የሽግግር መንግስት ምስረታ ጥሪ
Description
የንቅናቄው አባላት እነማን ናቸው?
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 4 የተቃዋሚ ፓርቲዎችና 3 ታዋቂ ግለሰቦች በትግራይ እስከ ቀጣዩ ምርጫ የሚያሻግር ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ አቀረቡ። ፓርቲዎቹ ይህን ለማሳካት የሚያስችላቸውን አደረጃጀት መፍጠራቸውንና አሁን ያለውን የጦርነት ድባብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚጥሩም ባወጡት የጋራ መግለጫቸው አመልክተዋል።
«የትግራይ ለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ» በሚል የተደራጁት ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ፣ ባይቶና፣ ዓረና ትግራይና ስምረት ፓርቲ ናቸው። ከታዋቂ ግለሰቦች ደግሞ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስቴር ኤታማዦር ሹም ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ፣ የቀድሞ አየር ሃይል አዛዥ ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖትና የቀድሞው የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አሰፋ አብርሃ በንቅናቄው ተካተዋል ያሉን የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ ሊቀመንበርና የንቅናቄው የኮሚዩኒኬሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከበደ አሰፋ ናቸው።
«ሁኔታዎች እየተካረሩ ወደ ጦርነት እንዳያድጉ ለማድረግ እንደዚሁም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ውል በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር፤ በትግራይ ውስጥ አቃፊ ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲመሰረትና ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ምህዳር ለመፍጠር ዓላማ ያደረጉ 4 ፓርቲዎች ማለትም ትንሳኤ 70 እንደርታ፣ ባይቶና፣ ዓረና እና ስምረት፤ እንደዚሁም በትግራይ ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ረዥም የትግል ታሪክ ያላቸው እንደጀነራል ጻድቃን፣ ጀነራል አበበ። ተክለሃይማኖት እና አቶ አሰፋ አብርሃ በግለሰብ ደረጃ ያሉበት የትግራይ የለውጥ ፈላጊ ሃይሎች እንቅስቃሴ የሚል አደረጃጀት ፈጥረን እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው።»
የጦርነት ድባብ
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገውና ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የታገደው ህወሐት አሁንም የክልሉን ፖለቲካ ይዘውራል። የፌደራል መንግስት ህወሐት ከሕገመንግስትና ከፕሪቶሪያ ውል ባፈነገጠ መልኩ ከኤርትራ መንግስት ጋር በማበር ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው፤ በሐገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አማፅያንም ይረዳል በማለት ይከሳል። ሕወሐት በበኩሉ ከኤርትራ ጋር « የሕዝብ ለሕዝብ» ያለውን ግኑኝነት እንደሚያጠናክር በቅርቡ ባካሄደው የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ አረጋግጧል።
ከትግራይ የጸጥታ ሐይሎች እራሳቸውን በመነጠል በዓፋር፣ በምዕራብ ትግራይና በሌሎች ግንባሮች የተደራጁ ሃይሎችም በትግራይ ያለውን የፖለቲካ ምስቅልቅል በሰላም ካልተፈታ የትጥቅ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ይገልጻሉ። አሁን በትግራይ ያለው ሁኔታ በጊዜ መላ ካልተበጀለት ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑን አቶ ከበደ ይገልጻሉ።
« ተሰባስበን አንድ ነገር ማድረግ ካልቻልን ጦርነቱ የማይቀር ነው የሚል ግምገማ ነው ያለን።»
«የትግራይ ለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ» የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ እስከ ቀጣዩ ምርጫ የሚያሻግር የሽግግር መንግት እንዲመሰረትም ጥሪ አቅርቧል በመግለጫው። አቶ ከበደ አሰፋ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
እስከ ምርጫ የሚያሻግር ጊዚያዊ መንግስት ስለማቋቋም
«የጊዚያዊ አስተዳደር ይቋቋም ስንል ሁሉንም ሃይሎች ያሳተፈ፤ ወደ ቀጣዩ ምርጫ የሚያሻግረን የጊዚያዊ አስተዳደር ማቋቋም ነው። ይህ ጊዚያዊ አስተዳደር ከላይ እስከታች ጊዚያዊ ምክርቤቶች ያሉበት፤ ምክርቤቶች የሚቆጣጠረው ካቢኔና በየደረጃው ያሉ የሥራ አስፈጻሚዎች ይኖሩታል። ስለዚህ በየደረጃው ያሉ ጊዚያዊ ምክርቤቶች የሥራ አስፈጻሚውን የሚቆጣጠሩበት አሰራር ተዘርግቶ፤ እስከ ቀጣይ ምርጫ ካቢኔ ላይ ያለውም ከሁሉም የተሰባጠረ እንዲሆን፤ነገር ግን የመንግስት ስራ ብቻ እንዲሰራ፤ የመንግስት ሐብትና ጊዜ ለፓርቲ አላማ እንዳያውል፤ ለቀጣዩ ምርጫ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው»
እንቅስቃሴው በትግራይ በተካሄደ ጦርነት «ጥፋተኞች» የተባሉት ላይ የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንደሚሰራና አሁን ያለው የትግራይ የጸጥታ ሐይል በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ከተደረገ በኋላ «አስፈላጊ» ያለውን ማሻሻያ እንደሚያደርግም ንቅናቄው አክሏል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ