ ተፎካካሪ ተደርገው ይታዩ ነበር ። ነገር ግን የፈረንሳይ እና የኮትዲቫር ጥምር ዜግነት ያላቸው በመሆኑ ከተፎካካሪነት ውጪ ተደርገዋል ። የፈረንሣይ ዜግነታቸውን ቢመልሱም ዘግይተዋል በሚል ከእጩነት ተሰርዘዋል ። እናም የአላሳን ዋታራ መንግሥት ዴሞክራሲን ችላ ብሏል በሚል ምርጫውን «የንግሥና ሥርዓት» ሲሉ በብርቱ ተችተዋል ።
እንደ የተባበሩት መንግስታት የሥነ ሕዝብ ድርጅት ከሆነ፦ ከ60% በላይ የሚሆኑት የኮትዲቫር ዜጎች ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ነው ። በዚህ ሁኔታ የሥራ ዕድል ፈጠራ እጅግ አንገብጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው ሲልም አክሏል ።
የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቱ በሁለት ዙር ነው የሚከናነው ። ከእጩዎች መካከል ከ50% በላይ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ ከሌለ፦ ምርጫው ወደ ሁለተኛ ዙር ይሸጋገራል ። በአብላጫ ድምፅ የተመረጠው ፕሬዝደንትም ኮትዲቫርን ለአምስት ዓመታት ያገለግላል ። 30 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት ኮትዲቫር ለዘንድሮ ምርጫ 8.7 ሚሊዮን ሰዎች ድምፅ ለመስጠት መመዝገቡም ታውቋል ። የምርጫው አሸናፊ ውጤት በምርጫው ማግስት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ሲሊያ ፍሮይሊሽ
አዜብ ታደሰ























