የታጣቂዎች ጥቃት በመተከል ዞን በርበር እና ጎንጎ ቀበሌ
Description
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ የሸኔ አባላት ናቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች በርበር የተባለ ቀበሌ መስተዳደር ቢሮና ሰነድን ማቃጠላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡የወረዳው አስተዳደር ግን የቀበሌዉን ሰነድ ለማቃጠል የሞከሩት ሌቦች ናቸዉ ባይ ነዉ።የዛሬ ሶስት ወር ገደማ በቀበሌው ቃጠሎ መፈጸሙን እና በድርጊቱ የተሳተፉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተነግሯልም።
በድባጢ ወረዳ የበርበር ቀበሌ ቢሮ በታጣቂዎች መቃጠሉ ተነገረ
በመተከል ዞን የድባጢ ወረዳ ገጠራማ ቦታዎች እና ቡሌን ወረዳ ጎንጎ በሚባል አካባቢዎች የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እክል እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ባለፈዉ ቅዳሜ ጠዋት በድባጢ ወረዳ በርበር በተባለ ቀበሌ የቀበሌው አስተዳደር ቢሮ ተቃጥሎ ማየታቸውን ያነጋገርናቸው አንድ የአካባቢው ነዋሪ አመልክተዋል፡፡ ነሔሴ 28/2017 በዚሁ ቦታ ታጣቂዎች ማዘጋጃ ቤት ማቃጠላቸውን የተናገሩት ነዋሪው ቅዳሜ በተከሰተው የቢሮ ቃጠሎ የተሳተፉ ግለሰቦችን ማንነት መለየት እንዳልቻሉ አብራርተዋል፡፡ በዚሁ ቀበሌ እንደሚሰሩ የተናገሩት አንድ ባለሙያ ቅዳሜ ምንነታቸውን ያልታወቁ ሀይሎች የቀሌውን ቢሮ እና ሰነዶች ማቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
በድባጢ ወረዳ በርበር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ስማቸው እንዳገለጽ የነገሩን ሌላው ነዋሪ አርብ ምሽት ለቅዳሜ አጥቢያ በሼነ ሀይሎች ድንገት ወደ ከተማው በመግባት ቢሮውና የተለያዩ ሰነዶችን ማቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኃላ አካባቢውን ጥሎ መሸሻቸውን የገለጹት ነዋሪው ከዚህ ቀደም ሁለት ዙር ጥቃት ለመፈጸም ወደ አካባቢው የመጡ ታጣቂዎች በጸጥታ ሐይሎች መመታታቸውን አክለዋል፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች ለሠላዊ እንቅስቀሴ አዳጋች እየሆነ እንደሚገኝ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡
በቡሌን ወረዳ ጎንጎ ቀበሌ በጸጥታ ሐይሎችና ሸማቂዎች መካከል በተከሰተው ግጭት በንብረት ላይ ጉዳት ደርሰዋል
በመተከል ዞን ቡሌን ወረዳ ጎንጎ በሚባል ስፍራ ደግሞ ትናንት በመንግስት ጸጥታ ሐይሎችና ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተገልጸዋል፡፡ በስፍራው ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ ታጣቂዎች ከሰዓታት የተኩስ ልውውጥ በኃላ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን በተኩስ ልውውጡ አራት መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን አንድ የአካባቢው ነዋሪ አብራርተዋል፡፡
የድባጢ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ መስፍን ተገኘ በወረዳው በርበር ቀበሌ ታጣቂዎች የቀበሌውን ቢሮው አቃጥለዋል መባሉን ያስተባበሉ ሲሆን ባለፈው አርብ ምሽት ማንነታቸው በወል ያልታወቀ በለብነት ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች ያሏቸው ሰነዶችን ለማቃጠል ሙከራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ጥቃት ለመፈተመ ከጫካ የመጣ ሐይል እንደለለ በመግለጽ በርበር በተባለ ቦታ ከዚህ ቀደም የማዘጋጃ ቢሮ ተቃጥሎ እንደነበር አክለዋል፡፡
ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አዛዥ አማካሪ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ያደረኩት ሙከራ አልተሳካም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቅምት 1/2018 ባወጣው ዘገባው በመተከል ዞን ድባጢ፣ቡሌን እና ወምበራ ወረዳዎች ከአሮሞ ነጻነት ሰራዊት(ኦነግ ሼኔ) እንቅስቃሴና ከጸጥታ ስጋት ጋር በተያዘ ሰዓት እላፊ መጣሉን እና አንድ አንድ ቦታዎች ላይ ነዋሪዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ አመልክተዋል፡፡ በዘገባው በተጠቀሱት አራት ክልሎች የሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ መብት በተሟላ ሁኔታ መፈጽም የሚያስችል እርምጃ በአፋጣኝ ሊወሰድ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ገልጸዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ