የደወሌው የባቡር አደጋ ያስከተለው ጉዳት
Description
በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው 28 ሰዎች በርካቶቹ ህክምና አግኝተው ወደ ቤት መሄዳቸውንም ገልጿል። አደጋውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የድሬደዋ ደወሌ የምድር ባቡር ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አየለ ወልደ ዮሐንስ በአደጋው 15 ሰዎች ሕይወታቸው መጥፋቱን ተናግረዋል። ከሟቾች መካከል አንዱ በፅኑ ተጎድቶ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ ያለፈ መሆኑ ተጠቅሷል።
በድርጅቱ ከ34 ዓመት ወዲህ ደረሰ በተባለው በዚህ አደጋ 28 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚው አብዛኞቹ ህክምና አግኝተው ወደ ቤት መሄዳችውን አስረድተዋል።
ከተጎጂዎቹ መካከል ስድስት ሰዎች በዛሬው ዕለት በተመሳሳይ ታክመው ከሆስፒታል መውጣታቸውን እንዲሁም ሁለት ተጎጂዎች ወደ ጅግጅጋ እና አዲስ አበባ ለህክምና መላካቸውንም የኃላፊው መግለጫ ያመለክታል።
በአሁን ሰዓት በህክምና ላይ የሚገኙ ተጎጂዎች ሰባት መሆናቸው እና ህክምናውም በሶማሌ ክልል ሺኒሌ እና በድሬደዋ በሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ወድቆ በነበረው የባቡር ጋሪ ሥር ሕይወቱ ያለፈ ሰው ሊኖር ይችላል በሚል ስጋት የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብሎ በማሰብ በወቅቱ መግለጫ አለመሰጠቱን ያነሱት አቶ አየለ በአፋጣኝ የወደቁትን ባቡሮች የማንሳት ሥራ ቢሰራም የታሰበው ስጋት አለመኖሩ ተጠቅሷል።
አደጋው እንዴት ተፈጠረ?
አደጋው የደረሰበት ባቡር ሁለት የመንገደኛ እና ስድስት የጭነት ጋሪዎችን ይዞ ከደወሌ ወደ ድሬደዋ የተነሳ መሆኑን የምድር ባቡር ድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አየለ ተናግረዋል።
ከደወሌ - ድሬደዋ ባለው የጉዞ መስመር ከሚገኘው የሺኒሌ ጣቢያ በኋላ እስከ ድሬደዋ የሚገኘው የጉዞ መስመር ዳገታማ በመሆኑ ባቡሩ የያዛቸውን ጋሪዎች ሁለት ቦታ ከፍሎ ወደ ድሬደዋ ማጓጓዙን አስረድተዋል።
በአሠራሩ መሠረት ከደወሌ የተነሱ አራት ጋሪዎችን ድሬደዋ አድርሶ ሺኒሌ በመመለስ ቀሪዎቹን አራት ጋሪዎች ይዞ ወደ ድሬደዋ ጉዞ ከጀመረ ከአስር ደቂቃ በኋላ ጋሪዎቹ ወደ ኃላ በመመለሳቸው ሺኔሌ ጣቢያ ላይ ቆሞ ከነበረ የሠራተኛ ባቡር ጋር በመጋጨታቸው አደጋው መድረሱን ሥራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።
«ሁለት ባቡሮች ተጋጩ የሚለው ትክክል አይደለም» የሚሉት አቶ አየለ ባቡር ወደ ኋላ በመመለሱ ምክንያት ሺኒሌ ጣቢያ ላይ ከቆመው ባቡር ጋር በመጋጨቱ የተከሰተ አደጋ ነው ብለዋል።
ባቡር ወደ ኋላ ለምን ይመለሳል?
የ130 ዓመት እድሜ ባለው አንጋፋው የባቡር ድርጅት ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ በመቆየት ልምድ ያላቸው የአሁኑየድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አየለ ባቡር በበርካታ ምክንያት ወደ ኋላ የመመለስ ችግር ሊገጥመው ይችላል ብለዋል።
ከአሁኑ አደጋ ጋር በተተያዘ ለምን ተመለሰ ለሚለውም «በቀጥታ ከባቡሩ ጋር በተያያዘ፣ ከሀዲዱ ጋ በተያያዘ፣ ከጭነት ጋር በተያያዘ የሚጠና ጥናት አለ» ነው ያሉት አቶ አየለ።
በቀጣይ የድርጅቱ የቴክኒካል የጥናት ፕሮግራምን ጨምሮ የድሬደዋ እና የሺኒሌ መስተዳድር ተወካዮች የሚካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ በሚገኘው ውጤት መሠረት ለችግሩ መከሰት መንስዔ ምላሽ እንደሚሰጥ በኃላፊው ተገልጿል።
አደጋው ከተከሰተ በኋላ ተጎጂዎችን ወደ ህክምና ተቋማት በማድረስ እና አስፈላጊውን ርብርብ በማድረግ የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ኅብረተሰብ እንዲሁም የሺኒሌ ዞን እና የድሬደዋ አስተዳደር የህክምና እና ፀጥታ ተቋማት እንዲሁም የምድር ባቡር ድርጅቱ ሠራተኞች ከፍተኛ ሥራ መሥራታቸውን አቶ አየለ ተናግረዋል።
የድሬደዋ ደወሌ የምድር ባቡር ድርጅትን በበላይነት የሚመራው ቦርድ አባላት በአደጋው ኃዘናቸውን በመግለጽ ከተጎጂዎች ጎን በመቆም እያደረገ ያለው ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የድሬደዋ - ደወሌ ባቡር አገልግሎት
በሳምንት ሁለት ቀናት ከድሬደዋ - ደወሌ ባለው 208 ኪሎ ሜትር ርቀት የባቡር መጓጓዣ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ በቀድሞ ስያሜ (ኢትዮ - ጅቡቲ የምድር ባቡር) የአሁኑ የድሬደዋ- ደወሌ የምድር ባቡር ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አስረድተዋል። ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ አራት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንዲሁም አራት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ አራት ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ዕቃ ማጓጓዙን የድርጅቱ መግለጫ ያመለክታል።
መሳይ ተክሉ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ
























