የምጣኔ ሀብት ምሁር ተመራማሪና ካህን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ዋሴ
Description
የ43 ዓመት ጎልማሳ ናቸው ከእድሜያቸው አብዛኛውን በትምሕርትና በምርምር ሥራ ነው ያሳለፉት። በአሁኑ ጊዜ ቦን ከተማ በሚገኝ በአንድ የጀርመን የልማትና የዘላቂነት ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ይሠራሉ። በልጅነታቸው ብዙም ትኩረት ባልሰጡት፣ ሆኖም ዩኒቨርስቲ ከገቡ በኋላ ይበልጥ ፍላጎቱ ባደረባቸው በአብነት ወይም በቆሎ ትምሕርትም ገፍተው ለዲቁናና ለክህነት ማዕረግ በቅተው ከሀገር ቤት አንስቶ በሚኖሩባት በጀርመን ሀገርም እያገለገሉ ነው፤ ጀርመን የዶክትሬትና የድኅረ ዶክትሬት ትምህርታቸውንና ምርምራቸውን የሰሩት ኢትዮጵያዊው የምጣኔ ሀብት ምሁር እና ካህን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ዋለ። አባታቸው ወጣቱ ያብባል ሕክምና እንዲማሩ ነበር የሚመክሯcቸው ። እርሳቸው ግን ስሙ ሲጠራ ደስ የሚያሰኘኝ ያሉትን ኤኮኖሚክስን መረጡ።
ዶክተር ያብባል አሁን በሚሠሩበት በGerman Institute of Development & Sustainability በእንግሊዘኛው ምህጻር IDOS የጥናትና ምርምር ተቋምውስጥ ከሚያከናውኗቸው የምርምር ተግባራት በተጨማሪ በፖሊሲ አማካሪነትም ይሠራሉ። ይበልጥ የሚያተኩሩት ደግሞ በልማት ፋይናንስ ላይ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ጀርመን የመጡት የዛሬ 18 ዓመት ነው። ያኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ ተማሪ ነበሩ። ሰሜን ጀርመን በሚገኘው የኪል ዩኒቨርስቲ የአጭር ጊዜ ምርምርና ጥናት አድርገው ተመለሱ። የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ2000 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት መሥራት በጀመሩ በሁለት ዓመት የነጻ ትምሕርት እድል አግኝተው ለዶክትሬት ዲግሪ ትምሕርት ተመልሰው ወደ ኪል ዩኒቨርስቲ መጡ።
የዶክትሬት ዲግሪ ትምሕርታቸውን ከጨረሱ በኋላ እዚሁ ጀርመን በጎቲንገን ዩኒቨርስቲ የድኅረ ዶክትሬት ዲግሪ ምርምር ቀጥለው በዩኒቨርስቲው በምርምርና የማስተርስ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማርም ለ8 ዓመታት ቆይተዋል። በምርምር ፣ በፖሊሲ አማካሪነትና በስልጠና ተግባራት ላይ በተሰማራው በቦኑ በIDOS አይዶስ ወይም በጀርመን የልማትና ዘላቂነት ተቋም ውስጥ በተመራማሪነት መሥራት ከጀመሩ ደግሞ አራት ዓመት አልፏቸዋል። ዶክተር ያብባል በጀርመን በትምሕርቱም ሆነ በሥራ ቆይታቸው በርካታ ምርምሮችን አካሂደዋል። አብዛኛዎቹም በልማት ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ዶክተር ያብባል የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ብቻ አይደሉም፤ ካህንም ጭምር እንጂ ። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር በደብረ ታቦር ከተማ ተወልደው ያደጉትና የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን የተከታተሉት ዶክተር ያብባል ሁለተኛ ደረጃን እስኪጨርሱ ድረስ ትኩረታቸው በቀለም ትምሕርት ላይ ብቻ ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከገቡ በኋላ ግን የቤተ ክህነት ትምሕርትም ትኩረታቸውን ሳበ። ይህን ፍላጎታቸውንም ዩኒቨርስቲ በትምሕርት ላይ ሳሉ በተፈጠረ አጋጣሚ ማሳካት ቻሉ።
ዶክተር ያብባል መደበኛ ሥራቸውንና የክህነት አገልግሎታቸውን ከሥራና ከክህነት አገልግሎት ጋር አቅማቸው በፈቀደ መጠን ጎን ለጎን ለማስኬድ ለቤተሰባቸውም በቂ ጌዚ ለመስጠት እንደሚሞክሩ ተናግረዋል ። በአሁኑ ጊዜ በብሬመን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ደብር አስተዳዳሪ ዶክተር ያብባል በተለያዩ የጀርመን ከተሞች በሚገኙ ዐብያተ ክርስቲያንም አገልግሎት ይሰጣሉ።
ሙሉውን ዝግጅት
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ