ተቃዋሚዎች ሥጋት ቢጫናቸውም በኢትዮጵያ ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ እየወሰኑ ነው
Description
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የጊዜ ሰሌዳ ከጸደቀ ከስድስት ወራት በኋላ ማለትም ግንቦት 24 ቀን 2018 የሀገሪቱ ዜጎች የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ለመምረጥ ድምጽ ይሰጣሉ። የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎችን ለመመልመል ምርጫ ቦርድ አውጥቶት የነበረው ማስታወቂያ ከወላይታ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ ለተመረቀ ወጣት ለአጭር ጊዜም ቢሆን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርለት ተስፋ አድርጎ ነበር።
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ አራት ዓመታት ያለፈው ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ወጣት “ሌላ ሥራ ስለሌለ” የምርጫ አስፈጻሚነትን “እንደ አማራጭ” ወስዶታል። የመጀመሪያ ዲግሪ ቢኖረውም ሥራ ፍለጋ “በጣም ከባድ ነው” የሚለው ወጣት በቋሚነት የሚቀጥረው አላገኘም።
“እስካሁን ተፍተፍ እያልን በግል እየሰራን ነው የቆየንው። በግል ቢዝነስ ሥራ ጀምረን መሀል ላይ የካፒታል ጉዳይ ስላጋጠመኝ ትተን ወጥተን አሁን ቤት ቁጭ ብለናል” የሚለው ወጣት የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ለመመልመል ማስታወቂያ ሲወጣ መመዝገቡን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።
የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ምልመላ ሜላተወርቅ ኃይሉ በሰብሳቢነት የሚመሩት ተቋም ከሚያከናውናቸው የ2018 ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅቶች አንዱ ነው። ተቋሙ ለምርጫ ያዘጋጀው የጊዜ ሰሌዳ ገና ባይጸድቅም ፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች እንዲያስመዘግቡ የሰጠው ጊዜ ዛሬ ያበቃል።
የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ መሐመድ አብራር የዕጩዎች ምዝገባ ከመከናወኑ በፊት ቢያንስ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው መጽደቅ ነበረበት የሚል አቋም አላቸው። “የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን በጋራ እናጸድቀዋለን ብለው ነበር” የሚሉት አቶ መሐመድ “ረቂቁን አቅርበው ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ተነስቷል። የማሻሻያ ሐሳቦቹን ለማድመጥ ዝግጁዎች አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶይቼ ቬለ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢ-ሜይል እና በስልክ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ቦርዱ “የዕጩዎቻችሁን ዝርዝር፣ የምትወዳደሩበትን ምልክት የመሳሰሉትን አስገቡ” ማለቱን ያስታወሱት አቶ መሐመድ “ምን ያህል ፓርቲዎች እንደሚሳካላቸው አላውቅም። እንግዲህ በተለያየ መንገድ እርስ በርስ ስለምናወራ የሚያሳኩ አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል።
በመጋቢት 2015 የተመሠረተው ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ቢወስንም ሊቀ-መንበሩ አቶ መሐመድ ግን “ብዙዎቹ ነገሮች የተመቹ አይደሉም” ሲሉ ይናገራሉ።
“የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ምርጫ ለማድረግ” የማይመች እንደሆነ የሚገልጹት የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ሊቀ-መንበር “መንገዶች በተለያየ አጋጣሚ የሚዘጉበት፣ ጦርነቶች ፣ ግጭቶች ፣ ዘረፋ እና የመሳሰሉት ያሉበት” በመሆኑ “ከሰላም አንጻር ምቹ ነገር የለም” የሚል አቋም አላቸው።
“ተቋማት በገዥው ፓርቲ ቅርጽ እና አምሳል የሚተነፍሱ ናቸው። ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን ቀስ በቀስ ከገበያው እንዲወጡ ተደርገዋል” ወይም ስፖርት እና መዝናኛን በመሳሰሉ “የፖለቲካ ቃና በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተደርገዋል” ሲሉ ይተቻሉ።
ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ለሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሲዘጋጅ ግጭቶች እና የጸጥታ ሥጋቶችን እያሳነሰ ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ ሲያተኩር ታይቷል። የፓርቲው ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች “100% የምርጫ ምቹነት” ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
“ሰላም የለም” ፣ “ምርጫ አያስፈልግም” “ምናምን” የሚሉ ችግሮች “ሥርዓተ-መንግሥት ለማዳከም ለማፍረስ” ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ለፓርቲው አመራሮች የገለጹት ዐቢይ “እያንዳንዱ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል ራስህን መፈተሽ ያለብህ ሕጋዊ ለመሆን ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ለሁሉም ኃይሎች አስቻይ እንዲሆን መስራት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በኢትዮጵያ ለምርጫ “አስቻይ ሁኔታዎች” ባለመኖራቸው “ለመሳተፍ ያስቸግረናል” የሚል አቤቱታውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቢያቀርብም መፍትሔ እንዳላገኘ የፓርቲው ምክትል ሊቀ-መንበር ሙላቱ ገመቹ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲው አባላት ታስረው ቢሮዎቹ በመዘጋታቸው “ተገፍተን ነው የወጣንው” የሚሉት አቶ ሙላቱ “ከአምስት ዓመት ጀምሮ ሁሉም ቢሮዎች እንደተዘጉ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
ይሁንና የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ “በሁለት ተከታታይ የምርጫ ወቅቶች በጠቅላላ ወይም የአካባቢ ምርጫ ውድድር ሳይሳተፍ የቀረ እንደሆነ” በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊሰረዝ እንደሚችል የሚደነግግ በመሆኑ ኦፌኮ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
በጉዳዩ ላይ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውይይት ማድረጉን የገለጹት አቶ ሙላቱ “አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል። ሕጋዊ ሆኖ ለመቆየት ያለው ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ስለሆነ ተገደን ለምርጫ ሳይሆን ራሳችንን ለማቆየት የሚቻለውን ያህል ለመካፈል እንሞክራለን ብለናል” ሲሉ አስረድተዋል።
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በምርጫ ቦርድ ላለመሰረዝ በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ለመሳተፍ ቢወስንም በአዲስ አበባ እና “ጥቂት አካባቢዎች ብቻ” እንደሚሆን አስታውቋል።
በሀገሪቱ የተከማቹ የጸጥታ እና የፖለቲካ ችግሮች “መንግሥትን ለመቀየር፣ ለመገዳደር ወይም መሠረታዊ የአቋም ለውጥ እንዲያደርግ” ጫና ለማሳደር ምርጫ ኩነኛ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል አቶ መሐመድ ያምናሉ። ይሁንና ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ በምርጫው ለመሳተፍ ቢወስንም “የይስሙላ” ሚና እንዲኖረውም ይሁን “አጃቢ” መሆን አይፈልግም።
አቶ መሐመድ “በምርጫው እንሳተፋለን። የምንሳተፈው ግን እያንዳንዱን የምርጫውን ሒደት በንቃት በመከታተል እና በምርጫው ሒደት ውስጥ ሆነን አስገዳጅ ነገሮች የሚመጡ ከሆኑ የተለዩ ውሳኔዎች ልንወስን እንችላለን” ሲሉ የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲን አቋም አስረድተዋል።
አርታዒ ጸሀይ ጫኔ























