በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በብሔራዊ ምክክር እንዲሳተፉ ተጨማሪ ጥሪ ቀረበ
Description
በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ በባሕር ዳር ሲጀመር የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረአያ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት በተደረጉ ጥረቶች በአማራ ክልል ከፍተኛ የማህበራዊ፣ የሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት በአማራ ክልል በተፈጠርው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነዋል፣ በርካታ እናቶች በህክምና እጦት ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ተዳርገዋል ፡፡
ችግሮችን በመለየትና የማያግባቡ ነጥቦችን ለይቶ በማውጣት በጉዳዮቹ ላይ ተወያይቶና ተመካክሮ መፍታት ተግቢ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን ከዚያ ውጪ ያሉ አማራጮች ዘላቂ መፍትሔ አያመጡም፣ ካመጡም ዘላቂነት የላቸውም ነው ያሉት።
የአጀንዳ ማሰባሰብ በአማራ ክልል
በክልሉ ትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ኃይሎች ወደ ምክክር መድረኩ እንዲመጡ ኮሚሽኑ ሠፊ ሥራ ሲስራ ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ አሁንም ታጣቂዎቹ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ በድጋሜ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዛሬ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የምክክር መድረኩ በይፋ ሲከፈት ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ምክከሩ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት አላቸው፣ በምክክር መድረኩ ያልተገኙ ወገኖችም ጥያቄዎቻቸውን አቅርበው ችግሮች ከአፈ ሙዝ መለስ በንግግር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል የሠላም ምክር ቤት የሠላም ጥረትና ጥሪ
በምክክር መድረኩ በአማራ ክልል ክሚገኙ 267 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች መካከል ከ263ቱ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ ከ4ሺህ 500 በላይ ተወካዮችና ከለሎች ማህበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከተፈናቃዮች፣ ከአካለል ጉዳተኞችና ከሌሎችም አካላት የተወከሉ፣ በአጠቃላይ ከ6ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 4/2017 ዓም በሚቆየው ምክክር፣ የአጃንዳ መረጣና በብሔራዊ ደረጃ የሚወከሉ ተሳታፊዎች እንደሚለዩ ታውቋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ