IOM የኢትዮጵያን የ5 ዓመታት የሥራ ፍኖተ ካርታ ይፋ አደረገ
Description
በተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ኢትዮጵያ ውስጥ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሁሉን አቀፍ ልማትና መረጋጋትን በማስፈን «የስደትና መፈናቀል ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል» ያለውን ፍኖተ ካርታ ዛሬ ይፋ አደረገ ። ድርጅቱ በእነዚህ ዓመታት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የመጀመርያው «የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና የነፍስ አድን ድጋፍ» መሆኑን ገልጿል ።
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ይፋ ያደረገው ሰነድ «የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦችን በፈቃደኝነት ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ እና ሕጋዊነቱ የተጠበቀ ወይም አስተማማኝ የስደት መንገድ ማመቻቸት» የሚሉ ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚንቀሳቀስ አስፍሯል።
ስደት እና መፈናቀል ከሰብአዊነት አንፃር ብቻ ሊፈቱ እንደማይችሉ ያስታወቀው አይ ኦ ኤም በልማት፣ መልሶ በማቋቋም፣ በሰላም ግንባታ እና በአየር ንብረት ላይ ተጨባጭ ሥራ በማከናወን መሆኑን ገልጾ፣ ለዚህ ስኬት የመንግሥትን ጨምሮ የለጋሾችን ድጋፍ እንደሚሻ አስታውቋል።
የፍኖተ ካርታው ዝርዝር ጭብጥ ምን ይዟል?
በተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የኢትዮጵያ ጽ/ቤት ዛሬ ሐሙስ ይፋ የተደረገው ፍኖተ ካርታ በግሪጎሪያን ከ2025 - 2029 ድረስ ሥራ ላይ የሚውል ነው። ማዕቀፉ የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ፣ አስቸኳይ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለመቅረፍ፣ የፍልሰት ሕጋዊ አሠራሮችን ለማጠናከር እና ማሻሻያዎችን ለማድረግ የያዘው ቁርጠኝነትን ማሳያ ተደርጓል። ሕይወትን ማዳን፣ ለመፈናቀል ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እና ደህንነታቸው የተጠበቁ የስደት መንገዶችን ማመቻቸት ትኩረት የሚደረግባቸው ስለመሆኑም ተጠቅሷል።
ድርጅቱ በአምስት ዓመታቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ዐቢይ ጉዳይ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና የነፍስ አድን ድጋፍ ሲሆን በመጠለያ፣ በጤና፣ በውኃ፣ በንፅህና እና ጥበቃ ሥርዓቶች አቅም ግንባታ ላይ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የተፈናቀሉ ማህበረሰቦችን በፈቃደኝነት መመለስ፣ ውህደት ማድረግ ብሎም ወደ ሌላ ቦታ በመዛወር ዘላቂ መፍትሔ ማዘጋጀት ሌላው የትኩረት ዘርፍ መሆኑም በሰነዱ ተዘርዝሯል።
አይ ኦ ኤም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር የሰራተኛ ፍልሰት ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ የድንበር አስተዳደርን ማሻሻል፣ ሥነ ምግባርን የተከተለ ምልመላን ማስፋፋት ሌላኛው የሥራ ትኩረቱ እንደሚሆንም ጠቅሷል።
በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ሀገራዊ ሥጋት ነው
አቶ አብርሃም አያሌው በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊና የትብብር ጥምረት ኃላፊ ናቸው። እንደ ሀገር ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ሥጋት ናቸው ተብለው ከተለዩ ወንጀሎች ውስጥ አንደኛው "በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል" መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ ሕገ ወጥ ስደትን የሚመርጡ ሰዎች በመተላለፊያ እና በመዳረሻ ሀገራት ላይ በአሸባሪዎችና በወንጀለኛ ቡድኖች ላይ ይወድቃሉ ሲሉ ይህንን ለማስቀረት የስደት እንቅስቃሴውን መደበኛ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ይህንንም ለማጠናከር የ IOM ድጋፍ ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተዋል።
"አቋርጠው [ድንበር] በሚሄዱበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት ብዝበዛ፣ የአካል ጉዳት፣ እስከ ሞት የሚደርስ አደጋ ይጋረጥባቸዋል።"
IOM በኢትዮጵያ ከ1995 ጀምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ለተጋላጭ ፍልሰተኞች እና ከስደት ለተመላሾች ድጋፍ ያደርጋል። በግጭት፣ በማህበራዊ ውጥረቶች እና በአደጋዎች ምክንያት ፍልሰት ውስብስብ ችግር ሆኗል ሲልም በርካታ ተፈናቃዮች በቂ ባልሆነ የኑሮ ሁኔታ፣ በመጠለያ እና አስፈላጊ አገልግሎቶች እጦት ይንገላታሉ ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስወገድ "የተቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት ሙሉ በሙሉ ባያሟላም" ያንን ለማድረግ "ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው" ሲል የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ያወጣው ዓመታዊ የሀገራት የዘርፍ ሪፖርት አመልክቷል።
"ንጋት ግሎባል ኢኒሽየቲቭ" የሚባል በዘርፉ የተሰማራ ድርጅት መሥራች እና ኃላፊ አቶ ዳንኤል መለሰ ድንበግ ከሚሻገረው ባለፈ የሀገር ውስጥ ፍለሰቱም በጣም ከፍተኛ የሚባል ነው ሲሉ ዘርፉ የተቀናጀ ጥረት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል። "በግብታዊነት የሚደረጉ ጉዞዎች አሉ።"
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚከናወንበት የገንዘብ ዝውውር ለምን አልተገታም?
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወነው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ ገንዘብ የሚገላበጥበት እንደሆነና በወንጀል መረብ ሰንሰለቱ ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያንም ሕጋዊ ሽፋን ያላቸው ድርጅቶች ጭምር መሆናቸው ይነሳል። ወንጀሉን የሚያሳልጠው የገንዘብ ዝውውር እንዴት ከመንግሥት የቁጥጥር አቅም በላይ ሊሆን ቻለ? የሚለውን የተጠየቁት በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊና የትብብር ጥምረት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም አያሌው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
"በአብዛኛው የጥሬ ገንዘብ ልውውጥ ነው ያለው። እሱ ደግሞ ለመቆጣጠር በጣም ከባድ ነው። ሁለተኛው የምርመራ እና የክርክር ሥርዓታችን የሚያተኩረው ሰዎቹን [ወንጀል ፈጻሚዎቹን] ማስቀጣት ላይ ነው እንጁ በሕገ ወጥ መልኩ ያካበቱትን ተከታትለን ሀብታቸውን ማድረቅ ላይ ገና ብዙ ይቀረናል።"
እንዲያም ሆኖ መንግሥት ሕጋዊ የሥራ ስምሪት ውል የሚሰጡ የመዳረሻ ሀገራትን ቁጥር በማስፋት፣ ብቁ የሰለጠኑ እና በከፊል የሰለጠኑ ፈቃደኛ ሰዎችን ወደ ውጪ ለሥራ በመላክ፣ በደላሎች እና አባባሽ ተቋማት ላይ ርምጃ ለመውሰድ ጥረት ላይ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያዊያንን ለስድት የሚገፋቸዉ ምንድን ነው?
በግጭት፣ በጦርነት፣ በአለመረጋጋት ብሎም በድርቅ እና በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከፍተኛ የስደት እና የመፈናቀል አደጋ የተጋረጠባት ኢትዮጵያ ለብዙ ሕገ ወጥ ስደተኞች መነሻ፣ መሸጋገሪያ እና መድረሻ መሆኗና ይህንንም የመከላከል ሥራ ለማጠናከር ተጨባጭ ምክንያት መሆኑን IOM ገልጿል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ