አዲስ አበባ፤ የዶቼ ቬለ የሀገር ውስጥ ዘጋቢዎች መታገድ
Description
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዶቼ ቬለ ዘጋቢዎችን ለጊዜው ማገዱን በደብዳቤ ዐሳወቀ። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለዶቼ ቬለ በላከው ይፋዊ ደብዳቤ «በኢትዮጵያ የጀርመን ድምጽ አገልግሎት (DW) ቋሚ የዜና ወኪሎችን» ለጊዜው ማገዱን አመልክቷል። ምክንያቱንም ሲገልጽ፤ «ቋሚ የዜና ወኪሎቹ በተደጋጋሚ የሚሠሯቸው ዘገባዎች የመገናኛ ብዙኀን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 እና የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/20212 ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ እና የሙያ ስነምግባር ስታንድርድን ያልተከተሉ በመሆናቸው» ነው ብሏል።
ዶይቸ ቬለ በአማርኛ ቋንቋ ከ60 ዓመት በላይ ሚዛናዊ ዘገባዎችን እያቀረበ ይገኛል
አያይዞም ይህን መነሻ በማድረግ የዶቼ ቬለ ተወካዮችን በተደጋጋሚ ቢሮ በማስጠራት ግብረ መልስ በመስጠት፤ በማወያየት፤ የቃል እና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያዎችን» መስጠቱን፤ «ዘገባዎቻቸው ሕግና የሙያ ስነምግባርን እንዲያከብሩ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን፤ ሆኖም ተጨባጭ መሻሻሎች ባለመታየታቸ በ01, 05 2015 የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በደብዳቤ ለመገናኛ ብዙሃኑ መስጠቱን ዘርዝሯል። እንዲያም ሆኖ ስህተቶች አለመታረማቸውን በማመልከት ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ የዶቼ ቬለ ቋሚ የዜና ወኪሎች ፈቃድ ለጊዜዉ የታገደ መሆኑን በባለሥልጣኑ የፈቃድና ምዝገባ ዴስክ ኃላፊ አቶ ዮናስ ፋንታዬ በተፈረመ ደብዳቤ ዐስውቋል።























