DiscoverDW | Amharic - Newsየጥቅምት 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የጥቅምት 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የጥቅምት 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

Update: 2025-10-20
Share

Description

አጀማመሩ ላይ ዘንድሮም የሚደርስበት የለም የተባለለት ሊቨርፑል ለቡድኑ ደጋፊዎች እጅግ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን አስተናግዷል ። አርሰናል፤ ማንቸስተር ሲቲ፤ ቸልሲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በድል ግስጋሴ ላይ ይገኛሉ ። የስፔን ላሊጋ አንዳንድ ጨዋታዎችን ከስፔን ውጪ ባሉ አገራት ለማድረግ የተጀመረው እቅድ የተጨዋቾች ብርቱ ተቃውሞ ደርሶበታል ። ባርሴሎና ከቪላሪያል ጋር ከሁለት ወር በኋላ ግጥሚያውን የሚያካሂደው ዩናይትድ ስቴትስ ሚያሚ ውስጥ ነው መባሉ ነው የተቃውሞው መንስዔ ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በተለያዩ ውድድሮች ድል ቀንቷቸዋል ።



የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል



ስሎቬኒያ ዋና ከተማ ሉብሊያና ውስጥ ትናንት በተከናወነው 29ኛው የሉብሊያና የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አሸንፈዋል ። በወንዶች ፉክክር አትሌት ሃፍታሙ አባዲ ገብረሥላሴ(2:06:52 ) ሩጦ አንደኛ ወጥቷል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ከማል ሁሴን ኬኒያዊው ኮሊንስ ኪፕኩሩይ ኪፕኮሪርን ተከትሎ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ተስማሚ በነበረው የሉብሊያና የመኸር ወቅት የአየር ጠባይ በማሸነፍ የ21 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያው በዕድሜ ትንሹ ተብሏል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 በኢትዮጵያዊው አትሌት ሲሳይ ለማ ካሳዬ የተተያዘው (2:04:58 ) ክብረወሰን እስካሁን አልተሰበረም።



በሴቶች ፉክክር ደግሞ፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትግስት ገዛኸኝ (2:22:46 )በአንደኝነት ለድል በቅታለች ። በርካታ ሯጮች ከተለያዩ አገራት በትናንቱ ፉክክር መሳተፋቸው ታውቋል ። ከክሮሺያ (1,543) ከሠርቢያ (1,097) እንዲሁም ሌሎች 200 ሯጮች ከጣሊያን፣ ኦስትሪያ፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ ቦስኒ ሔርዜጎቪና ፣ ጀርመን እና ፈረንሣይ ታድመዋል ።



በጃፓን ቶኪዮ የግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ሰለሞን ባረጋ ርቀቱን (1:01 .21) በማጠናቀቅ አሸናፊ ሁናል ። በሴቶች ፉክክር አትሌት መስከረም ማም ሦስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች ።



በአምስተርዳም ማራቶንም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል ። በሴቶች ፉክክር የግል ምርጥ ሰዓቷን በማስመዝገብ አትሌት ዓይናለም ደስታ (2 :17.37) አሸንፋለች ። አትሌት ብርቱካን ወልዴ 2ኛ ስትወጣ፤ አትሌት መቅደስ ሽመለስ 3ኛ ደረጃን አግኝታለች ። ኬንያዊው አትሌት ጂዮፍሪ ኪብቹምባ ባሸነፈበት የወንዶች ፉክክር የባለፈው ዓመት አሸናፊ የነበረው አትሌት ጸጋዬ ጌታቸው በዘንድሮው ውድድር 2ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል ።



ሞቃታማ፤ ነፋሻማ እና ወበቃማ በነበረው የቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሹሬ ደምሴ አሸንፋለች። የገባችበት 2:21:03 የቦታው ሁለተኛው ፈጣኑ ሰዓት ተብሏል ። የቦታው ክብረወሰን ባለፈው ዓመት የተያዘው በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ዋጋነሽ መካሻ (2:20:44 ) ነው ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት አልማዝ ከበደ ኬኒያዊቷ ቤቲ ቼፕኮሪርን ተከትላ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቃለች ።



በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር ኬንያውያን ኢትዮጵያውያንን በልጠው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ኖሐ ኪፕኬምቦይ እና ሲላ ኪፕቱ ን አስከትሎ አሸናፊ የሆነው ሌዮናርድ ላንጋት ነው ። አትሌት ወርቅነህ ታደሰ እና አትሌት ይሁንልኝ አዳነ ከአሸናፊው በ59 ሰከንዶች ተበልጠው 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ አግኝተዋል ።



ሞሮኮ ዕድሜያቸው ከ20 በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊ



ሞሮኮ ዕድሜያቸው ከ20 በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊ ሆነች ። ቺሊ ውስጥ በተከናወነው የዘንድሮ ፍጻሜ አፍሪቃዊቷ አገር ዋንጫውን የወሰደችው የአርጀንቲና ቡድንን 2 ለ0 አሸንፋ ነው ። እንደምታሸንፍ በብዙዎች ዘንድ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው አርጀንቲና ላይ ሁለቱን ግቦች ለሞሮኮ ያስቆጠረው ያስር ዛቢሪ ነው ። ሞሮኮ ከ16 ዓመት በፊት ዋንጫ የወሰደችው ጋናን ተከትላ ዕድሜያቸው ከ20 በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን በመውሰድ ሁለተኛዋ አፍሪቃዊ አገር ሁናለች ። ኮሎምቢያ ከ22 ዓመታት ወዲህ ለደረጃ በመብቃት በሦተኛነት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልማለች ። ኮሎምቢያ ሦስተኛ የወጣችው ጨዋታው በተጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ በዖስካር ፔሪያ ፈረንሳይን 1 ለ0 በማሸነፍ ነው ።



ቅዱስ ጎርጊስ ቡድን ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ0 አሸነፈ



በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ጨዋታ ፈረሰኞቹ ማለትም ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ0 አሸንፏል ። ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የከተማዪቱ ሁለት ቡድኖች (ደርቢ)ግጥሚያ የማሸነፊያዋን ግብ በ66ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው አቤል ያለው ነው ። ጨዋታውን የቡድኖቹ በርካታ ደጋፊዎች ታድመው ተከታትለዋል ።



የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ



ነገ እና ከነገ በስትያ 18 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች፥ እንዲሁም ሐሙስ 18 የአውሮጳ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። ከአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች መካከል የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ ጋር የሚያደርጉት ይጠበቃል ። ከሁለቱ ኃያላን ቡድኖች አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ሌላኛው የስፔን ቡድን ባርሴሎና ከግሪኩ ዖሎምፒያኮስ ጋር ይፋለማል ። ይህንንም ጨዋታ በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በልዩ ሁኔታ የሚጠብቁት ነው ።



የእንግሊዙ አርሰናል ነገ ማታ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድን ያስተናግዳል ። የነገው ጨዋታ ለአርሰናል የፕሬሚየር ሊግ ግስጋሴ በእጅ አዙር የተለየ መሠረት የሚጥል ግጥሚያ ነው ። በሻምፒዮንስ ሊጉ የጀርመኑ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን ረቡዕ ዕለት የሚገጥመው ሊቨርፑል አቋሙ እጅግ መዋዠቅ ተስተውሎበታል ።



ሊቨርፑል ሲያሽቆለቁል አርሰናል በአሸናፊነቱ እየገሰገሰ ነው



የዘንድሮ ሽንፈቱ በሻምፒዮንስ ሊጉ የጀመረው ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን እያስተናገደ ነው ። ሊቨርፑል ዘንድሮ ያደረጋቸውን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፏል ። እንዲህ አራት ሽንፈት በተከታታይ ሲደርስበትም ከ11 ዓመት ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ነው ። ምናልባትም ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉም በአይንትራኅት ፍራንክፉርት ሽንፈት የሚገጥመው ከሆነ አምስት ጊዜያት በተከታታይ በመሸነፍ ከግማሽ ምእተ ዓመት ወዲህ ሌላ ታሪክ ይጻፍበታል ማለት ነው ። ቀያዮቹ እንዲያ በተከታታይ የተሸነፉት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1953 ነበር ። ከ72 ዓመት በፊት ማለት ነው ። የጥቅምት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ



ሊቨርፑልን ጉድ የሠራው ማንቸስተር ዩናይትድ ካሜሪሩናዊ አጥቂ ብሪያን ምቤኡም ከባለፈው ነሐሴ ወር ወዲህ የመጀመሪያ ግቡን ሊቨርፑልን በሜዳው 2 ለ1 ባሸነፉበት ግጥሚያ አስቆጥሯል ። በትናንቱ የ2 ለ1 ድል ብሪያን ከአይቮሪ ኮስቱ የክንፍ መስመር አስጨናቂ ተጨዋች አማድ ዲያሎ የተላከለትን ኳስ ተቀብሎ ከመረብ ያሳረፈው የሊቨርፑል ዋና ተከላካይ ቪርጂል ፋን ጂክን አልፎ ነበር ። በአንፊልድ ሜዳ በሊቨርፑል ደጋፊዎች ፊት መላ ሊቨርፑልን ኩም ያደረገውም ጨዋታው በተጀመረ 61ኛው ሰከንድ ላይ ነበር ።



የሊቨርፑል የቀድሞ ተከላካይ የወቅቱ የስፖርት ተንታኝ ጂሚ ካራጋር የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ ተቀያሪ መሆን ነበረበት ሲል አሰልጣኙን ወቅሷል ። የ33 ዓመቱ ግብጻዊ አጥቂ ትናንት ከግብ ጠባቂ ፊት ለፊት ያገኘውን ግብ መሆን የሚችል ኳስ አምክኗል ። ጂሚ ካራጋር የሞሐመድ ሣላኅ አቋም ስለዋዠቀ በቀጣይ ግጥሚያዎች ተቀያሪ መሆን አለበት ብሏል ።



ጂሚ ካራጋር ለሊቨርፑል አሰልጣኝ ምክር አለው



ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉ፦ በጋላታሰራይ፤ በፕሬሚየር ሊጉ በቸልሲ፣ ክሪስታል ፓላስ እንዲሁም ትናንት ከዋነኛ ተቀናቃኞቹ በአንዱ በማንቸስተር ዩናይትድ መሸነፉ በደጋፊዎች ዘንድ ብርቱ ቁጣ አጭሯል ። የስፖርት ተንታኞች ያለፈው የተጨዋቾች ዝውውር ከመጠናቀቁ በፊት 600 ሚሊዮን ዶላር ካፈሰሰው ሊቨርፑል ይህ አይጠበቅምም ብለዋል ። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን የመጀመሪያ ሳምንታት ተከታታይ ድል እጅግ ሲወደሱ የነበሩት አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ላይም ነቀፌታው እየበረታ ነው።



የሊቨርፑል አሰልጣኝ ትናንት ቡድኑ አሉኝ ሲል የሚመካባቸውን አጥቂዎች በአጠቃላይ ከተቀያሪ ወንበር አስነስተው ቢያሰልፉም መራር የሽንፈትን ጽዋ ከመጎንጨት ግን ምንም የቀየረላቸው ነገር የለም ።



ጂሚ ካራጋር ለሊቨርፑል አሰልጣኝ ምክር አለው፥ የአጥቂ መስመራቸውን በዋናነት በአሌክሳንደር ኢሳቅ እና በፍሎሪያን ቪርትስ እንዲመሠርቱ ። በከፍተኛ ወጪ ወደ ቡድኑ የመጡት እነዚህ ሁለት አጥቂዎች እስካሁን በአብዛኛው በተደጋጋሚ ጊዜያት ከተቀያሪ ወንበር እየተነሱ ነው የሚሰለፉት ። አሰልጣኙ ሌላኛው አስጨናቂ አጥቂ ኢኪቲኬም አለላቸው፥ መላው ግን የጠፋቸው ይመስላል ። ሊቨርፑል እስካሁን ባደረጋቸው ስምንት ግጥሚያዎች እንደ በርመስ 15 ነጥብ ተመሳሳይ የግብ ክፍያ ሰብስቦ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይንቧቸራል ። ከመሪው አርሰናልም በአራት ነጥብ ይበለጣል ።



የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም እየተሳካላቸው ነው



በአንጻሩ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በትናንቱ ድል እጅግ ተወድሰዋል ። ከዘጠኝ ዓመታት ወዲህ ቡድናቸው በአንፊልድ ሜዳ ድል ሲቀዳጅ የመጀመሪያው በመሆኑም ለረዥም ጊዜ ሲሰቃይ ለነበረው ደጋፊ ታላቅ እፎይታ ብለውታል የትናንቱን ወሳኝ ድል ። የመስከረም 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ



አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ቡድኑን ከተረከቡ ከአንድ ዓመት ግድም ወዲህም ማንቸስተር ዩናይትድ በተከታታይ ግጥሚያዎች የማሸነፍ ወኔው እና ብቃቱ ተመልሷል ። ሆኖም ፖርቹጋላዊው አስልጣኝ፦ ቡድናቸው በዚህ የጨዋታ ዘመን ሌላም ማድረግ መቻሉ የሚረጋገጥበት ገና መሆኑን ጠቆም አድርገዋል ። ያን የሚያረጋግጡትም በሚቀጥለው ሳምንት ብራይተን ዖልድትራፎርድን ሲጎበኝ ተጨዋቾቻቸው በሚያሳዩት ብቃት መሆኑን ገልጠዋል ። የትናንቱ ድል ከሊቨርፑል በሁለት ነጥብ ብቻ ርቀው ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ከፍ እንዲሉ አስችሏቾዋል ። በቀጣይ ጨዋታዎች ምናልባትም ይበልጥ ወደ ላይ ከፍ ሊሉም ይችሉ ይሆናል ።



ቅዳሜ ዕለት ፉልሀምን በሜዳው ገጥሞ በሊያንድሮ ትሮሳድ ብቸኛ ግብ 1 ለ0 ያሸነፈው አርሰናል መሪነቱን ማስጠበቅ ችሏል ። ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ በኖርዌዩ ግብ አዳኝ ኧርሊንግ ዖላንድ ሁለት ግቦች ኤቨርተንን 2 ለ0 ጉድ አድርጓል ።



ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ ነገ ማታ ከቪላሪያል እንዲሁም በፕሬሚየር ሊጉ እሁድ ዕለት ከአስቶን ቪላ ጋር ይጋጠማል ። በነዚህ ጨዋታዎች አማካዩ ሮድሪ እንደማይሰለፍ ታውቋል ። የ29 ዓመቱ አማካይ ሮድሪ የማይሰለፈው ከኋላ ታፋው ላይ በደረሰበት ጉዳት መሆኑን አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ተናግረዋል ። በባለፈው የጨዋታ ዘመን ከደረሰበት ብርቱ የጉልበት ጉዳት አገግሞ የነበረው ሮድሪ የታፋ ጉዳት ያጋጠመው ብሬንትፎርድን 1 ለ0 ባሸነፉበት ግጥሚያ ነበር ። ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን 2 ለ0 ድል ሲያደርግም ሮድሪ አልተሰለፈም ። ማንቸስተር ሲቲ የሮድሪ የቀድሞ ቡድን ወደነበረው ቪላሪያል በነገው ዕለት ለሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ያቀናል ።



ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ ከመሪው አርሰናል በሦስት ነጥብ ተበልጦ በ16 ነጥብ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ግብ አዳኙ ኧርሊንግ ዖላንድ ደግሞ በ11 ከመረብ ያረፉ ኳሶች የሚደርስበት አልተገኘም ። የበርመሱ አንቷን ሴሜንዮ እና የክሪስታል ፓላሱ ዦን ፊሊፕ ማቴታ በስድስት እና አምስት ግቦች ይከተላሉ ።



በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ትናንት ቦሩስያ ዶርትሙንድን 2 ለ1 ያሸነፈበትን ጨምሮ በሰበሰበው 21 ነጥብ እየመራ ነው ። ኤር ቤ ላይፕትሲሽ በ16 ይከተላል፥ ሽቱትጋርት በ15 ነጥብ ሦስተኛ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ14 አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል።



በላሊጋው ተጨዋቾችን ያስቆጣው ምን ይሆን?



በስፔን ላሊጋ፦ ባርሴሎና እና ቪላሪያል ከዛሬ ሁለት ወራት በኋላ የሚያደርጉት ጨዋታ ከዩናይትድ ስቴትስ ሚያሚ እንዲሆን መወሰኑን በመቃወም የተለያዩናይትድ ስቴትስዩ ቡድኖች ተጨዋቾች በዝምታ ተቃውመዋል ። ላሊጋው የተጨዋቾችን ተቃውሞ ችላ በማለት የእግር ኳስ አሰሠራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተቃውሞውን ዕንዳያሳዩ አዝዟል ። ቢያንስ እስካሁን ባርሴሎና እና ቪላሪያል ተቃውሟቸውን አልገለጡም ያለው ላሊጋ በዕቅዱ እንደሚገፋበት ዐሳውቋል ። የመስከረም 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ



ቡድኖችን ከአገራቸው ውጪ የማጫወት እቅድ እንዲተገበር ከላሊጋው ቀደም ብሎ የጣሊያን ሴሪኣም ፈር ቀዳጅ ተግባር ፈጽሟል ። ኮሞ እና ሚላን ፔርዝ አውስትራሊያ ላይ ግጥሚያቸውን እንዲያደርጉ በሥራ አስፈጻሚዎች ደረጃ ንግግር እየተደረገ መሆኑም ተገልጧል ። ሴሪኣ እና ላሊጋ በሌሎች አገሮች ጨዋታዎችን ለማድረግ ማቀዳቸው ገቢያቸውን በከፍተና ደረጃ ለማሳደግ በማሰብ መሆኑም ተዘግቧል ። ትናንት የሪያል ማድሪድ እና ጌታፌ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊትም ተጨዋቾች ለ15 ሰከንዶች ያህል በፀጥታ ለአፍታ ቀጥ ብለው በመቆም ተቃውሟቸውን አንጸባርቀዋል ።



ሪያል ማድሪድ በዘጠኝ ተጨዋች የተጫወተው ጌታፌን በኬሊያን እምባፔ ግብ ትናንት እንደምንም 1 ለ0 አሸንፎ በ24 ነጥብ ዳግም ወደ መሪነቱ ተመልሷል ። አላን ንዮም ተቀይሮ በገባ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ከቪንሲየንት ጁኒዬር ጋር ተጋጭቶ 13ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ በቀይ ካርድ እስኪሰናበት ድረስ ጌታፌ የትልቁ ጎረቤት ከተማ ቡድን የሆነው ሪያል ማድሪድን አስጨንቆ ነበር ።



ቀይ ካርዱ በታየ ሦስት ደቂቃ ልዩነት ኬሊያን እምባፔ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ አስቆጥሯል ። ቆየት ብሎም አሌክስ ሳንክሪስ ሁለት ቢጫ ካርድ ዐይቶ በቀይ ከሜዳ ተሰናብቷል ። ሁለቱም ቀይ ካርዶች እንዲሰጡ ቪንሰንት ጁኒየር ላደረገው አስተዋጽኦ አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ አወድሶታል ። ሪያል ማድሪድ እና በሁለት ነጥብ የሚበለጠው ባርሴሎና በሚቀጥለው እሁድ በኤል ክላሲኮ ይፋለማሉ ። እጅግ በበርካቶች ዘንድ የሚጠበቅ ጨዋታ ነው ።



በፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ድል ርቆታል



በዩናይትድ ስቴትስ ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም፦ የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን ትናንት አሸናፊ ሁኗል ። የማክላረኑ ላንዶ ኖሪስ እና የፌራሪው ሻርል ሌክሌርክ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ዘንድሮ በፌራሪ ተሽከርካሪ የሚፎካከረው ሌዊስ ሐሚልተን አራተኛ ወጥቷል ።



እስካሁን በአጠቃላይ 346 ነጥብ የማክላረኑ ዖስካር ፒያስትሪ ይመራል ። ሌላኛው የቡድን አጋሩ ላንዶ ኖሪስ በ332 ይከተላል ። የትናንቱ አሸናፊ ማክስ ፈርሽታፐን በ306 ነጥብ ሦስተና ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሌዊስ ሐሚልተን በ142 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ከበላዩ የፌራሪ ቡድን አጋሩ ሻርል ሌክሌርክ በ192 እንዲሁም የመርሴዲሱ ጆርጅ ሩሴል በ252 ነጥብ ተደርድረዋል ።



ማንተጋፍቶት ስለሺ



አዜብ ታደሰ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የጥቅምት 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የጥቅምት 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi