DiscoverDW | Amharic - Newsየኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኞች ግጭት
የኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኞች ግጭት

የኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኞች ግጭት

Update: 2025-10-16
Share

Description

በኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በድጋፍ እጥረት ችግር ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው ። እንደ የአከባቢው ነዋሪዎች አስተያየት ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት የፈጠረው ችግር አልተቀረፈም ። በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት አንዳንድ ቦታዎች ላይ እስካሁንም ያልተከፈቱ መንገዶች መኖራቸው ነው የሚነገረው ።



የሶማሊ ክልልን የሚያዋስነው የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ዋጭሌ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው በሰጡት አስተያየት፤ «በኛ አከባቢ ግጭት ነበር፤ ግን አሁን ግጭቱ ቆሞ ሰው ግን በኛ ወረዳ በስፋት ከሚኖሩበት አከባቢ እንደተፈናቀለ ነው» በማለት በአዋሳኝ አከባቢዎቹ በስፋት የመንግስት ፀጥታ አካላት እንደሰፈሩበት አስረድተዋል ፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር የተቀሰቀሰውና የሰው ሕይወት መቅጠፍን ጨምሮ በርካቶችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው ግጭት ለጊዜው መቆሙን የገለጹት አስተያየት ሰጪው የዋጭሌ ወረዳ ነዋሪ፤ አሁን ላይ ወደ ከተሞች አከባቢ የተፈናቀሉት የአዋሳኝ ቀበሌያት ነዋሪዎች እስካሁንም ወደ ቀዬያቸውና ነባሩ ኑሯቸው እንዳልተመለሱ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ግጭት በነዚህ አከባቢዎች ላይ እየተካሄደ አለመኖሩን ግን አንስተዋል፡፡



የመንገዶች እና እንቅስቃሴዎች ክፍት አለመሆን



ሌላው አስተያየት ሰጪ የሞያሌ ከተማ ነዋሪ ክረምቱን በተለያዩ የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ላይ ተከስቶ የነበረው ግጭት ብዙ ሕዝብ ተቀላቅለውና ተከባብረው በሚኖሩባት ሞያሌ ከስጋት የዘለለ ግጭት አለመስተዋሉን በመግለጽ፤ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ ግን የሰዎችን እንቅስቃሴ የገደበው ግጭት አሁንም ድረስ ጥላው አለመገፈፉን አስረድተዋል፡፡ «በሶማሌ ክልል በኩል በወሰን አከባቢዎቹ ወረዳዎች ግንባታ ጀምረዋል፡፡ በኦሮሚያ በኩል ግን ቅሬታውን ያሰማው ሕዝብ በመንግስት በኩል ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል” በማት ምንም ግጭት በማይስተዋልበት ባሁን ወቅት የሰዎች እንቅስቃሴ ግን ከስጋት የተነሳ እንደተገደበ መቀጠሉን ነው ያመለከቱት፡፡ በዳስ እና ዋጪሌ ወረዳዎች በተለይም ወደ አዋሳኞቹ የሁለቱ ክልሎች አከባቢ ሰዎች ከቦታ ቦታ መንገሳቀስ ተወስኖ መዝለቁን በማስረዳትም በሞሌ ግን ከስጋት ውጪ ነባር እንቅስቃሴው አለመስተጓጎሉን ጠቅሰዋል፡፡



የዋጭሌ ወረዳው አስተያየት ሰጪ ነዋሪውም፤ "የእኛ ወረዳ ዋጭሌ አሁን የሚተዳደረው በቦረና ነጌሌ ምስራቅ ቦረና ስር ነው” በማለት ወደ ነጌሌ ቦረና ከሚወስደው የፌዴራል መንገድ ውጪ ሌሎቹ ብዙም ሰዎች እየተንቀሳቀሱበት አይደለም ይላሉ፡፡



የተፈናቃዮች መቸገር



ኢትዮጵያ ውስጥ በአዋሳኝ የሁለቱ ክልሎች ወረዳዎች አከባቢ ከሃምሌ ወር ጀምሮ እስከ መስከረም ለሁለት ወር ግድም አልፎ አልፎ በተስተዋለው ግጭት የተፈናቀለው ሕዝብ ቁጥር እጅግ ብዙ መሆኑንም የገለጹት አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪዎች፤ ከአከባቢው የተፈናቀሉት ነዋሪዎች ብርቱ ችግር ውስጥ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ተፈናቃዮች በከተማ አከባቢ ተጠልለው የሚገኙ መሆኑንና ማኅበረሰቡ አርብተው አደር እንደመሆናቸው ለራሳቸውም ሆነ ይዘው ለተፈናቀሉት ከብቶቻቸውም በምግብና ውኃ እጥረት እንደተቸገሩም አክለዋለው ገልጸዋል፡፡ አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ ለጊዜው እየተካሄደ ያለው ግጭት ባይኖርም ስጋቱ ግን ስላልተቀረፈ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬያቸው ለመመለስም አስተማማኝ ሁኔታዎች አለመኖራቸውን ጠቁመዋልም፡፡



በዚህ በኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በተፈጠረው ግጭት ከ288 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ሪፖርት ያመለከተው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ይህ የተፈናቃዮች ቁጥር ትክክለኛ መሆኑንም ከሁለቱ ክልሎች ባለሥልጣናት ማረጋገጡን አስገንዝቧል፡፡ ዓለማቀፋዊው የሰብአዊ ተቋሙ ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በተደጋጋሚ በተፈጠረው ግጭቱ በሰው ሕይወትና በመሰረተልማት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሷልም፡፡ የአገር መከላከያ ሰራዊት በአዋሳኝ የሁለቱ ክልሎች አከባቢ ላይ ተሰማርተው አከባቢውን ማረጋጋታቸውንም የገለጸው የኦቻ ሪፖርት ግጭት ቢያቆምም በየጊዜው የሰዎች መፈናቀል ግን አለመገታቱን ጠቁሟል፡፡



ለግጭቱ ምን መፍትኄ ተቀመጠ



የሶማሊ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ግጭቶቹ በዘላቂነት እንዲቀረፍና ተፈናቀሉ የተባሉ የአዋሳኝ አከባቢው ማህበረሰብ ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ መንግስት እንዴት እየሠራ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን ለመጠየቅ ለአከባቢው ባለሥልጣናት እና ለሁለቱ ክልሎች የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በመደወል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረው ጥረት አልተሳካም፡፡ ከዚህ በፊት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተው የነበሩት የሶማሊ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ አደም ግን አዲሶቹ የወረዳ መዋቅሮች ወሰን የመግፋት ፍላጎት የሌለውና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተልማት ዝርጋታ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡



አስተያየት ሰጪው የሞያሌ ነዋሪ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ «አዲሱ የአስተዳደር መዋቅር ወሰን የተሻገረ ነው» በማለት በነበረው የዞን፣ ወረዳ እና ከተማ መዋቅር ላይ አዲስ መዋቅር ያወጣ ነው ይላሉ፡፡



የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ የ14 አዳዲስ ወረዳዎች መዋቅር ማጽደቁን ተከትሎ፤ እነዚህ አከባቢዎች የአስተዳደር ወሰን ይገባኛል ውዝግብ ያለባቸው ነው በሚል በአዋሳኝ የኦሮሚያ መስተዳድር አከባቢዎች ተቃዉሞ እንደገጠመው መዘገባችን አይዘነጋም።



ሥዩም ጌቱ



ማንተጋፍቶት ስለሺ



ታምራት ዲንሳ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኞች ግጭት

የኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኞች ግጭት

ሥዩም ጌቱ