ከኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን የተጋራው አብን የግብፁን ፕሬዝዳንት ሰሞነኛ መግለጫ ተቸ
Description
የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ሀገራቸው በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን መብት ችላ እንደማትል ሰሞኑን የተናገሩበትን እና "ሚዛናዊነት የጎደለው" ያለውን መግለጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ ባወጣው መግለጫ ነቀፈ።ከፌዴራል እስከ ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ባሉ መዋቅሮች የመንግሥትን ሥልጣን የተጋራው አብን የግብፁ ፕሬዝዳንት "የኢትዮጵያን ፍትሐዊ መብቶች ወደ ጎን በመተው ቀጣናዊ ትብብርን የሚሸረሽሩ" አቋሞችን አራምደዋል ብሏል።
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ይፋ በሆነበት በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንት አልሲሲ ያራመዱት አቋም ላይ አስተያየት የሰጡ አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ "ማስፈራሪያ ያዘለ" ያሉት የፕሬዝዳንቱ ንግግር "በዲፕሎማሲም፣ በሕግም፣ በኃይልም" የማያዋጣና ተገቢነት የጎደለው ነው ብለዋል።
የፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ መግለጫ
ግብፅ በዓባይ ወንዝውኃ ላይ ያላትን መብት በምንም መልኩ አሳልፋ እንደማትሰጥ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ ሰሞኑን ካይሮ ውስጥ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸው "የውኃ ሀብት መብቷን ችላ ትላለች ብሎ የሚያምን ማንኛውም ሰው ተሳስቷል" ሲሉ ከዩጋንዳ አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በሰጡት መግለጫ አሳስብዋል።ፕሬዝዳንቱ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የሕዝባቸውን ሐብቶች ለማስጠበቅ "ማንኛውንም 'ርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን የተጋራው አብን ምን አለ?
ከኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን የተጋራው አብን ይህንን የፕሬዝዳንት አልሲሲ መግለጫ አጥብቆ በተቸበት መግለጫው የተራመደው አቋም "የኢትዮጵያን ፍትሐዊ መብቶች ወደ ጎን በመተው ቀጣናዊ ትብብርን የሚሸረሽሩ ማደናቀፊያ ዘዴዎችን የተከተለ ነው" ብሏል። ፀረ-ኢትዮጵያ ትርክቶችን፣ አሉታዊ ስም የማጥፋት ዘመቻዎች በመንዛት "የጸጥታ አደጋዎችን በማቀጣጠል ላይ እንደምትገኝ የተረጋገጠ ሃቅ ነው" ሲልም ተችቷል። መግለጫው "ግትርነት ብቻ ሳይሆን ግብዝነትም" የተሞላው መሆኑንም ይጠቅሳል።
የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ ዳምጠው ተሰማ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ምላሽ ባይሰጥም መነሻቸው ምን እንደሆን ጠይቀናቸዋል።"የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ ብሔራዊ ጥቅም እና የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ሀብት የመጠቀም መብት የመጋፋት ዘላቂነት ያለው የፖሊሲ አቅጣጫ የያዘ በሚመስል ደረጃ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ" መግለጫ ማውጣታቸውን ገልፀዋል።የግብፁ ፕሬዝዳንት "የውኃ ድርሻዋን መተው የግብፅን ሕይወት መተው ማለት ነው" ሲሉ ከዚህ አስቀድመው የሕዳሴ የግድብ የመመረቂያ ጊዜ መገለፁን ተከትሎ "እክል የመፍጠር" እንቅስቃሴ መኖሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ባለፈው ሳምንት አስታውቀው ነበር።
"ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አለ፣ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት አለ። እሱን ለማሟላት ተጨማሪ ግድቦችን መሥራት ይኖርብናል። እሲን ለመሥራት ደግሞ አስገዳጅ የሆነ የውኃ ክፍግል ስምምነት በአሁኑ ሰዓት መግባት ተገቢ ነው ብለን እንደተቋም አናስብም፤ መንግሥትም እያንፀባረቀ ያለው ያንን መልዕክት ነው።"
የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ አስተያየት
አስገዳጅ የውኃ ውል ስምምነት እንዲፈረም በኢትዮጵያ ላይ ጫና የምታደርገው ግብጽ ይህ ፍላጎቷ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ የተደረገ ነው። በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝም ይህንኑ ይጋራሉ።"ወደ ማስፈራሪያነት የሚቃጣው የግብፅ አቋም ተገቢ ወይም ሕጋዊ ነው ብየ እልወስድም። በዲፕሎማሲ የሚያዋጣም አይደለም፣ በሕግም የሚያዋጣ አይደለም፣ በኃይልም ሊፈታ የሚችል አይደለም።"
በመጪው ጥቅምትየዓለም የውኃ ቀን ግብጽ ካይሮ ውስጥ ይካሄዳል ያሉት ተንታኙ ሀገሪቱ በዚህ መድረክ ላይ አጀንዳ ታደርገዋለች ተብሎ ከሚገነተው ጉዳይ አንዱ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደፊት ዓባይ ላይ ሊገነባቸው ይችላል ተብለው የሚገመቱ ግድቦች እንደሚሆን ገልፀዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ