ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?
Description
ጋዛን ያንቀረቀበዉ፣ መካከለኛዉ ምሥራቅን ያተራመሰዉ፣ የተቀረዉን ዓለም ያስተዛዘበዉ የሁለት ዓመት ጦርነት ጋብ ሲል ባለፈዉ ሳምንት አፍሪቃ ቀንድ ላይ የቃላት ጦርነቱ ይንፈቀፈቅ ይዟል።በጦርነት ማግሥት ወዳጅነት፣ በወዳጅነት እፍታ መሐል ጠብ የሚገጥሙት የአዲስ አበባ፣ የአሥመራና የመቀሌ ገዢዎች ከ30 ዓመት በላይ እንደኖሩበት ያፍታ ፍቅር፣ ሥምምነት፣ወይም አቅም ማጣት ያዳፈነዉን ጦርነት ዳግም ለመጫር ከዲፕሎማሲ እስከ ጦር ሥልጠና እየተዘጋጁ ነዉ።ታዛቢዎች እንደሚሉት «አካባቢያዊ ኃይላት» የሚባሉ መንግሥታትም በግጭት፣ ጦርነት፣ ድሕነት የሚማቅቀዉን የሁለቱን ሐገራት ሕዝብ ለሚፈጀዉ እሳት ሞልቶ ከተረፋቸዉ ነዳጅ ጥቂቱን ቤንዚን እያርከፈከፉ ነዉ።ለምን? ላፍታ እንጠይቅ።አብራችሁኝ ቆዩ።
የአሥመራ፣ የካይሮና የመቃዲሾ ግንባር-አምና
መስከረም 30፣ 2017።አሥመራ።የኤርትራ፣ የግብፅና የሶማሊያ መሪዎች አስመራ ላይ ተሰብስበዉ ወዳጅነታቸዉን ለማጠናከር ተስማሙ።ለመገናኛ ዘዴዎች ፍጆታ «የአሥመራ መግለጫ» የተባለዉ የሶስቱ መሪዎች ሥምምነት በዚያን ወቅት በአዲስ አበባና በሞቃዲሾ መካከል በናረዉ ዉጥረት የአሥመራና የካይሮ ገዢዎች ከሶማሊያ አቻቸዉ ጎን መቆማቸዉን ያረጋገጠ እንደነበር ለማወቅ ጥልቅ የፖለቲካ ትንታኔ አልጠየቀም ነበር።
ታሕሳስ 2፣ 2017 አንካራ።በቱርክ ሸምጋይነት ሲደራደሩ የነበሩት የኢትዮጵያና የሶማሊያ ባለሥልጣናት የሁለቱን ሐገራት ጠብ ለማርገብ ተስማሙ።የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶሐን የሰበሰቧቸዉ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼሕ ማሕሙድና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ «የአንካራ መግለጫ» ባሉት ሰነድ ለጦርነት ያሰጋዉ ዉዝግብ መወገዱን አረጋገጡ።
የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ ወዳጅነት-ዘንድሮ
የሞቃዲሾና የአዲስ አበባ ገዢዎች ካንገትም ሆነ ካንጀት፣ ለጊዜዉ ይሁን ለዘለቄታዉ ባይታወቅም የመካሰስ፣መዛዛትና የዉጊያ ዝግጅት ፋይል በርግጥ ተዘጋ።የኤርትራ፣ የሶማሊያና የግብፅ ገዢዎች የጋራ ግንባር መፍጠራቸዉ አሥመራ ላይ በታወጀ ባመት ከሁለተኛ ቀኑ ዘንድሮ ትናንት የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ አዲስ አበባ ዉስጥ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር ተወያይተዋል።የኢትዮጵያ መንግሥት መገናኛ ዘዴዎች ዘገባ የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት የአዲስ አበባ ጉብኝትን ዓላማ፣ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር ያደረጉትን ዉይይት ፍሬ ሐሳብ አልጠቀሰም።
የጉብኝቱ ዓላማና የዉይይቱ ፍሬ ሐሳብ ምንም ሆነ ምን የአሥመራ መግለጫ በታወጀ ባመቱ፣ የሶማሊያና የኢትዮጵያ ጠብ በረገበ በ8ኛ ወሩ፣የአዲስ አበባና የአሥመራ ጠብ በተካረረበት ባሁኑ ወቅት የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት አዲስ አበባን መጎብኘታቸዉየአፍሪቃ ቀንድ መሪዎች ለጠባቸዉም ሆነ ለወዳጅነታቸዉ ዋና መሠረታቸዉ መርሕ ሳይሆን ስሜት፣ የሐገርና ሕዝብ ፍላጎት ሳይሆን ሥልጣን ለመሆኑ አንድ ግን ግልፅ አብነት ነዉ።
የአሥመራና የአዲስ አበባ ፍቅር-የጠላትሕ ጠላት ወዳጅሕ ነዉ-2010
የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰይድ ደግሞ ወደ 2010 መለስ ብለዉ ያኔ የአሥመራና አዲስ ሕዝብን ያስቦረቀዉን የኢሳያስ (ኢሱ) ዐብይ ፍቅርን አብነት ይጠቅሳሉ።
«በዐባይ አሕመድና በኢሳያስ አፈወርቂ አሥመራ ዉስጥ የተደረገዉ ሥምምነት በ2018 በፈረንጆች አቆጣጠር ሥጋቶች ነበሩ።የጥቅም ጋብቻ እንዳይሆን በእንግሊዝኛ Marriage of convenience ይባላል--እና ጥቅሙ በዚያን ጊዜ ምናልባት ያገናኛቸዉ የህወሓት ኃይል ለሁለቱም ሥጋት ሆኖ ሥለቀረበ ሁለቱን ኃይላት ወደ 2018 ሥምምነት ያስገባቸዉ ማለት ነዉ።»
ከአስመራ-አቡዳቢ-ጂዳ እየዞረ የተፈረመዉ ሥምምነት ዝርዝር ይዘት ለሕዝብ በግልፅ አልተነገረም።የአሥመራና የአዲስ አበባ ሕዝብ ግን በየአደባባዩ ለመጨፈር የሥምምነቱን ዝርዝር ይዘት ማወቅ፣ የጠላትሕ ጠላት-ወዳጅነቱን ማስተንተን፣ መጠየቅም አላስፈለገዉም።
የአስመራና የአዲስ አበባ ገዢዎችበሆይሆይታ፣ ጭፈራ-ቱማታ ሲታጀቡ፣ የመቀሌ ገዢዎች ባንፃሩ ከኢትዮጵያ ጦር ከ75 ከመቶ የሚበልጠዉን ኃይል በመቆጣጠራቸዉ አብጠዉ ነበር።ዉጤቱ ጦርነት።በትንሽ ግምት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዉ የፈጀዉ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለዉ ጦርነት ህወሓትን አዳክሞ በስምምነት ሲቆም የአሥመራና የአዲስ አበባዎች ፍቅር ወይም በአቶ አብዱረሕማን አገላለፅ የጥቅም ጋብቻም አበቃ።
ጦርነቱ አበቃ።የአሥመራና የአዲስ አበባ ፍቅር ሲሻክር፣ የአሥመራና የመቀሌ ጠብ ለዘበ
የኢትዮጵያ መሪዎች የአሥመራ መሪዎችንና የአማራ ክልል ታጣቂዎችን ማግለላቸዉን አቶ አብዱረሕማን የፖሊሲ ስሕተት ይሉታል።
«የትግራይ ኃይል እንደተመታ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ከአጋሮቹ በተለይ ከኤርትራና ከፋኖ ለየት ያለ ርምጃ መዉሰ,ድ ጀመረ።ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት ወስኖ ብዙም ጊዜ ሳይሰጥ ሳይደራደር ወደ ግጭት እንዲገባ ተፈለገ ማለት ነዉ በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል።ከኤርትራም ጋር በፊት ያልነበሩ የወደብ ጉዳይ፣ የ,ኤርትራን ነፃነትም---የመሳሰሉ ጉዳዩች እያነሱ ናቸዉ።እዚሕ ላይ የሚታየዉ እንግዲሕ የፖሊሲ ስሕተት እንዳለ ነዉ።»
የአሥመራና የአዲስ አበባ ገዢዎች ግንኙነት ከወዳጅነት ወደ ጠላትነት ሲለወጥ የአሥመራና የግብፅ፣ የአሥመራና የህወሓት ጠላትነት ይቀዘቅዝ፣ አልፎም ወደ ወዳጅነት ይለወጥ ገባ።
የአስመራና የመቀሌ ገዢዎች ከ1990 እስከ 1992፣ ከ2013 እስከ 2015 በገጠሟቸዉ ጦርነቶች ደም ባቃቡት ሕዝብ ሥም የሕዝብ ለሕዝብ ጥምረት (ፅምዶ) እያሉ ወዳጅነታቸዉን ያጠናክሩ ያዙ።
የኢሳያስ ማሳሰቢያ፣ የዐብይ አፀፋ «የቀይ ባሕር ታሪክ ይታረማል»
ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ1990 ጀምሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሁን ቃለ መጠይቅ ይስጡ፣ ወይም ባደባባይ ይናገሩ ህወሓትን ሳያወግዙ አያልፉም ነበር።
ባለፈዉ ግንቦት ባደረጉት ንግግር ግን ህወሓትን ዘለዉ የዉግዘት፣ ወቀሳ፣ ትችት ኢላማ ያደረጉት የአዲስ አበባ መሪዎችንና ተባባሪዎቻቸዉን ነበር።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አፀፋ ዘገየ እንጂ አልቀረም።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ባለፈዉ ጵዋግሜ እንዳሉት ሺሕ ዓመት ያስቆጠረዉ የአባይ ወንዝ ታሪክ ከተቀየረ፣ የቀይ ባሕር ታሪክ የማይታረምበት ምክንያት የለም።
«ቀይ ባሕር የዛሬ ሠላሳ ዓመት ነዉ።የትናንትና ታሪክ ነዉ።ነገ ይታረማል፣ ከባድ አይደለም።(ይኸ ግን የሺህ ዓመት ነዉ) የሺ ዓመት ያልተሞከረ ነገር ነዉ የተፈታዉ።እንደ ቀይ ባሕር ያሉ ከአባይ ያነሰ ነገር ነዉ።»
የደብዳቤዎች እሰጥ አገባ
ህወሓትን ከአሥመሮች ጋር ያቆረኘ የመሰለዉ የቃላት እሰጥ አገባ የአሰብ ወደብን ሰበብ አድርጎ እየናረ ነዉ።የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለፈዉ መስከረም ማብቂያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በፃፈዉ ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥትና «አክራሪ» ያለዉ የህወሓት አንጃ «ኢትዮጵያን ለመዉጋት እየተዘጋጁ ነዉ» ይላል ደብዳቤዉ ሁለቱ ኃይላት የአማራ ክልል አማፂያንን ወይም ፋኖን «በገንዘብ፣ በዘመቻና በዕዝ ይረዳሉ» በማለት ወቅሷልም።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረ መስቀል የኢትዮጵያን ወቀሳ «የቀድሞ ግዛትን ለማስመለስ ያለመ፣ ወታደራዊ የፀብ አጫሪነት የታካለበት ፕሮፓጋንዳ» በማለት አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።
የህወሓት መሪዎችም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለአፍሪቃ ሕብረት በጻፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያ መንግሥትን ደብዳቤ አደገኛ፣ እዉነትን የገለበጠ፣ በዳይን እንደ,ተበዳይ የቀረበበት በማለት ተቃዉሞታል።
ቀጥሎስ ይዋጉ ይሆን?
ኢትዮጵያ ዘንድሮ የሕዳሴ ግድብን አስመርቃለች።፣የካሉብ ጋዝ ማምረቻና የማደባሪያ ፋብሪካን የመሠረት ድንጋይ ጥላለች።አማራ ክልል ከፋኖ፣ ኦሮሚያ ክልል ከኦነሠ ወይም OLA ጋር የሚደረገዉ ዉጊያ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይለይበት እንደቀጠለ ነዉ።የኢትዮጵያ ምናልባትም የኤርትራ ክረምት ግን አብቅቷል።ዓየሩ ለወታደራዊ ንቅናቄ ይመቻል።እና ይዋጉ ይሆን?
«እንደዚያ ነዉ የሚመስለዉ ምክንያቱም በሁለቱ በኩል ያለዉን (ልዩነት) ግንኙነት በሰላም ተደራድሮ የመፍታት አቅሙም፣ ፍላጎቱም ያለ አይመስልም።»
ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ እየተዘገበ ነዉ።ሰሞኑን ከአሥመራ የሚናፈሱ መረጃዎች ደግሞ «ለሚፈጠረዉ ቀዉስ ነዳጅ ለመቆጠብ» በሚል የአስመራ የሕዝብ ማመላሻ ተሽከርካሪዎች ሥራ እንዲያቆሙ ታዘዋል።
የዉጪዎቹ ኃይላት፣ የሁለቱ መሪዎች ባሕሪ
የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት ደግሞ በሱዳኑ ጦርነት ሰበብ ከኤርትራ ጋር እንደጠላት የሚተያዩት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ገዢዎች የኢትዮጵያ መንግሥትን በመደገፍ፣ በሕዳሴ ግድብ ሰበብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበዉ ግብፅ ኤርትራን በመርዳት ጠቡን እያራገቡት ነዉ።
ከዉጪዎቹ ኃይላት ድጋፍና ግፊት ይልቅ የአዲስ አበባ፣ የአሥመራና የመቀሌ ገዢዎች ባሕሪና አስተሳሰብ ጦርነትን እንደብቻኛ አማራጭ እንዲያዩ ሳደርጋቸዉ አልቀረም።አቶ አብዱረሕማን እንደሚሉት በተለይም የአስመራና የአዲስ አበባ መሪዎች አስተሳሰብ ባካባቢዉ ካንድ በላይ አስገባሪ ሊኖር አይችልም ዓይነት ነዉ።ባንድ ቆጥ ሁለት አዉራ ዶሮ አይሰፍርም እንደሚባለዉ።
«የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አምቢሽን ደግሞ አለ።በኢትዮጵያ የመሳፍንት ታሪክ በጣም ኦብሴስድ ናቸዉ።እና ይሕንን ካስፈፀምኩ ምናልባት በኢትዮጵያ ተቀባይነት ይኖረኛል፣ ካሁን በ,ኋላ ከ20 እስከ 30 ዓመት የሚደርስ ያስተዳድሩ ይሆናል የሚል ሕልም ሊኖራቸዉ ይችላል።በኤርትራ በኩልም ዘ ሴም ሜንታሊቲ አለ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ ልክ እንደመጣ ለዲሞክራሲ ይሆን፣ ለሰብአዊ መብት----»
ከእንግዲሕ የሚሆዉን ጊዜ ነዉ በያኙ።ለዛሬዉ ይብቃን።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ























