ትኩረት በአፍሪቃ፣ የደቡብ ሱዳን ዉጥረት፣ የሩሲያ ጥቅም በሊቢያ
Description
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የገጠሙት ሽኩቻ አዲሲቱን ሐገር ዳግም ከጦርነት ይከታል የሚለዉ ሥጋት እየተጠናከረ ነዉ።የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና ዋነኛ ተቀናቃኛቸዉ ምክትል ፕሬዝደንት ዲያክ ማቻር ሐገራቸዉ ከሱዳን ከተገነጠለች ከጥቂት አመታት በኋላ የገጠሙት ጦርነት በሠላም ሥምምነት የቆመዉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2018 ነበር።በቅርቡ ደግሞ ሁለቱ ፖለቲከኞች የገጠሙት ሽኩቻ ተካርሮ የሚያዟቸዉ ኃያላት ካለፈዉ ጥር ጀምሮ በየሥፍራዉ እየተጋጩ ነዉ።
ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር የሚያዟቸዉ ፀጥታ አስከባሪዎች የተጣማሪዉ መንግሥት ባለሥልጣናት የነበሩትን የማቻር ፓርቲ አባላትን አስረዋል።ባለፈዉ ሳምንት ደግሞ ዶክተር ማቻር ራሳቸዉ በቁም ታስረዋል።ሁለቱ ወገኖች የገጠሙት ሽኩቻና ግጭት የለየለት ጦርነት እንዳያስከትል ለማደራደር የአፍሪቃ ሕብረት፣ ኢጋድና ምዕራባዉን መንግስታት እየጠየቁ፣ ለማደራደርም እያጣሩ ነዉ።
ተማፅዕኖ ጥረቱ የመቀጠሉን ያክል ተቀናቃኞቹ ወገኖች ኃይላቸዉን ለማጠናከር፣ ሌላኛዉን ወገን ለማደከምና ለዉጊያ የሚያደርጉት ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል።የሳልቫ ኪር መንግስት እስካሁን ድረስ የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ -ተቃዋሚ (SPLM-IO) የሚባለዉ የማቻር የፖለቲካ ፓርቲ ያዘዉ የነበረዉን አንድ ክፍለ ጦር ከማቻር ፓርቲ ከድቶ ሳልቫ ኪር ከሚያዙት የደቡብ ሱዳን ጦር ጋር እንዲያብር አድርጓል።
የጦሩ መክዳት፣ የሙሴ ቬኒ ድጋፍ
የጦሩ አዛዥ ጄኔራል ጋብሪየል ቦል አኑር ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት የሚያዙት ጦር ከእንግዲሕ ተጠሪነቱ ለደቡብ ሱዳን መከላከያ ጦር ነዉ።
«እኔ፣ የSPLM-IO የንቅናቄ የድርጅት ጉዳይ አዛዥ፣ ብርጌድየር ጄኔራል ጋብርኤል ቦል አኑር በማዝዘዉ ዞር ሥም በዶክተር ሪየክ ማቻር ከሚታዘዘዉ ከSPLA-IO አንጃ ለቅቀን ከደቡብ ሱዳን ሕዝባዊ መከላከያ ኃይል ጋር በይፋ ማበራችን አስታዉቃለሁ።»
ኢኳቶሪያል በተባለዉ ግዛት ከሰፈረዉ የSPLM/A-IO ጦር ኃይል 149 ተዋጊዎች እናት ክፍላቸዉን ከድተዉ ለሳልቫ ኪር መንግስት ጦር አጅ መስጠታቸዉም ተዘግቧል።
በፊት ለዶክተር ኮሎኔል ጆን ጋራንግ ኋላ ደግሞ ለሳልቫ ኪር ጠንካራ ድጋፍ የምትሰጠዉ ዩጋንዳ ለሳልቫ ኪር ኃይል ድጋፍ የሚሰጥ ጦር ኃይል ጁባ ዉስጥ ማስፈሯ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።የዘማቹ ጦር ብዛትና ትክክለኛ ተልዕኮዉ ግን በግልፅ አልተነገረም።የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴ ቬኒ ራሳቸዉ ባለፈዉ ሐሙስና አርብ ጁባን ጎብኝተዋል።ፕሬዝደንት ሙሴ ቬኒን አጅበዉ ጁባን የጎበኙት የዩጋንዳ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ሙሊንባ እንዳሉት የሁለቱ ሐገራት መሪዎች በጋራና አካባቢዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል።
«በሁለቱ መንግሥቶቻችን መካከል ባሉና ለሁለቱም መንግስታት በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ በመግባባት መንፈስ ተወያይተናል።በሁለቱ መንግስታቶቻችን መካከል፣ ባጠቃላይ በአካባቢዉ ያሉ የፀጥታ ጉዳዮችን አንስተናል።የንግድ ልዉዉጥን አንስተናል።የማሕበራዊና ኤኮኖሚያዊ ጥያቄዎችንም አንስተናል።»
ይበሉ እንጂ የጉብኝት ዉይይቱ ትኩረት ሙሴ ቬኒ ለሳልቫ ኪር አለኝታ መሆናቸዉን ለማሳየት እንደሆነ ለብዙዎች ሚንስጥር አልሆነም።
ከሙሳቬኒ ቀደም ብለዉ የአፍሪቃ ሕብረት «የብልሆች ምክር ቤት» ያለዉ የአደራዳሪዎች ቡድን ጁባን ጎብኝቷል።ቡድኑ ተቀናቃኛ ፖለቲከኞችን በተናጥል ቢያነጋግርም ዉጥረቱን ለማርገብም ሆነ ዶክተር ማቻርን ከቁም እስር ማስለቅ አልቻለም።ማቻር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከቁም እስር እንዲለቀቁ የአፍሪቃ ሕብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ባለፈዉ ሐሙስ ጠይቆ ነበር።እስካሁን የሰማዉ እንጂ የተቀበለዉ የለም።
የስምምነቱ ተግባራዊ አለመሆን የዉጥረቱ መሠረት ነዉ-ተንታኝ
የግጭት መነሻና መፍትሔዎችን የሚያጠናዉ ክራይስስ ግሩም የተሰኘዉ ተቋም የደቡብ ሱዳን ጉዳይ አጥኚ ዳንኤል አኬች እንደሚሉት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ጠብ አሁን ከደረሰበት ደረጃ የደረሰዉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2013 የተጀመረዉን ጦርነት ያስቆመዉ ስምምነት ገቢር ባለመሆኑ ነዉ።
«የርስበርስ ጦርነቱን ባስቆመዉ በ2018 በተደረገዉ ሥምምነት መሠረት በ2020 የተቋቋመዉ ተጣማሪ መንግሥት ዉስጥ አሁን ዉጥረት የተፈጠረዉ ስምምነቱ ተግባራዊ ባለመሆኑ ነዉ።ያን ሥምምነት ተግባራዊ ማድረጉ ከፍተኛ እንቅፋት ገጥሞታል።ከስምምነቱ ሐሳቦች ተግባራዊ የሆነዉ 10 በመቶዉ ብቻ ነዉ።በተጣማሪዉ መንግስት ዉስጥ ያሉት ፕሬዝደንቱና ምክትል ፕሬዝደንቱም እርስርበር መታገላቸዉን አላቆሙም።ግንኙነታቸዉ ጥሩ አልነበረም።በዚሕም ምክንያት ዉጥረቱ ተካርሮ አሁን ከ,ደረሰበት ደረጃ ደርሷል።»
ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ባወጀት በሁለተኛና ዓመቱ በ2013 በተጫረዉ ጦርነት ወደ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ አልቋል።ያላባረዉ የፖለቲካ፣ የጎሳና የሥልጣን ግጭት፣ ረሐብ፣ ጎርፍና በሽታ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ፈጅተዋል።ያሁኑ ዉጥረት ሌላ እልቂት ያስከትል ይሆን?
ሊቢያ አዲሷ የሩሲያ ሸሪክ
የቀድሞዉ የሶሪያ ፕሬዝደንት የበሽር አል አሰድ ሥርዓት በተቃዋሚዎቹ ከሥልጣን ከተወገደ ወዲሕ ሶሪያ የሚገኘዉ የሩሲያ ጦር ሠፈር በነበረበት መቀጠሉ እያጠራጠረ ነዉ።እርግጥ ነዉ በሶሪያዉ የሜድትራኒያን ባሕር ጠረፍ ታርቱስና ሕማይሚም የሚገኙት የሩሲያ የባሕርና የዓየር ኃይላት ጦር ሠፈሮች አሁንም በይፋ አልተዘጉም።
ይሁንና የሶሪያ አዲስ ገዢዎች በራሳቸዉ ፍላጎትም ሆነ በምዕራባዉያን ግፊት የሩሲያ ጦርን ከሐገራቸዉ እንዲወጣ ማዘዛቸዉ አይቀርም የሚለዉ ሥጋት በማየሉ የሞስኮ መሪዎች ሌላ አማራጭ እያማተሩ ነዉ።አማራጮቹ ብዙ ናቸዉ።ብዙ ታዛቢዎች ግን ሱዳንን በጣሙን ደግሞ ሌላኛዉን የሜድትራኒያን ባሕር አዋሳኝ አረብ አፍሪቃዊት ሐገርን ይጠቁማሉ።ሊቢያን።
የፀጥታ ጉዳይ አጥኚዎች እንደሚሉት በሽር አል አሰድ ባለፈዉ ታሕሳስ ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲሕ የሩሲያ ወታደራዊ አዉሮፕላኖች ከሶሪያ ወደ ሊቢያ በተደጋጋሚ በርረዋል።መንበሩን ኒዩርክ ያደረገዉ የሳዉፋን ማዕከል እንደዘገበዉ ደግሞ የሩሲያ የጦር መርከቦች የሊቢያዉ የጦር አበጋዝ ማርሻል ኸሊፋ ሐፍጣር በሚቆጣጠሩት የምሥራቅ ሊቢያ የቶብሩክ የባሕር ኃይል ሠፈር መሕለቃቸዉን ጥለዋል።የአዉሮጳ ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ጥናት ባልደረባ ታሪክ መግሪሲ።
«ለሩሲያ በጣም አጠራጣሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።በተለይ የአሰድ ሥርዓት ታሕሳስ ላይ ከተወገደ በኋላ በነበረዉ ጊዜ ጥርጣሬዉ በማየሉ፣ ሶሪያ የሚገኙ የሩሲያ መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን የጫኑ አዉሮፕላኖችና ዕቃ ጫኝ መርከቦች ለሩሲያ አስተማማኝ ሆኖ ወደተገኘዉ ወደ ሊቢያ ተደጋጋሚ በረራዎችና ጉዞዎችን አድርገዋል።ሥለዚሕ በሞስኮ ዓይን በሜድትራኒያን አካባቢ አስተማማኝ መስላ የታየችዉ ሊቢያ እንደነበረች ግልፅ ነበር።»
ሞስኮ ከሊቢያ የምትፈልገዉ ጥቅም
በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወረራ የተደገፉት የሊቢያ አማፂ ኃይላት የቀድሞዉን የሐገሪቱን መሪ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ሥርዓት ካስወገዱ ወዲሕ በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉ ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሐገር ተከፋፍላለች።መግሪሲ እንደሚሉት ሩሲያ የተለያዩ ተቀናቃኝ ታጣቂ ኃያላት በተከፋፈሏት ሊቢያ የተለያዩ ጥቅሞችን ለማግኘት እየጣረች ነዉ።
ቀዳሚዉ ሜድትራኒያን ጠረፍ ላይ ጦር ሠፈር ማግኘት ነዉ።የሊቢያን የተፈጥሮ ሐብት በተለይም ነዳጇን ለገበያ ማዋል፣በምዕራባዉያን ማዕቀብ ለተሸበበዉ የሸቀጥ ምርቷ ገበያ ማግኘት እና የጦር ሸማች ማግኘትም የሚጠቀሱ ናቸዉ።የኒዮርኩ ሶዉ ፋን ጥናት ተቋምም ተመሳሳይ እምነት አለዉ።ተቋሙ እንደሚለዉ የሩሲያ መድፎች ሐፍጣር ለሚያዙት የሊቢያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት (LNA) ተሸጧል ወይም ተሰጥቷል።ተቋሙ እንደሚለዉ ሊቢያን አቋርጠዉ ወደ አዉሮጳ ለመግባት በሚፈልጉ ስደተኞችም ላይ ሩሲያ ተፅዕኖዋን ማሳረፍ ትፈልጋለች።
የኸሊፋ ሐፍጣር ልጅ ሚና
የኮንራድ አደንአደናወር ጥናት ተቋም ባልደረባ ኡልፍ ለይሲንግ እንደሚሉት ሩሲያ ከምዕራባዊ ሊቢያና ርዕሠ ከተማ ትሪፖሊ ከሚገኙ የሐፍጣር ባላንጦች ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላት።ዋና ወዳጅዋ ግን ማርሻል ሐፍጣር ናቸዉ።
«(ሞስኮ) ከምዕራብና ከትሪፖሊ ኃይላት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላት።ትኩረቷ ግን ግልፅ ነዉ።ሐፍጣር ናቸዉ።ሐፍጣር ራሳቸዉም ብዙ ወዳጅ የላቸዉም።ዋና ደጋፊያቸዉ ሩሲያ ናት።ሩሲያ ቶብሮክ ዉስጥ የሶሪያዉን የመሰለ የባሕር ኃይል ሠፈር ለመያዝ አበክራ እየጣረች ነዉ።ሩሲያ የጦር ሠፈሩን እንዳታገኝ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የባደን አስተዳደር ሐፍጣር ላይ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርግ ነበር።የትራም አስተዳደር አቋም ገና አይታወቅም።»
ሐፍጣር ለዩናይትድ ስቴትሱ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) ሲሰልሉ አብዛኛ የጎልማሳነት ዕድሜያቸዉን ማሳለፋቸዉ ይነገራል።ኑሯቸዉም አሜሪካ ነበር።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2011 ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከተወገዱ በኋላ ወደ ሐገራቸዉ የተመለሱት ሐፍጣር ዘንድሮ 81 ዓመታቸዉ ነዉ።ዕድሜ መግፋት ምናልባትም የማይቀረዉ ሞት ካጋጠማቸዉ ልጃቸዉን ሳዳም ሐፍጣርን ለመተካት ሽማግሌዉ ማርሻል የተዘጋጁ መስለዋል።
ሥደኞችን እንደ መሳሪያ
ወጣቱ ሳዳም ጋና ካሁኑ ጄኔራል ናቸዉ።በግሪጎሪያኑ 2024 አንድ የስጳኝ ፍርድ ቤት በጦር መሳሪያ አዘዋዋሪነት ከሷቸዉ ነበር።ሩሲያ ሊቢያ ዉስጥ የጦር ሠፈር ለማግኘት በምታደርገዉ ጥረት አባታቸዉን ወክለዉ የሚደራደሩት ሳዳም ሐፍጣር ናቸዉ።የአዉሮጳ ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ጥናት ተቋም ባልደረባ ታሪክ መግሪሲ እንደሚሉት ጄኔራሉ በሚያዙት ቢን ዛይድ ብርጌድ በተባለዉ ሚሊሺያቸዉ አማካኝነት የረቀቀ መረብ ዘርግተዉ ስደተኞችን ማዘዋወሩን እያቀለጣጠፉት ነዉ።
በመግሪሲ ጥናት መሠረት አዉሮጳ ለመግባት የሚመኙ ሰዎች ከፓኪስታን፣ከባንግላዴሽ፣ ከተለያዩ የአፍሪቃና የአረብ ሐገራት እየተፈለጉ ምሥራቅ ሊቢያ ይደርሳሉ።አንዳዱ ስደተኛ እስከ 9ሺሕ ዶላር እንዲከፍል ይገደዳል።የሚደርስበት ግፍ ደግሞ ሲበዛ ዘግናኝ ነዉ-ታሪክ መገሪሲ እንደሚሉት።
«የሊቢያ አረብ ጦር ኃይል የሚባለዉ ዉስጥ የሚገኘዉ የእሳቸዉ ድርጅት ለስደተኞቹና ፈላሾቹ ቪዛ የሚሉትን የማስመሰያ የይለፍ ፈቃድ ይሰጣል።(ሳዳም ሐፍጣር) ሶሪያ ከሚገኝ ሻም ዊንግስ ከተባለዉ አየር መንገድ ጋር ግንኙነት አላቸዉ።ዓየር መገዱ ስደተኞቹን በሶሪያ በኩል ሊቢያ ያደርሳል።ዓለም አቀፉ የስደተኞች አሸጋጋሪ መረብ ሊቢያ ከሚደርሰዉ ከያንዳዱ ስደተኛ ገንዘብ ይከፈላቸዋል።ስደተኛዉ ከሊቢያ ወደ አዉሮጳ ለመሻገር ሲሞክር ደግሞ አንዳዴ መርከቡ ሻል ያለ ከሆነ ለአንያዳዱ መርከብ እስከ 80 ሺሕ ዶላር ያስከፍላሉ።»
መግሪሲ እንደሚሉት ሩሲያ በርካታ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ መፍለሳቸዉ አዉሮጶችን ለመጉዳት እንደ ጥሩ መሳሪያ ትጠቀምበታለች።ከዚሕ ቀደም የሶሪያ ስደተኞች በቤሎ ሩስ በኩል አዉሮጳ እንዲገቡ ትገፋፋ ነበር።አሁን ደግሞ ምሥራቅ ሊቢያን የሚቆጣጠሩት ወዳጆችዋ ስደተኞቹን በብዛት ወደ አዉሮጳ ማሻገራቸዉን መግሪሲ እንደሚሉት ትደግፋለች።አዉሮጶችን ለመበቀል እንደመሳሪያ ትጠቀምበታለች።
ነጋሽ መሐመድ