በርካቶችን ስጋት ላይ የጣለው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ስንብት
Description
ላለፉት 12 ዐመታት በከሰም ስኳር ፋብሪካ በቋሚ ሰራተኝነት በመቀጠር የሰራችው ውብነሽ ዓለሙ አስራ ሁለት ዓመታትን በዘለቀው በፋብሪካው ሰራተኝነት ወቅት በዚያው ትዳርን መስራተው ሶስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝን ተደጋግሞ በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ ሰበብ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ከሰም ስኳር ፋብሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹን ለመበተን ያስተላለፈው ውሳኔ ክፉኛ ስጋት ላይ ከጣላቸው የፋብሪካው ሰራተኞችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከፍተኛ ስጋት የደቀነው የመሬት መንቀጥቀጥ
የውብነሽ የልጆቿን ሞግዚት እና ባለቤቷን ጨምሮ ስድስት የቤተሰብ አባላት ያለው ጎጆአቸው አሁን አደጋ ላይ መውደቁንም ተናግረዋል፡፡ “ፋብሪካው የሁለት ወራት ደመወዝ እስከ ሚያዚያ 10 በመክፈል ሰራተኞቹን ለመበተን ወስኗል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሰራተኛው ጥቅሙ ሳይከበር የዓመት እረፍ ያለውም በዚሁ ወቅት እረፍት እንዲሞላ ተገደዋል፡፡ ስራም ሌላ ቦታ አልተመደብንምና ያው የራሳችን ውሳኔ እንድንወስድ ነው የተወሰነብን” ብለዋል፡፡
የሁለት ወራት ደመወዝ አለመከፈል ሌላው ተጨማሪ ፈተና
ከዚህም ባሻገር ከጥር ወር ወዲህ የሁለት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው የሚገልጹት የፋብሪካው ሰራተኞች ብያንስ ቀነገደብ እስከተቀመጠለት ሚያዚያ 10 እንኳ መንቀሳቀሻ የሚሆናቸው ነገር ማጣታቸው ብርቱ ፈተና ላይ እንደጣላቸው ያስረዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተለይም እንደውብነሽ ያሉትን ቤተሰብ አስተዳዳሪ የፋብሪካው ሰራተኞችን ህይወት ብርቱ ፈተና ላይ ጥሏል፡፡
“የገቢያ ማሻቀብ አለ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ደመወዝ ሳይከፈል ምንም ሳይኖር እንደኔ ቤተሰብ የያዘ አለ፡፡ እኔ አሁን ምንም ገቢ የለኝም፡፡ ባለቤቴም እዛው ነበር የሚሰራ ምንም ስራም አላገኘንም በጣም ችግር ላይ ነው ያለነው” በማለት አስተያታቸውን አክለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የካቲት ወር ላይ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ የስራ ማፈላለግያ የሁለት ወራት ቀነገደብ ተሰጥቷቸው እንዲበተኑ የስም ዝርዝራቸው በፋብሪካው ከተዘረዘሩ ሰራተኞች መካከል አንዱ መሆኑን የሚገልጸው ሙሴ የተባለ ሌላው ሰራተኛ በፊናው፤ “ደመወዝ ሁለት ወር በሙሉ አልተከፈለንም፡፡ እጃቸው ላይ ብር እንደሌለ ነው የሚነግሩን፡፡ በቃ አብዛኛው ሰራተኛ ቀን ስራም ምንም ያገኘውን እየሰራ ህይወቱን ለመምራት ተገዷልና አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጻዋል፡፡
የቀሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ከስራ መሰናበት
ዶይቼ ቬለ በነዚህ የሰራተኞቹ አቤቱታ ላይ ፋብሪካው አስተያየት እንዲሰጥበት በተለይም ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስከያጅ አቶ አሊ ሁሴን በተደጋጋሚ የእጅ ስልካቸው ላይ በመደወል ጥረት ብያደርግም እስካሁን አልሰመረልንም፡፡
የሰራተኞቹ መብት ተጣሰ መባሉ
ከወርሃ መስከረም መጀመሪያ ጀምሮ በተከታታይ አከባቢውን በናጠው ርዕደ መሬት ፋብሪካው ክፉኛ በመጎዳት ፈራርሷል የሚሉት የፋብሪካው ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ጌታሁን አርፍጮ፤ ፋብሪካው ሰራተኞቹን ለመበተን ሲያስብ መከተል ያለበትን ሂደት ጥሷል በማለት ማስተካከያም እንዲደግበት ለፋብሪካው ደብዳቤ ማስገባታቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
“አንደኛው ነገር ሰራተኛ ቅነሳ ሲያደርግ በህጉ መሰረት ከሰራተኛ ማህበር ወይም ተወካያቸው ጋር መነጋገር አለበት የሚለው ህግ ላይ ብኖርም ፋብሪካው ይህን አላደረገም፡፡ ሁለተኛው ነገር በተለይም ከ9 ዓመታት በላይ ላገለገሉ ሰራተኞች የሶስት ወራት ማስጠንቀቂያ መስጠት ይገባል ብልም ህጉ ፋባሪካው ለሁሉም ሰራተኞች የሁለት ወራት ማስጠንቀቂያ ብቻ በመስጠት ነው እያሰናበተ ያለው” በማለት ለወላድ ሴት ሰራተኞች ልሰጥ ይገባ የነበረው የአራ ወራት የእረፍ ጊዜ በዚህ መጣሱን አስረድተዋል፡፡
የማስተካከያ ያሉት ደብዳቤውን ለፋብሪካው አስገብተው እስከመጪው ሰኞ ምላሹን እየተጠባበቁ መሆኑንም የገለጹት የሰራተኛ ማህበሩ ኃላፊ በርካታ የፋብሪካው ሰራተኞች አሁን ላይ የመሬት መንቀትቀጥን ተከትሎ በየመጠለያውና ሌሎችም ቦታዎች በችግር ላይ መውደቃቸውንም አመልክተዋል፡፡ በተፈጥሮ አደጋ ከስራቸው ለመፈናቀል የተገደዱትን ቤተሰብ አስተዳዳሪ ጭምር የሆኑ ሰራተኞቹን መንግስት ከመበተን በማዳን በሌሎች የመንግስት ልማት ድርጅቶች የማሸጋሸግ እርምጃ እንዲወስድም ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ