የመንገድ ብልሽት በመተከል ዞን
Description
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት መንገዱ በከፍተኛ ሁኔታ በመበላሸቱ ለመጓጓዣ አገልግሎት አስቸጋሪ ሆኗል። በወምበራ ወረዳ በቡና ንግድና እና ምርት ላይ የተሰማሩ እንዲሁም በቡሌን ወረዳም ለሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች በዚሁ መንገድ ችግር ምክንያት ምርታቸውን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመጫንና ለመሸጥ መቸገራቸውን ይናገራሉ። በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የመንገድ ብልሽት በዚህ ዓመት በስፋት ተስተውሏል። የዞኑ ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ችግሩን ለመፍታት መጠነኛ ጥገና እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክቷል።
የመንገድ ብልሽት በቡሌን እና ወምበራ ወረዳዎች የነዋሪዎችን እንቅስቀቀሴ ገድቧል
የመንገድ ብልሽት በመተከል ዞን ስር በሚገኙ እንደ ወምበራ ወረዳ፣ ቡሌን ያሉ ወረዳዎች በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም የተናገሩት ከቡሌን ወረዳ ባሩዳ የተባሉ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አሰናፊ ቢተው ጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚሻው ያሳስባሉ። በትራስፖርት እጥረት ተማሪዎች ወደ ከሌጅ ለመሄድ ሁለት ሳምንት እና ከዛ በላይ በአንድ ቦታ መቆየት እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ነዋሪው ከወረዳቸው እስከ ቻግኒ እና ግልገል በለስ ያለው መንገድ ብልሽት የንግድና የተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ማወኩን አስረድተዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ብቸኛው ቡና አምራችና በምርቱ የሚታወቀው ወምበራ ወረዳ የሚገኙ የቡና አምራቾችና ነጋዴዎች የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ወደ ማዕከላዊ ገበያ ምርታቸውን ለማቅረብ ከፍተኛ ጫና እያሳደረባቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል። አቶ ዋቃዩ ፉፋ በወምበራ ወረዳ ቦለሌ የተባለ ቀበሌ ነዋሪ እና የቡና አምራች ናቸው። በየዓመቱ የቡና ምርታቸው መጠን እየጨመረ የሚገኝ ቢሆንም ምርቱን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብና ለሌሎች ማኅበራዊ አንቅስቃሴዎችም የመንገድ ችግር አካባቢውን እየፈተነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በወምበራ ወረዳ የቡና ነጋዴዎችና አምራቾች ቅሬታ
«የምንታወቀው በቡና ምርት ነው። አምርተን መንገድ የለንም። ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ተረካቢም የለንም። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ምርት ጭኖ መንቀሳቀስ አልተቻለም። አርሶ አደሩ እዚሁ ለነጋዴዎች ይሰጣል። ትልቁ ችግራችን የምርት ሳይሆን የመንገድ ችግር ነው።»
በወረዳው ሌላው ቡና አምራች አቶ መገርሳ ታምራ በሰጡን አስተያየት አካባቢው በቡና ምርት የታወቀ እና ቡናን ወደ አማራ ክልል ከቻግኒ እና ባሕርዳ እንዲሁም በአዲስ አበባ ለገበያ እንደሚያቀረቡ ገልጸዋል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንገድ ችግር ተጽዕኖ እያሳደረባቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል።
«እንደ ወምበራ ወረዳ መንገድ የለንም። በተጨማሪም የወምበራ ቡና ልክ እንደ ጥይት ነው ኮንትሮባንድ እየተባለ የሚያዘው። ይህንን ችግር መንግሥት ሊፈታልን ይገባል። ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ በቀላሉ የምናቀርብበትን መንገድ መንግሥት እንዲያመቻችልን እንጠይቃለን። ባለፈው ዓመት የተሻለ ምርት አግኝተናል ይሄ ቡና መንገድ ከሌለ ምርቱ ዋጋ አይኖረውም።»
በወምበራ ወረዳ ቦለለ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ቢቅላ አበበ ይህ አካባቢ የሚታወቅበት ቡናን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ካለው መንገድ ችግር በተጨማሪም የቡና ቅጠል በመጎዳት ምርቱ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኝ በሽታም አንዳንድ ቦታዎች እየተከሰተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
‹‹በመንገድ መበላሸት ምክንያት መጓጓዣ አገልግሎት ለሁለት ሳምንት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር›› የዞኑ ንግድና ትራንስፖርት መምሪያ
የመተከል ዞን ንግድና ትራንስፖርት መምሪያ በበኩሉ ወምበራን ከቡሌን የሚያገኘው መንገድ ከፍተኛ በሆነ መልኩ መበላሹቱንና ለሁለት ሳምንት ያህልም አገልግሎት አቁሞ እንደነበርም ገልጸዋል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም አዲሱ የመንገድ ብልሽት በዚህ ዓመት ከቡሌን ወምበራ መካከል ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት ማስተጓጉሉን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ መለስተኛ ጥገናዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በመተከል ዞን ከወምበራ ወረዳ፣ በቡሌንና ድባጢ የተባሉ ወረዳዎች በኩል ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስና አማራ ክልል ቻግኒ ከተማን የሚያገናኘው መንገድ ብልሽት በዚህ ዓመት በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ