ኢሰመኮ የመዘዋወር ነጻነት አደጋ ላይ ወድቋል ሲል ላወጣው መግለጫ የመንግሥት ምላሽ
Description
ኢሰመኮ በአራት ክልሎች ባደረገው ምርመራ «በመንገዶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት መብት አደጋ ላይ መውደቁን» የጠቀሰበት መግለጫ «ሚዛናዊነት የጎደለው ነው» ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ከበደ ደሲሳ ማምሻውን ለዶቼ ቬለ በሰጡት ምላሽ ኢሰመኮ «የመንቀሳቀስ መብት በጣም የተገደበ አድርጎ፣ መንግሥት የሚያደርገውን እርምጃም እውቅና ሳይሰጥ ማለፉ ትክክል አይመስለኝም» ብለዋል።
ሚኒስትር ድኤታው የኢትዮጵያመንግሥት ያለፈው ክረምት ላይ «በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ዝርፊያዎችን፣ እገታዎችን እና መሰናክሎችን በተጠና መንገድ መቆጣጠር ይገባናል» ሲል ያስቀመጠውን አቅጣጫ ምን ያህል እየተገበረ ነው የሚለውን በመመለስ ይጀምራሉ።
የኢሰመኮ የስድስት ወራት የምርመራ ውጤት ምን ይላል?
ብሔራዊው የመብት ድርጅት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን ክትትል እና ምርመራ ባከናወነባቸው ቦታዎች በተለይም «በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚጣሉ የሰዓት እላፊ የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመንገዶች ላይ በሚጣሉ ኬላዎች፣ የመንገድ መዝጋት ትዕዛዞችና እርምጃዎች እንዲሁም በመንገዶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት መብት አደጋ ላይ መውደቁን» መገንዘቡን አስታውቋል።
ኢሰመኮ እነዚህ እርምጃዎች እና ጥቃቶች «ከመዘዋወር ነጻነት መብቶች ባሻገር በሕይወት የመኖር፣ የአካልና የንብረት ደኅንነት መብቶች ላይም ጥሰቶችን ማስከተላቸውን» ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ ከዚህም ባሻገር እነዚህ ችግሮች «የዕለት ከዕለት ተግባራትን በማወክና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽነትን በመገደብ በድርጊቶቹ ተጎጂዎች ላይ በቀጥታ ከሚደርሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪም በኅብረተሰቡ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል» ብሏል። ኮሚሽኑ በዚህ ችግር ውስጥ አሉበት በሚል የጠቀሳቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ፋኖ እና የቅማንት ታጣቂ ቡድናት ናቸው። የመንገድ መዘጋት፣ የሰዓት እላፊ እና በኬላዎች ላይ የሚደረጉ ቁጥጥሮች ጋር ተያይዞ ደግሞ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢሰመጉም መግለጫ አውጥቷል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) «በአማራ ክልል ያለው ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተስፋፍቶ የቀጠለ ሲሆን ከዚህ ግጭት ጋር ተያይዞም ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች እና በመንግሥት የጸጥታ ሀይሎች እየተፈጸመ ይገኛል»። ብሏል።
በተጨማሪም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች «ከፍተኛ የሆነ የሹፌሮች እገታ ያለ ሲሆን» የጸጥታ ችግርምክንያት የአካባቢው ማኅበረሰብ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንግልት የተዳረገ ሲሆን፤ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸውም በእጅጉ መገደቡን ኢሰመጉ ለመገንዘብ ችሏል ሲል ጠቅሷል።
መንግሥት ችግሩን ለማስቆም አስቀምጦት የነበረው አቅጣጫ
የኢትዮጵያ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ «የአሻጥር፣ የከተማና የገጠር ውንብድና፣ የኮንትሮባንድ፣ የሙስና፣ ሕገ ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር እና የመሳሰሉ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር የሕዝቡን ሰላም ማስከበር እንደሚገባ» ከጸጥታ ተቋማት አመራሮች ጋር ሰሞኑን ሲደረግ በነበረ ውይይት ላይ በስፋት መነሳቱን እና ርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ክረምቱ መውጫ ላይ አስታውቀው ነበር።
«በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ዝርፊያዎችን፣ እገታዎችን እና መሰናክሎችን በተጠና መንገድ መቆጣጠር ይገባናል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀጥታ ኃይላት «እነዚህን አካላት ከእኩይ ተግባራቸው መግታት፣ ብሎም ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባቸው አጽንዖት ተሰጥቶታል»፣ ለዚህ ተግባርም የየአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ወሳኝ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነሥቷል ሲሉም መግለጻቸው ይታወሳል።በተደጋጋሚ እየተፈፀመ የሚገኘው እገታ እና አስገድዶ መሰወር «የሥርዓት እልበኝነት» ማሳያ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታው አቶ ከበደ ደሲሳ እንዳሉት ይህ ችግር በኅብረተሰብ ተሳትፎ እየቀነሰ ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ