በአስከፊ ኹኔታና ሥጋት ምያንማር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥሪ
Description
በአስከፊ ኹኔታ እና ሥጋት ምያንማር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጥሪ
የተሻለ ገቢ አለው ለተባለ ሥራ ወደ ምያንማር የተጓዙ፤ ይልቁንም ራሳቸውን አስከፊ አደጋ ውስጥ ያገኙት ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ መንግሥት የድረስልን ጥሪ አቀረቡ። በምያንማር በተለያዩ ድርጅቶች የማጭበርበር ድርጊት እንዲፈጽሙ ሲገደዱ ከቆዩት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ፣ አሁን ወደ ሀገሪቱ ጦር ሠራዊት ይቀላቅሉናል ወይም ወደ ቆየንበት የማጭበርበር ወንጀል ይመልሱናል ወደሚል ተጨባጭ ሥጋት እና አጣብቂኝ ውስጥ መውደቃቸውን ተናግሯል። የ21 ሀገራት ወጣቶች በዚሁ ችግር ምክንያት በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ እንደቆዩ የገለፀው ይሄው ኢትዮጵያዊ አሁን የኬንያ፣ የቬትናም እና የኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ መቅረታቸውንና የበለጠ ጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
አቤል የተባለው ወጣት ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ የተሻለ ገቢ ላለው ሥራ ወደ ምያንማር ሲጓዝ አስከፊ ሰቆቃ ከፊቱ እንደሚገጥመው አስቀድሞ አልገመተም ነበር። እሱን ጨምሮ ተገደው የማጭበርበር ሥራ እንዲያከናውኑ ይገደዱበት ከነበረበት የምያንማር ሩቅ ሥፍራ አሁን ለጊዜውም ቢሆን ወደ ሌላ ካምፕ 723 ኢትዮጵያውያን ከወጡ 46 ቀናት ቢሆናቸውም ከሀገሩ ጠቅልለው ሊወጡ ግን አልቻሉም።ምያንማር ውስጥ ለፈተና የተዳረጉት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ
"ሦስት ሀገራት [ዜጎች] ብቻ ነው ያለው። ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ቬትናሞች ናቸው። ቬትናሞች ከነገ ወዲያ እንደሚወጡ መረጃ አለኝ። ነገ ደግሞ ኬንያዎች ናቸው የሚወጡት። እኛ ኢትዮጵያውያኖች ብቻ ነው ያለነው"። ምያንማር ውስጥ "በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ" የተባሉ 32 ኢትዮጵያውያን በአንድ በረራ፣ 43ት ደግሞ በሌላ በረራ ከዚህ በፊት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። ዶቼ ቬለ ተመላሾችን እና ቤተሰቦቻቸውን ጠይቆ ይህንን አረጋግጦ ነበር።
እዚያው ምያንማር ውስጥ ከቀሩት መካከል አንዱ የሆነው አቤል (ስሙ ለደህንነቱ ሲባል በራሱ ጥያቄ የተቀየረ) ግን ተስፋቸው መመናመኑን ሊሸሽግ አልወደደም። "መንግሥታችን ብዙም ለእኛ እየተጨነቀ አይደለም። ከእነሱ ይልቅ እዚህ እዚህ አሸባሪ የሚባሉት ቢያንስ እንኳን በቀን ሁለት ጊዜም ቢሆን ሩዝ እያመጡልን ነው። ሁሉም ነገር ከአቅማችን በላይ ነው። ሥጋት ላይ ነው ያለነው"።ምያንማር ውስጥ ለችግር የተጋለጡት ኢትዮጵያውያን
እነዚህ ኢትዮጵያውያን አሁን ሁለት አጣብቂኝ ከፊታቸው መደቀኑን ጭምር በዚሁ ወጣት በኩል ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ሕብረተሰቡ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሀሰተኛ ቅስቀሳ ተታሎ የሥራ ስምሪት ውል ወደ አልተፈፀመባቸው ሀገራት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ" ከዚህ ቀደም አሳስቧል። ለዚህ ዘገባ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ተቋሙ ቃል ዐቀባይ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።
አዜብ ታደሰ
ሰለሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሰ























