የፓርቲዎች የመንቀሳቀሻ ሜዳ ጠበበ ወይስ ሠፋ?
Description
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በታችኛው የአስተዳደር መዋቅሮች በሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ አማራጭ የፖለቲካ ሐሳባቸውን ለማቅረብ መቸገራቸውን የዐሥራ አንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው ሰላም ጥምረት አመለከተ፡፡ በክልል ደረጃ በዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ ላይ ከሞላ ጎደል ተግባብቶ የመሥራት ሁኔታ መኖሩን የጠቀሱት የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ በበኩላቸው በታችኛው መዋቅር ይታያሉ ያላቸው ተግዳሮቶች ከመጪው አገራዊ ምርጫ በፊት መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል ፡፡
የፓርቲዎች የመንቀሳቀሻ ሜዳ ጠበበ ወይስ ሠፋ?
አቶ ዳሮት ጉምአ አሥራ አንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያሰባሰበው የሰላም ጥምረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው ፡፡ በኢትዮጵያ በ2010 የተደረገው የፖለቲካ ለውጥ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰፊ የመንቀሳቀሻ ሜዳ የፈጠረ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ዳሮት በሂደት ሁኔታዎች እየጠበቡ የመምጣት አዝማሚያ መታየቱን ይናገራሉ ፡፡ በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ወደ ማኅበረሰቡ ወርደው ሐሳባቸውን ለመሸጥ እንዳልቻሉ ነው ሰብሳቢው የገለጹት ፡፡
በታችኛው መዋቅር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች
በተፎካካሪነት በሚንቀሳቀሱበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፓርቲ አመራሮችን ማሰር ፣ ማዋከብ ፣ ስብሰባዎችን ማስተጓጎል በታችኛው የአስተዳደር መዋቅር የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸው የጥምረቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል ፡፡ ሰሞኑን ብቻ ሦስት የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋዴፓ አመራሮችና አባላት አርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ በፖሊስ ተደብድበው መታሠራቸውን ጠቅሰዋል ፡፡
በተጨማሪም በተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ በሚያደርጉ ነዋሪዎች ላይም የተለያዩ ተፅዕኖዎች እንደሚደርሱ የጠቀሱት አቶ ዳሮት "እንደዞን ፣ ወረዳ እና ቀበሌ በመሳሰሉት መዋቅሮች የተለየ የፖለቲካ አመለካከት መያዝ እንደጠላት የሚታይበት ሁኔታ ነው ያለው ፡፡ የፓርቲ ሽታ ያላቸው ግለሰቦችን ከመንግሥታዊ አገልግሎት እንዲርቁና እንዲከለከሉ እየተደረገ ይገኛል " ብለዋል ፡፡
የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምን አሉ ?
አቶ ጎበዜ አበራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርት ቤት ሰብሳቢ ናቸው ፡፡ በክልል ደረጃ በዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ ላይ ከሞላ ጎደል ተግባብቶ የመሥራት ሁኔታ አለ የሚሉት አቶ ጎበዜ ወደ ታችኛው መዋቅር አካባቢ ግን በከፊል ከአቶ ዳሮት ሀሳብ ጋር እንደሚስማሙ ተናግረዋል ፡፡
በዞኖች ላይ የሚታየው ምህዳር በአንጻራዊነት ትንሽ ጠበበ ያለ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጎበዜ " ለምሳሌ በጋሞ ዞን የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋዴፓ አመራርና አባላት ታሥረው ይገኛሉ ፡፡ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር የዞኑን ከፍተኛ አመራሮች በሥልክ ለማግኘትም ሆነ በአካል አርባምንጭ ድረስ ሄደን ለማነጋገር ብንሞክርም አግኝተን ለማነጋገርም ሆነ የሆነውን ለማወቅ እንኳን አልተቻለም " ብለዋል ፡፡
የአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ በበኩሉ የፓርቲው አባላቱ የተያዙት በፓርቲ አባልነታቸው ሳይሆን በወንጀል በመጠርጠራቸው ነው ሲል ትናንት ለዶቼ ቬለ አስታውቋል ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በከተማው ነዋሪዎች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ህግን በተከተለ መንገድ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የጠቀሱት የከተማው ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል " በአባላቱ ላይ ድብደባ ተፈጽሟል የሚባለው ፈጽሞ ሀሰት ነው ፡፡ ማንም መጥቶ ተጠርጣሪዎቹን ማየት ይችላል " ብለዋል ፡፡
ከአገራዊው ምርጫ በፊት
ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላይ በጥቅሉ የፖለቲካ ምህዳሩ የከፋ ነው የሚል ድምዳሜ የለኝም ያሉት አቶ ጎበዜ " ተስማምተን እየፈታናቸው የመጣናቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ ፡፡ እስከአሁን ውጤት ያስመዘገብንባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ ፡፡ ግን ደግሞ በታችኛው የአስተዳደር እርከን ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ተግዳሮቶች ከመጪው አገራዊ ምርጫ በፊት መፈታት ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ " ብለዋል ፡፡
ከቀድሞው የደቡብ ሕዝቦች ክልል በመነጠል ከሁለት ዓመት በፊት በተደራጀው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሁኑ ወቅት 20 ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ፡፡ በክልሉ ገዥው የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተካተቱበት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ