ዋና መቻል ምን ያህል ህይወትን ሊታደግ ይችላል?
Description
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) መረጃ በዚህ በጎርጎሮሲያውያኑ ዓመት ብቻ በሜዲትራኒያንን ባሕር ላይ 675 ስደተኞች መሞታቸው ተመዝግቧል። በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት ብቻ፤ ድርጅቱ ይፋ እንዳደረገው በጣሊያኗ ላምፔዱሳ ደሴት አቅራቢያ ሁለት ጀልባዎች ሰጥመው ቢያንስ የ 27 ስደተኞች ሕይወት አልፏል። ናትናኤል መኩሪያ በባሕር ተሰዶ አውሮፓ የገባ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው። እንደነገረን አውሮፓ ለመግባት እና ባሕር ለማቋረጥ ጀልባዋ ላይ ሲወጣ ዋና አይችልም ነበር። ስለ ዋና የሚያውቀው ነገር ስላልነበረ እና በውኃ ላይ መጓዝ ከመሬት ላይ ጉዞ የተለየ ነገር ይኖረዋል ብሎ ስላልገመተም ስጋትም አልነበረውም።
እሱም ሆኑ አብረውት ጀልባዋ ላይ የነበሩት ስደተኞች የውኃ ላይ መንሳፈፊያ ጃኬት አልነበራቸውም። ማን ዋና ይችላል አይችልም የሚለውንም አናውቅም አልተጠያየቅንም ይላል። « እኔም በዛ ሰዓት ባሕር ላይ ከወጣሁ በኋላ አስፈሪ ስለነበረ በእራሴ ስጋት ውስጥ ነበርኩ። መብረቅ አለ፣ ዝናብ አለ፤ ማዕበል፣ የሰው ጩኸት አለ። እነዛ ነገሮች ሲደማመሩ ሌላ አለም ውስጥ ነው የሚገባው። »
በመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ ምስሎች እንደሚጠቁሙት የሜዲትራንያንን ባሕር ለማቋረጥ የሚሞክሩ ስደተኞች አብዛኞችን ጊዜ በጎማ ጀልባ ላይ ተሳፍረው እና ጀልባዋም ከመጠን በላይ ሰዎችን አሳፍራ ስትጎዝ እንደነበር ያሳያሉ። ለጀልባ መስመጥ በዋናነት የሚጠቀሰውም ይኸው ከአቅም በላይ ሰዎችን ማሳፈር ነው። እንደው ናትናኤል በባሕር ላይ ካደረገው ጉዞ በመነሳት....
ዋና መቻል ምን ያህል ባህር ላይ ሕይወትን ሊታደግ ይችላል ይላል?
« ይህንን ጥያቄ በየዋህነት ከመመለስ እውነታው ላይ መነጋገሩ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ንፋስ አለ፣ ዝናብ አለ፣ ማዕበል አለ። የመትረፍ እድሉ 20 እና 10 ፐርሰንት ከሆነም ትልቅ ተስፋ ነው። ምክንያቱም ሰዎች ባህር ውስጥ መስመታቸውን የምንሰማው ትርፍራፊ ዜና ከሰማን በኋላ ነው። የመትረፍ እድሉ በጣም ጠባብ ነው። ምናልባት ሰው ዋና እንኳን ቢችል ለተወሰነ ሰዓት ውኃ ላይ ሊቆይ ችላል። ይህ ግን እንተርፋለን ማለት አይደለም።»
ናትናኤል ከነበረው ተሞክሮ ለመስመጥ ምክንያት ነው የሚለውን እና ተሳፋሪዎች ቢያደርጉ ጥሩ ነው የሚለውንም ገልፆልናል። «ብዙ ጊዜ ጀልባዋ የመገልበጥ አደጋ የሚያጋጥማት የባላንስ መሳት ነው። ሰዎች ተረጋግተው ባለመቀመጣቸው፣ በመጮሀቸው። በሚፈጠረው ፓኒክ ከጀልባው ይልቅ ውኃውን ያምኑታል። ዘለው ይገባሉ። ዋኝቼ እተርፋለሁ የሚል እምነት አላቸው። በሰው ጉልበት እና በዋና የሚታለፍበት አይደለም። ተረጋግቶ መቀመጥ፣ ጩኸት መቀነስ ውኃ ዳር ሲቃረቡ እስከመጨረሻው ውኃው ጉልበት ድረስ እስኪደርስ ድረስ መጠበቁ ለመትረፍ ይረዳል ብዬ ነው የማስበው»
ዋና የምትሰለጥነዋ ወጣት
ማርያም ሙሴ የ 20 ዓመት ወጣት እና የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ናት። ዋና ለመማር ፍቅሩ ያደረብኝ ገና የ9 ዓመት ልጅ ሳለው ነው ትላለች፤ ዛሬ ላይ አራት ዓይነት የዋና ስልቶች ትችላለች። «በፊት ልጆች ሲሰሩ አይ ነበር። አሰልጣኜ ኃይቅ ላይ ያሰራቸው ነበር። እና ሄደው ተወዳድረው ሲመጡ አይ ነበር። የኔ ታላላቆች፤ ወንድሜም ይሰራ ነበር። ሰፈር ውስጥ የሚወራ ነገር አለ። ሀዋሳን ወክለው ይባል ነበር። እና አሰልጣኜን እባክህ አንድ ሳምንት እንኳን አሰልጥነኝ አልኩት፤ እናቴ ታበረታታኝ ነበር። መሰልጠን በጀመርኩ በአራት ወሬ አዳማ ላይ በውድድር ተሳትፌ 2ኛ ወጥቼያለሁ። በጣም ብዙ ሜዳሊያዎች አሉኝ» ማርያም ዋና የተለማመደችው በውኃ ገንዳ ውስጥ ቢሆንም ሐይቅ ላይ መዋኘቱ ብዙም እንግዳ ነገር አልሆነባትም። « አካባቢያችን ላይ ተጠራርተን እየሄድን እንዋኛለን። ስልጠና ከመጀመሬም በፊት። »
ወንድይፍራው ሰለሞን ፤ በብሔራዊ ደረጃ በውኃ ዋና የተወዳደረ እንዲሁም ማርያምን ጨምሮ በሀገር ደረጃ የሚወዳደሩ ዋናተኞችን ፣ ዋና መማር የሚፈልጉ ሕጻናት እና ወጣቶችን በሀዋሳ ከተማ የሚያሰለጥን ወጣት ነው። «አጋጣሚ ሆኖ ቤታችን ሀዋሳ ሐይቅ ዳር ነው።እዛው እየተቦጫረቅን ነው ዋና የለመድነው።ከዛ በኋላ 94 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማራቶን ተወዳዳሪ ሆኜ የጀመርኩት። በ2006 በምክትል አሰልጣኝነት እና በተወዳዳሪነት ቆየሁ። ከ 2006 በኋላ በዋና አሰልጣኝነት ሠርቼያለሁ። »
በአካባቢያችን የውኃ ዋና ክለቦች ባለመኖራቸው «አልፎ አልፎ ውድድሮች ሲኖሩ ብቻ ነው በከፍተኛ ደረጃ ተወዳዳሪዎችን የምናሰለጥነው» የሚለው ወንድይፍራው በዚህም የተነሳ በዋንኛነት የሚያሰለጥናቸው በራሳቸው ዋና መለማመድ የሚፈልጉትን ነው።
በኢትዮጵያውን ዘንድ ዋና የመልመድ ፍላጎት ምን ይመስላል?
ሐይቅ ዳር እንደመኖሩ ሳይሆን በአጠቃላይ ኢትዮጵያውስጥ ዋና የመልመድ የሰዎች ፍላጎትም ከፍተኛ ነው ይላል። «በጣም ፍላጎት አለው። ግን የውኃ ዋና በጣም አደጋ አለው። ግን በጣም ለሕይወት አስፈላጊ ነገር ነው። ውኃ ዋና መልመድ ለጤናም ተመራጭ እና የሚመከር ነው።ማንኛውም ሰው መልመድ አለበት ባይ ነኝ። ብዙዎች ልጆቻቸውን ይዘው ለማስለመድ ይፈልጋሉ። » ይላል።
ወንድይፍራው ከልጅነት ጊዜው ጋር ሲያነፃፅር አሁን ላይ ወላጆች ልጆቻቸውን ዋና እንዲለምዱ ሊወስዱበት የሚችሉባቸው በርካታ የውኃ ገንዳ ያለባቸው አማራጮች አሉ። እሱም የሚያሰለጥናቸው ልጆች መጀመሪያ ዋና የሚለምዱት ገንዳ ውስጥ ነው። « የስልጠናው መጨረሻ ሐይቁ ላይ መዋኘት ነው። ሐይቅ ላይም ማለማመድ እንችላለን። ዋናው ድፍረት ነው። ግን ቶሎ ለመልመድ ፑል የተሻለ ነው። »
ወንድይፍራው ወላጆቹ ዋና እንዲማር አላበረታቱትም። ግን ውኃ ዳር መኖሩ ረድቶታል። «እኛ ስንለምድ፣ ከብት ስንጠብቅ ውኃ ዳር ነው ሳር የምናበላቸው። እነሱ ሲበሉ እኛ ደግሞ ትላልቆቹ ሲዋኙ አይተን ውኃ ውስጥ እንገባ ነበር። ባህላዊ አወኛኘት ነው የምንለምደው። ከዛ በኋላ ነው በአሰልጣኝ የለመድኩት። ለወጣቱ የምመክረው ዋና መቻል የሕይወት እስትንፋስ ነው የሚል ነው። የሰው ልጅ በሕይወቱ ምን እንደሚገጥመው አይታወቅም። መቻል ጥሩ ነው። ሁሉ ነገር እጃቸው ላይ ነው ያለው። መሰልጠን ይችላሉ። ዋና ለምደው እንደኔ ስሜቱን ቢያውቁ ደስ ይለኛል። »