ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ተሸለሙ
Description
በቀድሞዉ የኢትዮጵያ መንግሥት(ደርግ) ዘመን በኤርትራ ክፍለ-ሐገር አስተዳዳሪነት፣ በምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነትና በርዳታ ማስተባባሪያ ኮሚሽነርነት ያገለገሉት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርስ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ተሸለሙ።ለሻለቃ ዳዊት ዕዉቅናና ሽልማቱን የሰጠዉ ኮሚቴ አባል አቶ ኃይልገብርኤል አያሌዉ እንዳሉት ሻለቃ ዳዊት ለሐገርና ለወገን ያደረጉት አስተዋፅኦ አብነታዊ ነዉ።ሻለቃ ዳዊት ባሁኑ ወቅት የአፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ናቸዉ።
የሻለቃ ዳዊት አበርክቶ በኢትዮጵያ
ሻለቃ ዳዊት፣በኢትዮጵያ በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ከሰሯቸው ስራዎች መኸከል፣ጉልሕ ሆኖ የሚጠቅሱት ምን እንደሆነ፣ከዶይቸ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣እንደሚከተለው መልሰዋል።
''ትልቁ ሰራሁት የምለው፣ሁለት ነገሮች ናቸው፣ኢትዮጵያ ውስጥ እያለሁ። ኤርትራና ዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ነው። ኤርትራ በፖለቲካ ረገድ፣ ፖለቲካውን ወደ ሰብአዊነት በመለወጥ ህዝብ ግን እንደ ህዝብ ማየት፣የህዝብ መብት ማስጠበቅ፣ ህዝብን በተቻለ መጠን መብቱን እንዲረከብ ለማድረግ ጥረት ባለመደረጉ እዚያ ያደረሰው አንዱ እሱ በመሆኑ፣በእዛ ረገድ ፈትኜው፣ያንን ተግባር፣ያንን መለኪያ ያንን ዓይነት እርምጃ ውጤታማ ነበር። ግን ያን ለዘለቄታው አልሄደም። ሁለተኛ፣የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ሆኜ መጨረሻ ላይ የሰራነው ስራ፣ የብዙ ሚሊዮን ህዝብ ህይወት አትርፈናል፤ብዙ ሚሊዮን ህዝብ ህይወት አድነናል። ይሄ የተመዘገበ ነው፣እሱ እኮራበታለሁ።''
የዓለም አቀፍ መድረክ ድርሻ
ሻለቃ ዳዊት፣በዓለሙ ማኀበረሰብ ዘንድም ዕውቅና የተሰጣቸው ዲፕሎማት እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ከሃገር ከተሰደዱ በኋላ፣በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ስር ያሉ የተለያዩ ተቋማትን በመምራትና በማማከር አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅት፣በአፍሪቃ ደህነትና ፀጥታ ስጋቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ፣የአፍሪቃ ስትራቴጂና የጸጥታ ጥናት ተቋምን መስርተው፣በዋና ስራ አስፈጻሚነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
''በአፍሪቃ በጠቅላላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያገኘሁትን ልምድ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር የመስራት ልምድ እና በአገር ውስጥ ደግሞ የዕርዳታ መስጠት፣ባከበትኹት ልምድ ብዙ የአፍሪቃ አገሮችን ረድቼያለሁ። እና የተወሰኑ ቦታዎች በተለይ ትዝ የሚሉኝ፣በሩዋንዳ በጣም አስፈላጊ በነበረበት ጊዜ እዛ ነበርኹ። ላይቤሪያ በጣም አስፈላጊ በነበረበት ጊዜ እዛ ነበርኹኝ ፣እና ሌሎችን ቦታዎች ያንን ልምዴን መጠቀም በመቻሌ፣ደስ ይለኛል ፣ትዝ ይለኛል። ''
የዝግጅቱ ዓላማ
ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስን ለማመስገን፣ለማክበር እና ለመሸለም ባለፈው ቅዳሜ የተዘጋጀውን ልዩ መድረክ ካሰናዱት መኻከል፣የአስተባባሪው ኮሚቴ አባል የሆኑት፣አቶ ኀይለገብርኤል አያሌው፣የመርሃ ግብሩን ዓላማ በተመለከተ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተውናል።
''የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማ፣አንድም ለዘመናት ለሰራ ሰው ማመስገን ተገቢ በመሆኑ፣ዘግይተናል እንጂ መፍጠን ነበረብን። ለሚሰራ ሰው መመስገን እንዳለበት ማሳየት ነው። በዋናነት ግን ለትውልዱ ተምሳሌ ማሳየት ይኖርብናል። እንደ ሻለቃ ዐይነት ሞዴል የሆኑ ሰዎች ደግሞ፣ መመስገንም በአደባባይ መከበርም መታውቅም ያለባቸው፣በትምህርታቸው፣ በስራ ልምዳቸው፣በህይወት አኗኗራቸው ተምሳሌት፣ለዚህ ትውልድ በመሆናቸው፣ሻለቃን ማክበር አለብን፣ትውልዱ ከዚህ ታላቅ ሰው መማር አለበት፤የመማርን፣የመስራትን፣የመምከርን፣ማንበብን መጻፍን፣ እንግዲህ ሻለቃ ወታደርም፣ደራሲም፣ ዲፕሎማትና በጣም ሁለገብ ነው። ''
በዚሁ መድረክላይ፣የተለያዩ ዕውቅ ግለሰቦች፣ለሻለቃ ዳዊት የላቀ አስተዋጽዖ ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ለመታሰቢያ የሚሆን የምስጋና ስጦታ ለሻለቃ ዳዊት መበርከቱን፣የኮሚቴው አባል ገልጸውልናል።
የወደፊት ዕቅድ
ወደፊትም፣ለሃገርና ለማኀበረሰባቸው የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎችን የማመስገንና የመሸለም ዕቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
''ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን፣ለአገር የደከሙ የሰሩ ሰዎችን እንደዚሁ የማክበር የማስተዋወቅ ዐሳቦች አሉን። '' ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ
























