የደመወዝ ማሻሻያ፤ በትግራይ ክልል የወንጀል መስፋፋትና የተሳሳተ ወሬ የተናፈሰባት አትሌት
Description
ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ፤ በትግራይ ክልል የወንጀል መስፋፋት እና የተሳሳተ መረጃ የተናፈሰባት አትሌት ጉዳይ
«ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ» ፤ ዜግነት ልትቀይር የተሳሳተ ወሪ የተናፈሰባት አትሌት መቐለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች የተስፋፋዉ ወንጀል በተሰኙ ዘገቦች ስር የተሰጡ አስተያየቶች ተጠናቅረዉበታል።
ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ሊደረግ መሆኑ
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአዲሱ 2018 ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኞች «ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ» እንደሚያደርግ በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ አስታዉቋል። የደሞዝ ጭማሪዉ ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከነበረበት 4,760 ወደ 6,ዐዐዐ ብር እንዲያድግ ፤ 6,940 የነበረው የዲግሪ ተመራቂ መነሻ ደመወዝ ወደ 11,500 ብር እንደሚሻሻል ያስታወቀው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከሲቪል ሰርቪስ ውጭ በተለያዩ ዘርፎች የተሠማሩ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝም ማሻሻያ ይደረግበታል ብሏል። በማሻሻያው መሠረት ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከነበረበት 21,492 ብር ወደ 39,000 ብር ያድጋል ተብሏል።
ሰላም ለሁለም ይሁንልን የተባሉ የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የደሞዝ ጭማሪ ታሳቢ መደረጉ መልካም ነገር ቢሆንም ዋናው ፍሬ ሀሳብ ግን መንግስት የፍጆታ እቃዎች እና መሰረታዊ የግብርና ምርቶችን አቅርቦት ከ 95 % በላይ ሟሟላት አለበት። ካልሆነ አሁን በጣም የኑሮ ውድነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይደረሳል። ሙስናም ኢትዮጵያ ውስጥ ምክንያታዊና ምክንያታዊ ያልሆኑ ጦርነቶችን እነደ መነሻ በማደረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እያደረገ ይገኛል ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።
ዳዊት ለጌ ፋንታዉ በበኩላቸዉ ፤ መንግሥት ይላሉ መንግሥት ከነጋዴው ጋር በትይዩ ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍልና ለዚህ አይነት ድርጊት ተጋላጭ ለሆኑ አካላት፤ በሁሉም አይነት አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የማረጋጋት ሥራ በኃላፊነት መስራት አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት የልምድ ልውውጥ እንዲወስድ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ምክረ ሐሳብ ይለግሱለት። ሀገርም ተወዳዳሪ የሚሆነው የተሻለ አሰራር ካላቸው ሀገሮች በመኮረጅ በቀጥታ ሲተገብር ነው፤ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
ገበያው እንዲረጋጋ መንግሥት በአጭበርባሪ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም 'አብዮታዊ' እርምጃ መውሰድ አለበት። ኅብረተሰቡም አጭበርባሪዎችን 'No' ማለት ይገባል ፤በተጨማሪም ሸቀጦችን ከመጠን በላይ እየሸመተ እቤቱ ማከማቸት የለበትም ሲሉ አስተያየታቸዉን በፌስቡክ ላይ ያስቀመጡት ደግሞ ተሾመ ወልዴ ናቸዉ። በፈቃዱ አባይነህ ፀጋዬ በበኩላቸዉ ይጨመራል የተባለዉ ደምወዝ አሪፍ ነው! ግን ይህ ተጨመረ ተብሎ መንግስት ዝም በማለት የሠራተኛውን ኑሮ ማስተካከል አይቻልም። ምክንያቱም ደመወዝ እንደ ተጨመረ ጣርያ የወጣውን የሸቀጥ እቃዎች የዋጋ ንረት እና ግብር(income tax) ካልተቀነሰ ነገሩ ውኃ ውቀጣ ሆኖ ይቀራል ሲሉ ጽፈዋል። ያሬድ ፀጋዬ እንደሚሉት ደግሞ ጦርነት ካልቆመና ህዝብ እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ መስራት ካልቻለ መቼም ለውጥ አይመጣም ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። ስለደመወዝ ጭማሪው የሕዝብ አስተያየት
በትግራይ ክልል ስጋት ያሳደረዉ የወንጀሎች መስፋፋት ጉዳይ
መቐለን ጨምሮ በትግራይ ከተሞች የተስፋፋዉ ወንጀል አሳሳቢ ሆንዋል መባሉ ባለፈዉ ሰሞን የክልሉ ነዋሪዎች አስታዉቀዋል። በክልሉ በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የኅብረተሰቡን ደኅንነት ላይ ስጋት ደቅነዋል ይላሉ። እንደነዋሪዎቹ፤ ግድያ፣ እገታ እና ዝርፍያ ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች እየተፈፀ መሆኑን ገልፀዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮምሽን ህብረተሰብን ያማረሩ የወንጀል ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን አምኖ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ አስታዉቋል።
ኢማን ሃጬሳ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ፤ ይሄ ይላሉ ይሄ በመላው ኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተለመደ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። በረከት ወልዴ የተባሉ ሌላ ተጠቃሚ እንደሚሉት ደግሞ ህወሓት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የለመደውን ዘረፋ ነው በራሱ ህዝብ ላይ የጀመረው ሲሉ ነዉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት። ፍቃዱ ተፈራ ወልደማርያም በበኩላቸዉ እነዚህ ኃይሎች፣ ደሃና ኃብታም ለይተው አያውቁም እንዴ፤ ዘረፋ ከፈለጉ የሚዘረፈውን ለዬተው ማወቅ ነው አንጅ ያገኙትን መግደል ሰብዓዊነት የጎደለው አመለካከት ነው። ይኸ ሁሉ ችግር ከየት መጣ? በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተስፋፋው የዘረፋ ቡድን በትግራይ መከሰቱ በጣም ያሳዝናል። ይኸን ሁሉ ችግር ግን የወለደዉ ማን ነዉ? በዘር በጎሳ ተመስርተው በየክልሉ ሠላማዊ፣ ሰው:መለየት በማይችሉ ዜጎች ዜጋቸውን እየዘረፋ እየገደሉ ያሉት እናማን ናቸዉ? ይህ በይፋ ይታወቃል ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።ደቡብ ትግራይ ሞኾኒ ከተማ በተቀሰቀ ግጭት 6 ሰዎች ቆሰሉ
ገብሩ አሰፋ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ እዉነት ነው ችግር እየተከሰተ ነው። ይህ የማን ሴራ ዉጤት እንደሆነ ይታወቃል። ሆን ተብሎ ሰርዓት እንዲፈርሰ ባጀት ተመድቦ እየተሰራበት ይገኛል። የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያሸንፍዋል ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል። ዳዊት ፋንታዉ በበኩላቸዉ፤ ዜጎችን ህፃናትን በማገት የሥራ መስክ አድርጎ የሚንቀሳቀስን ግለሰብ/ቡድን አስረህ ቀልበው አትግደለው ወይም የዕድሜ ልክ እስራት አትፍረድበት ማለት ሌላውም ተቀልቤ እፈታለሁ በማለተ ድርጊቱ እንዲቀጥል ለወንጀለኞችም አቅም እየተፈጠረ ነው። ይህን አይነት ድርጊት አስቀድሞ ለመከላከል አለፍ ሲልም በቁጥጥር ስር ለመዋል ህውሐት የቀድሞ ልምድ ነበረው። ዛሬ እንዴት ይህ ልምድ በተፈጠረበት አካባቢ ወንጀል ተስፋፋ,,, ሲሉ አስተያየታቸዉን በእንጥልጥ አብቅተዋል።
ዜግቷን ልትቀይር ነዉ ተብሎ የተሳሳተ ወሪ የተናፈሰባት አትሌት ጉዳይ
በመጪው የመስከረም ወር ጃፓን ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሆቴል የገባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን እያካሄደ ባለበት ወቅት ከቡድኑ የተገለሉ አትሎቶች መኖራቸው ተሰምቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአስደናቂ ብቃት ዉጤታማ እየሆነች የመጣች አንዲት አትሌት ዜግነቷን ልትቀይር ነው የሚሉ መረጃዎች በማኅበራዊ መገናኛ እና በአንዳንድ ሚዲያዎች ተናፍሶ ነበር ። በዚህ ርዕስ ስር ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤ አዎል ጂቢር የተባሉ አስተያየት ሰጭ ፤ ኢትዮጵያዊነት በዶላር የሚለወጥ አይደለም።ማንም ይሁን ማን ኢትዮጵያን ለመካድ ያሰበን መንገዱን ጨርቅ ያርግለት፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። ሎግ አዉት የተባለ መጠርያ ያላቸዉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ፤ አትሌቶች ዜግነት የመቀየር መብት የላቸውም እንዴ? እነሱም እንደኛ ሰዎች አይደሉም? አሁንም በጥያቄ አስተያየታቸዉን ዘግተዋል። ማርዬ ዉበቱ የተባሉ ሌላዉ አስተያየት ሰጭ ፤ ትሂድ ምንም ማለት አይደለም ኢትዮጵያን እስከዛሬ አገልግላለች ሲሉ ጽፈዋል። የኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዜግነት ልትቀይር ነው መባል እና የአውሮጳ ታላላቅ ሊጎች ጅማሬ
ዜግነትዋን ትቀይራለች ተብሎ ወሪ የተናፈሰባት አትሌት መዲና ኢሳ ትባላለች። የዶቼ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ከመዲና አዲስ አበባ እንዳረጋገጠልን፤ አትሌት መዲና ኢሳ ኢትዮጵያን ወክላ በመጭዉ መስከረም ወር ቶክዮ የዓለም ሻንፒዮና ላይ በአምስት ሺ ሜትር ትሳተፋለች። አትሌት መዲና ኢሳ በአሁኑ ወቅት እንደሌሎቹ አትሌቶች ሁሉ በሆቴል ገብታ ልምምዷን እያደረገች ትገኛለች ሲል ተባባሪ ዘጋቢያችን አረጋግጦልናል። የተናፈሰዉ ወሪ የተወሰኑ ሰዎች አሉባልታ ነዉ ስትልም አትሌትዋ መናገርዋን አክሏል።
ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ
ልደት አበበ