ሩስያ በዩክሬይን ላይ የፈጸመችው የሚሳይል ጥቃት
Description
ሩስያ በማዕከላዊ የዩክሬይን ግዛት በምትገኝ የፕረዚደንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ የትውልድ ከተማ ላይ በፈጸመችው የሚሳይል ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18 መድረሱን የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ዛሬ ገለጹ። ትላን በክሪቪሪክ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት 61 ሰዎች ቆስለዋል ነው የተባለው።
የግዛቲቱ ገዥ ሰርሒ ሊሳክ ለአሶሽየትድ ፕረስ እንዳሉት ከሞቱት 18ቱ መካከል አንድ የ9 ዓመት ሕጻን ይገኝበታል። ከቆሰሉት 61 ሰዎች መካከልም የ3 ወር ሕጻንና ሽማግሌዎች ይገኙበታል ሲሉ የስራ ሓላፊው ተናግረዋል።
የዩክሬይኑ ፕረዚደንት ቮለደሚር ዘለንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው «የሚሳይሉ ጥቃት በመኖሪያ ቤቶች፣ በአካባቢው በሚገኙ የመጫዎቻ ሜዳዎችና ተራ መንገዶች ላይ ያነጣጠረ ነው» ሲሉ ጽፈዋል። «የሩስያ ወታደራዊ ጥቃቶች ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት እንደሌላት ያሳያሉ» ያሉት ፕረዚደንት ዘለንስኪ፤አጋሮቻቸው ይህን ለማስቆም በሩስያ ላይ ጠንከር ያለ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሚሳይል ጥቃቱ 20 የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች፣ ከ 30 በላይ መኪኖች፣ ቁጥራቸው ያልተገለጸ የትምህርትና የምግቤት ሕንጻዎች መውደማቸውን ታውቋል።
ከሚሳይል ጥቃቱ ዘግየት ብሎ በከተማዋ በተፈጸመ የድሮን ጥቃትም አንዲት ሴት መገደሏንና 7 መቁሰላቸውን ዜናው አክሏል።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ በከተማዋ በሚገኝ አንድ ምግቤት ተሰብሰበው በነበሩ የዩክሬይን ወታደራዊ አዛዦችና ምዕራባውያን አማካሪዎቻቸው ላይ ኢላማውን ሳያዛንፍ በሚሳይል መምታቱን ገልጿል።
በጥቃቱ 85 የዩክሬይንና የውጭ ወታደሮች መግደሉንና 20 መኪኖችን ማውደሙንም አረጋግጧል።
በሌላ ዜና የታላቋ ብሪታንያና የፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትሮች ለዩክሬይን በመደረገው ወታደራዊ ድጋፍ ላይ ለመምከር ክየቭ ይገኛሉ ሲል የዘገበው ደግሞ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።