የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ለጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል
Description
ከሶማሊያ ራሷን ነጥላ እንደ ሀገር የምትንቀሳቀሰው የሶማሊላንድ 6ኛ ፕሬዝዳንት ሆነው በምርጫ ያሸነፉት አብዲራህማን ሞሃመድ ትናንት ማክሰኞ ለጉብኝት አዲስ አባባ ገብተዋል።የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንቱ አዲስ አበባ መግባታቸውን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞትዮስ አቀባበል ሲያደርጉላቸው የሚያሳይ በፎቶ የተደገፈ መረጃ ይፋ አድርጓል።በኢትዮጵያ በኩል ግን እስካሁን ድረስ በይፋ ምንም የተገለፀ ነገር የለም
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉብኝቱ "ወዳጅነት እና የትብብር ግንኙነትን ለማጠናከር አስፈላጊ" መሆኑን ጠቅሶ "በመጓጓዣ፣ በንግድ፣ በደኅንነት እና በሌሎች የሁለትዮሽ መስኮች የትብብር መስኮችን ያሰፋል" ሲል አስታውቋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታህሳስ 22 ቀን 2016 በአንድ ወር ውስጥ ይፈፀማል የተባለና ለኢትዮጵያ የባህር በር ያስገኛል የተባለለት በ"ሰበር ዜናነት" የተገለፀ የመግባቢያ ስምምነት ቢፈራረሙም ጉዳዩ ከሶማሊያ፣ ግብጽ የአረብ ሊግ እና ሌሎችም ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞት ተግባራዊ ሳይሆን ሁለት ዓመት ሊሞላው ሁለት ወራት ቀርተውታል።
ስለ ጉብኝቱ እስካሁን የሚታወቀው
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን መሃመድ ትናንት ማክሰኞ አዲስ አበባ መግባታቸውን የሚያሳዩ ይፋዊ የሀገራት መሪዎች አቀባበልን የሚያሳዩ ፎቶዎች ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቴ አንድ አካል ናት በምትላት ራስ ገዝ ሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጋርተዋል። ለፕሬዝዳንቱ አቀባበል ያደረጉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞትዮስ መሆናቸው በፎቶው ይታያል።
ዶቼ ቬለ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን አዲስ አበባ መግባታቸውን በኢትዮጵያ ከሚገኘው የሶማሊላንድ "የግንኙነት ጽ/ቤት" አምባሳደር አደም ገዲ ደውሎ አረጋግጧል። "ፕሬዝዳንቱ የተጣበበ ጊዜ ያላቸው በመሆኑ ለቃለ መጠይቅ ሊገኙ እንደማይችሉ" ላቀረብነው ጥያቄ አያይዘው መልሰዋል።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጉብኝቱ "ወዳጅነት እና የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር አስፈላጊ ደረጃ ነው" ሲል ጽፏል። አክሎም "በመጓጓዣ፣ በንግድ፣ በደኅንነት እና በሌሎች የሁለትዮሽ መስኮች ውስጥ የትብብር መስኮችን ያሰፋል" ሲል ከዚህም አልፎ በምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት "በቀጣናው በጋራ የደኅንነት ሥጋቶች ጋር የተያያዙ አስፈላጊ ውይይቶችን ለማድረግ ያስችላል፤ የአዲስ አበባ እና የሐርጌሳን ግንኙነትም ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ያስገባል" ብሏል።
ሚኒስቴሩ አክሎ ይህ ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል "የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በጽኑ የተመሠረተ መሆኑን ያመለክታል፤ ቀጣናውም ደኅንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል" ሲል አስፍሯል።
የዚህ ጉብኝት የጊዜ ትርጉም ምን ይሆን ወይም ለምን አሁን?
የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት በሰላማዊ መልኩ ከቀድሞው የራስ ገዟ ፕሬዝዳንት ሙሴ ባሂ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ ኬቢኔያቸውን ያዋቀሩት በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር። ቃጣርን ጨምሮ ወደሌሎች ሀገሮችም ለጉብኝት ተጉዘዋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የ20 ኪሎ ሜትር ለንግድ እና ለ50 ዓመት የሚያገለግል የባሕር ኃይል መቀመጫነት የሚሆን የባሕር በር ለመስጠት ያደረጉትን የመግባቢያ ስምምነት በጥንቃቄ ዳግም እንደሚያጤኑትም በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን በዚሁ አሳሪ ያልሆነ ስምምነት ወይ የመግባቢያ ፊርማ ምክንያት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ተካርሮ የነበረው የዲፕሎማሲ ውዝግብ አሁን በእጅጉ ረግቦ ግንኙነቱ የታደሰ ይመስላል። በቱርክ አሸማጋይነት ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው በሚል ሶማሊያ ውድቅ ከማድረግ ባለፈ ስምምነቱ “ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው” ያለችው ይህ ቁልፍ ጉዳይ ሳይተገበር ሁለት ዓመት ሊሞላውም ነው።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ሙሃሙድኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ስታስመርቅ በስፍራው ከመታደም አልፈው ከሁለት ቀናት በፊትም ዝርዝሩ በግልጽ ይፋ ያልሆነ በአዲስ አበባ የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል። ይህም በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ሰላም ለመውረዱ ጥሩ አብነት ተደርጓል።
ይህንን የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ጉብኝት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል" ከማለት በቀር ዝርዝር የውይይቱን ጭብጥ ይፋ አላደረጉም።
ጉብኝቱ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት የሚውስድ ነው ተብሏል
ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት የሚውስድ ነው የተባለለት እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋባዥነት የተደረገ ነው የተባለው ይህ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት ጥቂት የማይባሉ የውጭ ጉዳይ፣ የገንዘብ፣ የመዋዕለ ንዋይ ዘርፎችን የሚመሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ወይም የካቢኔ አባሎቻቸውን ያካተተ ከመሆኑም በላይ የሶማሊላንድ የጦር አዛዥ እና የደኅንነት ጉዳዮች ኃላፊዎችን ጭምር ያሳተፈ መሆኑ በአካባቢያዊ ደኅንነት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ለመነጋገር ማሰባቸውን ይጠቁማል።
ከሶማሊላንድ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ደግሞ የፕሬዚዳንት ኢሮ ጉብኝት "በሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን የሚያመለክት" እንደሆነና አስተዳደራቸው የሐርጌሳን "ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ እና በአህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ እና ወሳኝ ተዋናኝ በመሆን ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ያሳየ" ተደርጎ ተጠቅሷል።
ጉብኙቱ ምንን ያመለክታል?
የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት አዲስ አበባ እና ሐርጌሳ አድርገውት የነበረውን የመግባቢያ ስምምነት ዳግም ለመመልከት፣ ሶማሊያን፣ ግብጽን፣ አረብ ሊግን ጨምሮ ሌሎችን ያስቆጣውን ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠት የሚለው ጉዳይ (የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ ባለፈው ሳምንት ዱባይ ውስጥ በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ እውቅና መስጠትን በተመለከተ አሜሪካ በቅድሚያ ለሶማሊላንድ እውቅና ከሰጠች ለሌላው ቀላል ነው በማለት በጉዳዩ ላይ ለዘብተኛ አቋም ስለመያዙ መጠቆማቸው ይታወሳል) ምናልባትም በሌሎች ማለትም በፀጥታ፣ የበርበራ ወደብን በመጠቀም እና ከበርበራ ቶጎውጫሌ አዲስ የተገነባወኡን የአስፋልት መንገድን በመጠቀም ንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን ይበልጥ ለማሳደግ ያለመ ስለመሆኑ ይጠቁማል።
ይህንን የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ጉብኝት ተከትሎ ከሶማሊያ በኩል እስካሁን ምንም ነገር አለመባሉም ይህንን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ አካሄድ እስካልመጣ ድረስ በኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘቷ ጉዳይ ላይ በቅርቡ አወንታዊ ምላሽ እና አቋም እያንፀባረቀች በመሆኑ ነው።
የሶማሊላንድ የውስጥ ኹኔታ ምን መሳይ ነው?
ሶማሊላንድ ላለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት ራሷን እንደ አንድ ነፃ ሀገር የምትቆጥር ሲሆን የራሷ ሕገመንግሥት፣ የመገበያያ ገንዘብ፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ የጦርና፣ የፀጥታ ኃይል፣ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የባህር ላይ ግዛቷን ከባህር ላይ ወንበዴዎች የጠበቀች፣ ሰላማዊ ምርጫ እና የሥልጣን ርክክብ በማድረግ በአካባቢው ካሉ ሀገራት የተሻለ ልምድ ያላት፣ በምስራቅ አፍሪካ ቁልፍ ስልታዊ ስፍራ ላይ መገኘቷ በብዙዎች የሚታመን ግን እስከዛሬ ድረስ ዓለም አቀፍ መድረክ እውቅና ማግኘት ያልቻለች አስተዳደር ናት
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ