በደሴ ከተማ በተማሪ ሊዛ ደሳለ ላይ የተፈጸመው ግድያ ያስነሳው ቁጣ
Description
ተማሪ ሊዛ ደሳለ በደሴ ከተማ በአንድ የግል ኮሌጅ በጤናው ዘርፍ እየተማረች ሳለ ነበር መስከረም 27 ምሽት ተገድላ የተገኘችው የዚች እንስት መገደልም በማህበራዊ ሚዲያውም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ እናም የደሴ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚገልፁት አካባቢው በምሽት ብቻም ሳይሆን በቀንም ጭምር በሴቶች ላይ ጥቃትየሚደርስበት እየሆነ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ሰውን ያህል ነገር ህፃናት ተደብድበው ሲታይ ማለፍ ኢትዮጵያዊ ባህል አይደለም፤ በመስከረም 27 የሞተችው ልጅ ገለዋት ነው የተገኘችው ህብረተሰቡ ገና የእሱም ልጅ የዚህ ዓይነት ጥቃት ይደርስባታል ማለት ነው፡፡ ፒያሳ ላይ የባንክ ዘበኛ አንድን ሴት ሲደበድባት እየታየ ዝም ብሎ ማህበረሰቡ ያልፋል፤ ይህ አግባብ አይደለም፡፡››
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት መባባስ
በአደባባይ ገሀድ ወጥቶ ከሚደመጠው የሴት ልጆች ጥቃት ይልቅ ፣ በየቤቱ ቤት ይፍጀው የተደበቀው በርካታ ነው የሚሉት በደሴ ከተማ በሴቶች ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሰራተኞች የኑሮ ውድነት፣ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል የተደጋጋሚ ጥቃት መንስኤ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
‹‹ጦርነት ፣ የኑሮ ውድነት፣ ሰው ተስፋ መቁረጥ የሴቶች ጥቃት በጣም እየጨመረ ነው የሕግ መላላት ምንም እርምጃ አለመውሰድ ምክንያት ነው፡፤ እስከዛሬ አስገድዶ መደፈር ብቻ ነበር የምንሰማው አሁን ደግሞ ደፍሮ መግደል ብዙ እየሰማን ነው፡፡››
የህግ ክፍተት ወይስ የሴቶች ጥቃትን እንደ ልማድ መዉሰድ
በወሎ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፣መምህር ሀሊፈት አሊ፣ የሴቶችን ጥቃት በተመለከተ እንደ ሀገር ለብቻው የተዘጋጀ ሕግ ባይኖርም በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ በሚገባ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን የሴቶችን ጥቃት ትኩረት ሰጥቶ አለመመልከት እና የሴት ልጅን ጥቃት በቸልተኝነት መመልከት እየተለመደ ነው ይላሉ፡፡
‹‹በተለይ ከጦርነት በኋላ የሴቶች ጥቃት ልማድ ተደርጓል በቃ የቁጥር ጉዳይ እንጂ ዘግናኝ የሆነ ጉዳይ ሳይሆን ሴት ልጅ ሴት ስለሆነች የተለመደ የሚደርስባት ነገር ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡››
በተለይም ሴቶች ላይ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ ጥቃት አድራሾችን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት መጨመር ፣ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ጥፋተኛ ማድረግ በማህበረሰቡ ዘንድ እየበረታ መምጣት ለጥቃቱ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ተደርጎ ነው የሚገለፀው፡፡
‹‹ጥቃቱን ያደረሰውን ሰው ምን ብታደርገው ነው ብለው ጭራሽ ጥቃት ፈፃሚውን ሰው ተጠያቂ ከማድረግ እንደዛ እንዲያደርግ ምን ገፋፋው ብለን ሰበብ እንፈልግለታለን፡፡››
የተማሪ ሊዛ ደሳለኝ የግድያ ወንጀልም ሆነ ሌሎች በየጊዜው ጥቃት የሚደርስባቸውን ሴቶች ላይ የሚፈፀመው ወንጀል አሰቃቂ እየሆነ መምጣቱን ነው የሴቶች መብት ተሟጋቾች የሚገልፁት፡፡
‹‹ደሴ ከተማ ላይ የምትሰማቸው ጥቃቶች ዘግናኝ ናቸው፤ የህግ ሰዎች፤ የጤና ባለሙያዎች ህፃናትን አስገድደው እየደፈሩ መሆኑ ቤተሰብ፤ አባት ልጁን፣ ሰሞኑን የሰማነው አስገድዶ መድፈር ከዚያ መግደል በጣም ከባድ ሆኗልጉዳዩ፡፡››
«አስፈላጊው ምርመራና ማጣራት እየተካሄደ ነው» የደሴ ከተማ ፖሊስ
የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮ/ር ጥላሁን ታደሰ በበኩላቸው በከተማዋ የተፈፀመው ድርጊት አሳዛኝ መሆኑን ገልፀው ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራና ማጣራት ለማድረግ እየሰራ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ምርመራ እያጣራን ነው ፣ የህክምና መረጃ እየሰበሰብን ነው፤ ሌሎች ለምርመራ አጋዥ የሚሆኑ ማስረጃዎች እየተሰበሰቡ ነው በጥርጣሬ የታሰሩ ሰዎች አሉ፤ ስራእየሰራን ነው፤ ወደፊት የምንደርስበትን እናሳውቃለን፡፡ የተፈፀመው ግን አሳዛኝ ነው፡፡››
ኢሳያስ ገላው
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ